>
5:13 pm - Sunday April 20, 7400

የኦሮሞ ፖለቲካ በጽንፈኞች እንዳይጠለፍ? (ሀይሌ ግብሬላ)

የኦሮሞ ፖለቲካ በጽንፈኞች እንዳይጠለፍ?
ሀይሌ ግብሬላ 
* ኦነግ ከታሪክ እስረኛነት ተላቆ የኦሮሞንን ሕዝብ የሚመጥንና የጸረ ወያኔ ትግሉን የሚያጠናክር ሃላፊነትን ሊወጣ ይገባል
ኦሮሞ አቃፊ የሆነ የጉዲፈቻ ምርጥ ባህል ያለው ማህበረሰብ እንጂ አንዳንድ አፍራሾች እንደሚያራግቡት የአግላይነት ልማድ የለውም:: የኦሮሞ የአማራውና የሌሎች ኢትዮጵያውያን ብሄሮች በመከባበር ላይ የተመሰረተ ስርዐት ከመገንባት ውጪ ምንም አይነት አማራጭ የለንም
ለዛሬይቱ ኢትዮጵያ እዚህ መድረስ የኦሮሞው ወገናችን ድርሻ ቀላል አይደለም:: ዘመን ከባተ ፊደል መቁጠር ሲጀመር ከስልጣኔ ጋር ሰይጣናዊ የጥላቻ እርዕዮተ ዓለም የተጋቱት የመጀመሪያዎቹ የኦሮሞ ታጋይ ድርጅቶች ያመጡት ፈተና ይህው ለዛሬው ትውልድ ተርፏል:: ጠባብና ጨለምተኛ የሆኑት አንዳንድ አክቲቪስቶችና የፖለቲካ መሪዎች ትውልዱን በዛገ የታሪክ እግረሙቅ ጠፍረው የተጨቋኝነት ትርክታቸውን እየተጋተ በበታችነት ደዌ ተጠቅቶ ከዘመኑ ጋር እንዳይራመድ ወደጋርዯሽ ዘመን እየወሰዱት ይገኛል::
በዚ ባለንበት የስልጣኔ ዘመን አውሮፓና አሜሪካ ኖረው የቆንጨራ አያያዝን የሚያስተምሩና ያጡትን የዘረፋ ስልጣን ለማስመለስ የሚተጉ : ተጋግዘው ትውልዱን በጥላቻ ቅስቀሳ አስክረው ለደም ማፍሠስ የሚያዘምቱ የቀን ጅብ ጭራቆች ገፋፊነት በአዲስ አበባ ዙሪያ በንጹሃን ወገኖቻችን ላይ ዘግናኝ ጭፍጨፋ ተፈጽሟል::
ይህን አይነት ድርጊት በዚህ ዘመን ያሳፍራል:: ከምዕራቡ ዓለም የስልጣኔና የነጻነት ሃገር ሄዶ ሽብርና ሁከትን ማስፉፉት ያስደነግጣል:: የነጻነት ሕይወት አጥቶ መከራውን ሲያይ በኖረ ሕዝብ ትከሻ ላይ ዝናና ስልጣንን ለማግኘት መሞከር ከፍ ያለ ዋጋም ያስከፍላል:: የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ወደ ዘሌቄታዊ የለውጥና የዲሞክራሲ ስርአት ለማሸጋገር መድከም ሲገባ ብጥብጥና ሁከት ማንገስ ለማናችንም የማይጠቅም ሃገር አፍራሽ ድርጊት ተቆጥቦ ሰላም እንዲሰፍን ሁሉም ወገን
ቆም ብሎ ሊይስብበት ይገባል::
