>
11:09 pm - Saturday December 4, 2021

ኢትዮጵያ ትቅደም (ሙክታሮቪች ኡስማኖቭ)

ኢትዮጵያ ትቅደም
ሙክታሮቪች ኡስማኖቭ
(በዚህ አርዕስት ስለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ክርር ያለና ፅንፈኛ አቋሞችን እናንፀባርቃለን)
ኢትዮጵያትቅደም 11
ኢትዮጵያ ትቅደም ማለት ተጨፍልቀን አንድ እንሁን ማለት አይደለም! አንድነት አንድአይነትነት አይደለም! ይህ ኢትዮጵያን ካለማወቅ የሚመጣ ተራ ማስፈራርያ ነው። ከዚህ ቀደም ይህ ማስፈራሪያ ሀገርን ጎዳ እንጂ አልጠቀመም!
የኢትዮጵያዊነት ጥንካሬ ያለው በብዙሃነቱ ላይ ነው። 85 እግር እንዳለው ጠረጴዛ ቁጠረው። በየትኛውም ተራ ነፋስና አቧራ አይወድቅም። ማን ይህን ፅኑ መሰረት ለመናድ ይሻል? ማንም! ሁሉም አንዳንድ እግር ይዞ ጠርጴዛ ነኝ ካለ ግን ለአንድ ደቂቃ አይቆምም፣ ሁሉም ይወድቃል። ኢትዮጵያ መሆን የምትችለው አንድ አገር ነው። የጥንካሬዋ መሰረት ብዙሃነቷ ነው። የሀይል መሰረቷ አንድነቷ ነው።
አንድነቷን የሚያቀነቅነው ኢትዮጵያዊነት የበለጠ ለጥንካሬዋ ይተጋል!
ከኢትዮጵያዊነት ጋር ወደፊት!!!
ኢትዮጵያትቅደም 12
ከሊቃውንት አንደበት ስለ ኢትዮጵያ ማስረዳት አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል! ተቀበል! ፕሮፌሰር መስፍን፣ የንቅናቄያችን መሰረት ለማድረግ በቅርቡ የምንጠይቀያቸው የኢትዮጵያ አባት ናቸው!!!
 
ያስፈራል፤ግን ኢትዮጵያአትፈርስም !
ይቺ ኢትዮጵያ የምትባል አገር ስንት የመከራ ወንዞችን ተሻግራለች! ገና ስንት ትሻገራለች! ስንት የግፍ ተራራዎችን አቋርጣለች! ገና ስንት ታቋርጣለች! ስንት የበደል ሰይፎችንና ጦሮችን አምክናለች! ገና ስንት ታመክናለች! ስንት የውጭ ኃይሎችን አሳፍራለች! ገና ስንቱን ታሳፍራለች! ስንት አምባገ- ነኖችን እያለቀሰች ቀብራለች! ገና ስንቱን ትቀብራለች! ጭቆና ከኢትዮጵያውያን ደም ሙልጭ ብሎ ወጥቶ በነፃነት፣ በእኩልነት፣ በዳኝነት በጠራ ደም እስቲተካ ድረስ ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ዘርግታ ትጸልያለች! እግዚአብሔርም ቃል ኪዳን አለበት ይሰማታል! የኃያላን ኃያል ኢትዮጵያ እንድትፈርስ አይፈቅድም !
የኢትዮጵያን መፈራረስ የሚመኙ ግለሰቦችም መንግሥቶችም ሞልተዋል ፤ ኢትዮጵያ እንድትፈራርስ የሚመኙ ጭንጋፍ ልጆችም አሏት፤ ማኅጸንዋ እየደማ እየረገማቸው ሰላምና እንቅልፍ አጥተው አብጠው ይፈነዳሉ፤ የኢትዮጵያን መፈራረስ የሚመኙ መንግሥቶች ሁሉ ከዚህ በፊት ቀድመው ፈራርሰዋል፤ ወደፊትም ይፈራርሳሉ። የአገራቸው ፍቅር፣ የእርስበርሳቸው ዝምድና፣ የተራራውና የሸለቆው፣ የሜዳውና የገደሉ፣ የበረሀውና የለምለሙ፣ የዝናቡና የወንዙ፣ የዓየሩና የነፋሱ፣ የበዓላቱና የድግሱ፣ ያለውን አብሮ መቋደሱ፣ ተዝካሩ፣ ሙታዓመቱ ለሞቱ፣ መላእክቱ፣ ቅዱሳቱ፣ ሰማዕታቱ፣ እየተሸከሙ ያደረሱት ጸሎቱ፣ ለምዕተ-ዓመታት የተከማቸው እምነቱ፣ ሃይማኖቱ፣በዚህ ሁሉ የተገነባው ኅብረቱ እንዴት ይፈርሳል! ማን ችሎ ያፈርሰዋል! አፍራሾች ቀድመው ይፈርሳሉ !