የኦሮሞ ወንድሞቻችን በዘመነ ወያኔ አስከፊ መከራ ሲፈጽምባቸው ቆይቷል:: የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር (ሕወሃት) የኦሮሞን ሕዝብ እያሰረና እየገደለ በላዪ ላይ የሚፈልገውን እየሾመ ለ27 አመታት ያደረሰው መከራ ጠባሳው በግልጽ የሚታይ ነው:: እውነታው ይህ በመሆኑ ለ27 አመታት ጸንቶ የኖረውን የሕወሃት የባሪያ አሳዳሪ አገዛዝ ለመገርሰስ ላለፋት 3 አመታት የኦሮሞ ወጣቶች (ቄሮ) መራር ትግል በማድረግ ከሌሎች የኢትዮጵያ የትግል ሃይሎች ጋር በጣምራ አሁን የሚታየው ለውጥ መጥቷል::
በትግሬ ወያኔዎች አዝማችነት : የኦሮሞ ወጣት በየጥሻው እየተገደለ ጥፍሩ እየተነቀለና ብልቱ እየተኮላሸ የደረሰበት መከራ አንረሳውም:: እናት በልጇ አስከሬን ላይ የተቀመጠችበት ዜና በእግሩ ተራምዶ የገባው እግሩ ተቆርጦ የወጣው ሕያው ምስክር በሕይወት እያለ ጨለምተኞቹ አክቲቪስትና አንዳንድ መሪ ነን ባዮች ምዕተ ዓመት ያለፈውን የታሪክ መቃብር ሲቆፍሩና ከእኛ አልፎ የዓለም ጥቁር ሕዝቦች የነጻነት አርማ በሆነው ባንዲራ ላይ ሲዘባበቱ እናያለን::
ጠቅላይ ሚንስትር አብይ የብሄር ፖለቲካው ድንበሩን አልፎ ትልቁን የኦሮሞ ሕዝብ አሳነሰው ያሉት ከዚህ አንጻር ይመስለኛል:: ታሪክ የሰራው ቄሮ በሴረኞች ተጠልፎ በሽብር ስሙ እየጎደፈ ነው:: የለውጡ ሃዋርያ ቄሮ የቀልባሾችም ደቀመዝሙር እንዳይሆን የሚሰጋ ቢኖር አይፈረድበትም::  የኦሮሞ ልጆችን በገፍ ሲያድገድልና ደም ሲመጥ የኖረው ስብሃት ነጋ የኦነግ ወዳጅና ተቀባይ መስሎ መታየቱ ከጀርባው ሴራ ቢኖር ብሎ ቢጠረጠር አይገርምም::
የኦሮሞ ልሂቃንና ሽማግሌዎች ጥላቻና መለያየትን የሚሰብኩት የትግሉ መሪ ነን የሚሉትን የስደት ተመላሽ ወጠጤዎች አደብ ሊያስገዙና ሊመክሩ ይገባል:: ሁኔታዎች በዚህ ከቀጠሉ ለማንም የማይበጅ በሶሪያና በየመን የታዩትን ጥፉቶች የሚያስከትል ድባብ ውስጥ መሆናችን መዘንጋት የለበትም::
የሕዝባችን መብት እንዲረጋገጥ እኩልነትና ነጻነት እንዲሰፍን ባለፋት አመታት በኦሮሞ የፖለቲካ ሃይሎች ተፈጽሟል የሚባለውን ጥቃት ለታሪክ በመተው ነገን የተሻለ ለማድረግ አብረን ታግለናል:: በዚህም ብዙ የስም ማጥፋት ዘመቻም ደርሶብናል:: ነገር ግን አሁን የምናየው ሁኔታ እንዳይፈጠር በግዜ ለመመከ ብዙ ጥረት አድርገናል ::
 ከምርጫ 97 ጀምሮ በዶር መራራ መሪነት በህብረቱ ውስጥ ከኦብኮ ጋር ሰርቻለው :: በሗላም ከቀድሞው ኦነግ መስራቾች የአሁኑ ኦዴግ  ጋር በቅርብ አብሬ ተንቀሳቅሻለው:: በዚህ ሁሉ እንቅስቃሴ የተዋወኳቸው የኦሮሞ ፖለቲከኞች ብዙ ተምሬያለሁ ብዙም ወዳጆች አግኝቻለሁ :: ይህን የመሰል እድል በማግኘቴም የኦሮሞን ጉዳይ ከራሴ ጉዳይ ነጥዬ እንዳልመለከት አድርጎኛል::
ከኦሮሞ ወጣቶች ጋር አድገናል :: ለኔ በግሌ የቅርብ ጏደኞቼና ሚዜዎቼ ጭምር ኦሮሞዎች ናቸው:: በኦሮሞነታቸው የሚኮሩ : በኢትዮጵያዊነታቸው የሚደሰቱ የምኮራባቸው ወንድሞቼ ብዙ ናቸው:: በተለይ በተለይ መቼም የማልረሳው በቅርቡ የተለየን ውድ ወንድሜ ጏዴና መካሪዬ የምለው ምርጡ የአምቦ ልጅ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር አመራር ዘውዴ ጉደታን ልገልጽበት የምችልበት ቃል የለኝም::
ኦሮሞ አቃፊ የሆነ የጉዲፈቻ ምርጥ ባህል ያለው ማህበረሰብ እንጂ አንዳንድ አፍራሾች እንደሚያራግቡት የአግላይነት ልማድ የለውም:: የኦሮሞ የአማራውና የሌሎች ኢትዮጵያውያን ብሄሮች በመከባበር ላይ የተመሰረተ ስርዐት ከመገንባት ውጪ ምንም አይነት አማራጭ የለንም ::
 ይህ በመሆኑም ሰሞኑን የታየው አይነት ማንነትን መሰረት ያረገ ጥቃት መፈጸሙ ሁሉም ሊያወግዘው ይገባል::
ከስምንት አመታት በፊት የኦነጉ መሪ አቶ ዳውድ ኢብሳና ሌሎች እንደ ዶር በያን አሶባ ያሉ ከፍተኛ አመራሮቹ ባሉበት አንድ ውይይት አካሂደን ነበር::
በወቅቱ የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ሃይሎች ሕብረትን በምክትል ሊቀመንበርነት የማገለግል ስለነበር ሕብረት ከኦነግ ጋር የሚያደርገውን ግንኙነት በመምራት የተሳካና ሞቅ ያለ ወንድማማችነት የታየበት ውይይት አድርገን ነበር:: በዚያ ውይይት ላይ ትንሽ ስሜት በተጫነው ሁኔታ ኦነግ ከታሪክ እስረኛነት ተላቆ የኦሮሞንን ሕዝብ የሚመጥንና የጸረ ወያኔ ትግሉን የሚያጠናክር ሃላፊነትን እንዲወጣ ሃሰብ ሰንዝሬ ነበር:: አቶ ዳውድም በፈገግታ እናንተ ወጣቶች ያን ታደርጉታላችሁ የሚል እምነት አለኝ በማለት ሃሳቡን በበጎ ጎኑ ሲቀበል አስታውሳለሁ::
ከአመታት በሗላ ኦነግ ተሰንጥቆ በዛ ውይይት ከነበሩት ዶር በያን አሶባን ጨምሮ ጎምቱ የድርጅቱ መሪዎች ያሉበት የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር ተመስርቶ የኦሮሞ ልሂቃን በኢትዮጵያ የፖለቲካ ጠገግ ውስጥ ጉልህ ሚና እየያዙ የመጡበት ሁኔታተ :ፈጠረ:: በተለይ ኦዴግ በሃገራዊ ንቅናቄ መስራችነት የሃገራችንን የፖለቲካ ሃይሎች ትብብር እንዲጎላ ከፍ ያለ ሚና ተጫውቷል:: በተለይ የአማራና የኦሮሞ ፖለቲካዊ ፍጥጫ ረግቦ ሃገራዊ መግባባት እንዲኖር ላደረጉት በጎ አስተዋጽዖ በቅርብ አብረን የነበርነው እንመሰክራለን::