አንዳንዶች ቢጨነግፉም፣ አንዳንዶች ቢክዱም፣ አንዳንዶች ሆዳም ቢሆኑም ፣ አንዳንዶች ቢወላውሉም ፣ ኢትዮጵያ ልጆች አሏት፣ አሁንም የሚሞቱላት፣ ያልበሏት፣የሚሳሱላት፤ ያልሸሿት፤ አፈሯን የሙጢኝ ብለው አፈርሽ እንሁን የሚሏት፣ ደሀነትም ሆነ ጭቆና ካንቺ አይለዩንም የሚሏት፣ ኢትዮጵያ ዛሬም ልጆች አሏት ስትፈርስ ቆመው የማያዩ፣ ሲያማት ነፍሳቸውን ዘልቆ የሚያማቸው፣ ሳልፈርስ አትፈርስም ነው ቃል ኪዳናቸው። ቱርክና ግብጽ መጥተው ሄደዋል፤ ፖርቱጋል መጥቶ ሄዷል፤ እንግሊዝ መጥቶ ሄዷል፤ ኢጣልያ መጥቶ ሄዷል፤ ጠላቶች እየመጡ በመጡበት ተሸኝተዋል፤ ወዳጆች በጨዋነት ተስተናግደው ተዋኅደዋል፤ ቤተ ሙሴ፣ ቤተ ክርስቲያን፣ ቤተ እስልምና ኢትዮጵያዊ ሆነዋል፤ ዛሬ እንግዳ አይደሉም፤ ዛሬ ባዕድ አይደሉም፤ ኢትዮጵያ በፍቅር ለመጣ ፍቅር ነች፤ ምቹ ነች፤ በጠብ ለመጣ እሾህ ነች፤ ትዋጋለች።
ኢትዮጵያ፣ ነቢዩ ኢሳይያስ ለአንቺ የተናገረው ይመስለኛል ፤ ‹‹ብርሃንሽ መጥቶአልና፣ የእግዚአብሔርም ክብር ወጥቶልሻልና ተነሺ፤ አብሪ፤ እነሆ ጨለማ ምድርን ድቅድቅ ጨለማም አሕዛብን ይሸፍናል፤ ነገር ግን በአንቺ ላይ እግዚአብሔር ይወጣል፤ ክብሩም በአንቺ ላይ ይታያል፤ አሕዛብም ወደብርሃንሽ፣ ነገሥታትም ወደመውጫሽ ጸዳል ይመጣሉ። ዓይኖችሽን አንስተሽ በዙሪያሽ ተመልከቺ፤ እነዚህ ሁሉ ተሰብስበው ወደአንቺ ይመጣሉ፤ ወንዶች ልጆችሽ ከሩቅ ይመጣሉ፤ ሴቶች ልጆችሽንም በጫንቃ ላይ ይሸከሙአቸዋል፤ በዚያን ጊዜ የባሕሩ በረከት ወደአንቺ ስለሚመለስ፣ የአሕዛብም ብልጥግና ወደአንቺ ስለሚመጣ አይተሽ ደስ ይልሻል፤ ልብሽም ይደነቃል፤ ይሰፋማል፤ የግመሎች ብዛት የምድያምና የጌፌር ግመሎች ይሸፍኑሻል፤ ሁሉ ከሳባ ይመጣሉ፤ ወርቅንና ዕጣንን ያመጣሉ፤ የእግዚአብሔርንም ምስጋና ያወራሉ፤ የቄዳር መንጎች ሁሉ ወደአንቺ ይሰበሰባሉ፣ የነባዮትም አውራ በጎች ያገለግሉሻል፤ እኔን ደስ ሊያሰኙ በመሠዊያዬ ላይ ይወጣሉ፤ የክብሬንም ቤት አከብራለሁ።›› (60፦1-7) ኢትዮጵ ትወድቅ ይሆናል፤ ግን ያለጥርጥር ትነሣለች፤
በፊትም ወድቃ ተነሥታለችና፤ ኢትዮጵ ትሰነጠቅ ይሆናል፤ ግን ያለጥርጥር ትገጥማለች፤ በፊትም ተሰንጥቃ ገጥማለችና፤ ለኢትዮጵያ በጎ የማይመኙላት የአየሉ ቢመስሉም የንስሐ ጊዜ ስትሰጣቸው ነው፤ ኢትዮጵያ ዕብሪተኞችንም ትሕትና ታስተምራቸዋለች፤ ዕብሪተኞች ከነዕብሪታቸው በራሳቸው እሳት ቀልጠው እስቲያልቁ ኢትዮጵያ ትእግስትዋ አያልቅም፤ ኢትዮጵያ ትእግስት ነችና። በበጎ መንፈስ እስከተመራን ድረስ፣ ፍርሃትንና አለመተማመንን፣ ጥላቻን፣ ጠብንና ድብድብን፣ ሊዘሩብን ከሚፈልጉ ርኩሳን መናፍስት ከራቅን ኢትዮጵያችን አትፈርስም፣ የደፈረሰውም ቶሎ ይጠራል።
(የኔታ ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም)
ፍትሕ ጋዜጣ 2004 ዓ.ም.
ኢትዮጵያትቅደም 13
ኢትዮጲያ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ልዩ የሚያደርጋት በአደዋ ጦርነት በነጮች ላይ የተቀዳጀችው ድል አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ ከሌሎች አፍሪካዊያን በተለየ በኢትዮጲያ ስር የነበሩት ነባር ግዛቶች፡- ሸዋ፥ ጎንደር፥ ትግራይ፥ ጎጃምና ወሎ በደቡብ፥ ምስራቅና ምዕራብ አቅጣጫ ከነበሩት ሌሎች ብሄሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች በመቀናጀት የቅኝ-ገዢዎችን በጋራ ለመመከት መስማማታቸው ነው።
 ስለዚህ፣ ኢትዮጲያዊያን በኩራት የሚጠቅሱት የአደዋ ድል የመጨረሻ ውጤት እንጂ መነሻ ምክንያት አይደለም። ከአደዋ ድል እና ከኢትዮጲያ ነፃነት በስተጀርባ ያለው ሚስጥር የኢትዮጲያ ብሄሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች በጋራ በመሆን ራሳቸውን ከቅኝ-ግዛት ወረራ ለመከላከል የፈጠሩት የወደፊት አብሮነት (common future) ነው።
 ሌሎች አፍሪካዊያን ይህን የወደፊት አብሮነት መፍጠር ስለተሳናቸው ለቅኝ-ግዛት ተዳርገዋል። ኢትዮጲያዊያን ግን ራሳቸውን ከቅኝ-ገዢዎች ወረራ መከላከልን ዓላማ አድርገው የፈጠሩት አብሮነት ለአንድነታቸው መሰረት ሆኗል።
ማን?! ኢትዮጵያዊነት! ጎሰኝነትማ ለቅኝ ሀገራት ውርደት እንደዳረጋቸው 52 የአፍርካ ሀገራት ምሳሌ ናቸው!!! ኢትዮጵያ ለነፃነታቸው በመቆም ምሳሌ ነች! በጣም ያሳዝናል ይህን እውነት ለኢትዮጵያውያን መንገር!!
ኢትዮጵያዊነት መሰረቱ ጥልቅ ነው ጓዶች! የጎሰኝነት ግን የገበጣ መጫወቻ ያህል ነው!!! ዘመኑ ነው እንድንፎካከር ያደረገን እንጂ የያዝነው እውነት የትየለሌ ድረስ ሩቅ ነው!
ኢትዮጵያትቅደም 14
ኢትዮጵያ የሚለው ቃል ከአንድም ብሄር ጋር ምንም የትርጉም አንድነት የሌለው ኒውትራልና አካታች ረቂቅ ቃል ነው! ኢትዮጵያ የሚለው ቃል ሲጠሩትም ሆነ ሲሰሙት መንፈስን የሚወር ስሜት ያዘለ ተዓምረኛ ቃል ነው። ኢትዮጵያ የሚለው ቃል ሲጠሩት ቶሎ አፍ ውስጥ ማለቅ የሌለበት እንደ ፀሎት መርዘም ያለበት ማግነጢሳዊ ቃል ነው!!!!ኢትዮጵያትቅደም
ኢትዮጵያትቅደም 15
የትግላችን አደናቃፊ የብሄር ፖለቲካን ገላልጠን በማሳየት ትውልዱን በማስተማር ወደ የራሳችን ንቅናቄ ማምጣት ያስፈልጋል!!! ወገን አትሸወድ! የጎሳ ፖለቲካን የብሄር ይሉታል። በዚህ ላይ እንመለሳለን። ባሉት መሰረት የብሄር ፖለቲካ ምንድነው? የሀሳብ ትግሉ ይፋፋም!!!!!
የእገሌ ብሄር ሀሳብና አስተሳሰብ የሚባል ነገር የለም። እርግጥ የአንድ ብሄር አባላት አብላጫቸው የሚደግፉት ሀሳብ ይኖራል። በአንድ ማህበርም አብላጫው የሚቀበለው ሀሳብ እንደሚኖረው። ያ ሀሳብ ገዢ ሀሳብ የሚሆነው በዴሞክራሲያዊ የድምፅ አሰጣጥ ሂደትን ተከትሎ ነው። የብሄር ፖለቲካ አራማጅ ግን አንዳቸውም የብሄራቸው ውክልና የላቸውም።
የብሄር ጥቅምና ፍላጎትን ማንንም ጠይቀው፣ ምርምር አድርገው፣ የብሄር አባላትን ፍቃድና ውክልና አግኝተው አያውቁም። የዚህ ብሄር አስተሳሰብ፣ ሀሳብና ርእዮተአለም የዚያ ብሄር አስተሳሰብና ሀሳብ የሚባል የተረጋገጠ ነገር የለም። የግለሰቦች ሀሳብ ነጥሮና ተቀምሮ አብላጫው የሚደግፈው ሀሳብ ሊገኝ ይችላል። ይህም የግለሰቦች ሀሳብ ነው፣ ጊዜያዊ ነው። በጊዜ ሂደት ሊለወጥ ይችላል። የብሄር ማንነት ግን አይለወጥም።
ብሄር ለፖለቲካ ስብስብ ሲውል ቆይቶ የሀገር መፍረስ አደጋ የሚያመጣ ነው። ብሄር ላይ የሚንጠለጠል ፖለቲካ ለሰጥቶ መቀበል፣ ፍላጎቶችን ለማጣጣም አይመችም። አይዲዮሎጂው ወደፊት ለእድገት የሚያመች የመፍትሄ ሳይሆን የቂም፣ የጥላቻና የእኛብቻ አይነት ግትር ነው። ዘውጌ ብሄርተኞች ባጠቃላይ ለአንድ ብሄር ብዙ ወኪሎች ያለውክልና የእንደራሴነት ሹመት ለራሳቸው የሚሰጡት ለራሳቸው የስልጣን ጥም ነው፣ በሀሳብ የሚለያዩትም ብሄር ጉኡዝ ነገር ስለሆነ ማሰቢያ አዕምሮ ስለሌለው ነው። ግለሰቡ ነው የሚያስበው፣ መብትም የግለሰብ ነው። የግለሰብ ስብስብ የሆነው ብሄር በለው ሌላ ቡድን በግለሰብ ነፃ ፍቃድ ላይ የሚመሰረት ስብስብ ከሆነ ብቻ ነው ሀሳቡ አትሊስት የማጆሪቲው ሊታወቅ የሚችለው። በብሄር ፖለቲካ ግን ከናት ማህፀን የወጣ ልጅ ገና እንደተወለደ ፖለቲከኛ ነው። እጣ ፈንታው ያርባ ቀን እድሉ ተወስኖለታል። ይህ ሃላቀር ፖለቲካ ነው። በግለሰብ ፈቃድ ስብስብ የምትመሰረተው ቡድን የግለሰቦቹ ሀሳብ ፍላጎትንና ጥቅምን መሰረት አድርጎ ሊደራጅ ይችላል። የዘውጌ ብሄርተኝነት ስብስብ ግን በአርባቀን እድልህ የሚወሰን ፀረደሞክራሲና ሰው የመሆንን ፀጋ ገፋፊ ነው።
ሰው መሆናችንን መስመለሻ እስትራቴጂ ኢትዮጵያዊ ማንነታችን ማስከበር ነው!!
ኢትዮጵያዊ ማንነት አሁነኑ!!
ኢትዮጵያትቅደም 16
በድሬደዋ 40 40 20 የሚባል የመንግስት መስሪያቤት መቀጠሪያ የኮታ ቀመር አለ። ከመቶ አርባ ለኦሮሞ፣ አርባው ለሶማሌ የቀረው ሃያ ከመቶ ለቀሪዎቹ ብሄርብሄረሰቦች!!! ይህ ከአፓርታይድ ስርዓት ምን ይለያል? ከሁለቱ ብሄር ውጪ ከተወለድክ አንተ ባልመረጥከውና በድክመትህ ምክንያት ባላገኘኸው ጎሳ ምክንያት ሀገርህን የማገልገል ዕድልህ ከሌሎች ብሄረሰቦች፣ ጎሳዎች (whatver the fuck you call it) ጋር ሃያ ፐርሰንት ነው። ይህ ቀመር አዲሳባ የማይገባበት አንዳችም ምክንያት የለም። ዛሬ ቀለም እንቀባ፣ ነገ ደግሞ ኮታ!!! ኖ ዌይ! የሀገሬ  ወጣት ተነስ!! የአባቶች ውርስ በሆነች ሀገር ላይ በጎሰኞች እጣፈንታህ አይወሰን! እጣ ፈንታህን በእጅህ አስገባ! ኢትዮጵያዊ ማንነትህ እንዲከበር አስረግጠህ ጠይቅ!!! ትግሉ ይፋፋም! ዘራፍ! ከጎሰኞች መብት አንለማመጥም! ነጥቀን እንወስዳለን! ሰው መሆናችንን ነጥቀን እንቀበላለን! እንዲህ ነው!
ኢትዮጵያትቅደም 17
የአዲሳባ ጉዳይ ንቅናቄያችን በዚህ መንገድ ይመለከተዋል!!! ከሸነግ ጋር ለምናደርገው የጋራ አላማም ይጠቅማል!!
መጀመሪያ የአዲስ አበባ ህዝብ በህገመንግስቱ እንኳ የተረጋገጠለትን የራስን በራስ ማስተዳደር መብቱ የለውም። አዲስ የአዲስአበቤ እንጂ የማንም አይደለችም። ማንም ከክፍለ ሀገር መጥቶ ነው ሚመራት ከክፍለ ሀገር ሞዴል አመራር መጥቶ ነው ሚመራው።  በስልጣን ረገድ በ ብሄር ስብጥር ነው   አዲስ ግን ይህንን የብሄር ስብጥር አታውቅም። ይህ ባለበት ሁኔታ የአዲስ ችግር አይፈታም። የአዲስ ልጅ ከ ፖሊስ ጀምሮ እስከ ዳኛ ድረስ በተወለደበትና ባደገበት ከተማ እንዳይሰራ ተደርጎል።
በጎሰኝነት ቅኝት በተቃኘ ከተማ መኖር የማንኛውም ነጻነት ፈላጊ ዜጋ የመጀመሪያው ምርጫ አይሆንም። ጎጥ ያፍንሃል። ጠና ካለም ይገድለሃል።ስለእዚህ ሁሌም ሽሽት ያምርሃል። አዲስአበቤነት ትንሿ ኢትዮጵያዊ ማንነት ነው! የአዲስአበቤ ትግል የኢትዮጵያዊነት ትግል ነው! አይደለም እንዴ!?
አዲስአበቤ – ኢትዮጵያ
የሀሳብ ትግሉ ይፋፋም!!!
Filed in: Amharic