በአንድነት ሃይሉ የጠቅላይነት በሽታና ትግልን የመጥለፍ አባዜ በአማራ ስም ተደራጅተናል የሚሉ ታክቲክ አልባ ጠላት አብዢዎች የስሜት ወጀብ የተበከለው ፖለቲካችን : በተሳሳተ የጥላቻ ትርክት ተኮትኩቶ ያደገውን የኦሮሞ ወጣት ከተቀረቀረበት የሃሰት ማጥ አላቆ ከኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ጋር ለማሰለፍ የሚያስችል ስራ እንዳይሰራ እንቅፋት ሆነው ቆይተዋል::
ይህ ዛሬ የተከሰተው ግጭት እንዳይከሰት ብሎም ሕዝብ እንዳይጫረስ በትዕግስትና በእርጋታ መያዝ እንዳለበት የተረዱ የኦሮሞ ጎምቱ ፖለቲከኞች ከአማራውና ከሌሎች የብሄርና የአንድነት ሃይሎች ጋር የተቀናጀ ሃገራዊ መግባባትን እንዲኖር የሚያስችል ሁኔታን ለመፍጠር ብዙ ጥረት ተደርጏል:: በተለይ ይህ ሁኔታ ዘወትር የሚያሳስበው በቅርቡ የተለየን የኦዴግና የሃገራዊ ንቅናቄው ከፍተኛ አመራር የነበረው ታላቁ ሰው ወንድሜ ጟዴና ልባዊ ወዳጄ  ዘውዴ ጉደታ ከማለፉ ጥቂት ቀናት በፊት ይህንኑ ሁኔታ አንስቶ ያለውን ጥልቅ ስጋት ተወያይተን ነበር::
ይህ የባንዲራ (የድርጅት አርማ) ሁኔታን በቀና ሁኔታ ተቀብሎ በዲሞክራሲያዊ መንገድ ታሪክን ፖለቲካን እውነትን መሰረት ያደረገ የሰከነ ውይይት ለማድረግ ቅንነቱ ጠፍቶ ቆይቷል::
 በተለይ የኢትዮጵያ ሃገራዊ ንቅናቄ ሲፈጠር በባንዲራው(በድርጅት አርማው) ዙሪያ ሰፊ ውይይት እንደነበር አስታውሳለው:: በዛ ውይይት ዛሬ ለማጋደል የበቃው የኦነግ አርማና ድርጅቱን የፈጠሩት  እነ አቶ ሌንጮና ዶር ዲማ ነግዖ ሲያስረዱ ለረጅም ዘመን የቆየንና ብዙ ዋጋ የተከፈለበት የትግል አርማ ከማህበረሰቡ ጋር ቁርኝት ያለው በመሆኑ ሌላው ወገን ይህን በመረዳት
በትግዕስት እንዲይዘው እንደተናገሩ አስታውሳለሁ::
ይህ ዛሬ የተገኘው መረጋጋት ያስቆጫቸው : የአሮጌው ሰው በላ አገዛዝ ጭፍሮችና ጥቅማቸው የቀረባቸው ዘራፊዎች ቀውሱን ለማቀጣጠል አድብተዋል:: የዝና ስካርና የበታችነት ደዌ ያጠቃቸው ልፍስፍስና ምርኮኛ የስደት ፖለቲከኞች ከንቱ ፋክክር እየተገፋና በስሜት እየተነዳ ያለው ወጣት ከኪሳራ ውጪ ውጤት ለሌለው አላማ ሊያጨራርሱት ሃላፊነት የጎደለው ድርጊት ላይ ተጠምደዋል::
የወያኔ አረመኒያዊ አገዛዝ ከህዝብ ጫንቃ ላይ እንዲወገድ ላለፋት 27 አመታት ያልተቋረጠ ትግልና መስፈሪያ የለሽ መስዋዕትነት ተከፍሏል:: በረጅሙ አመታት ትግል የተዳከመው ቡድን በመጨረሻ  በተካሄደ የጎዳና አመጽ የተወገደ አድርጎ በመቁጠር የድሉ ባለቤት ለመሆን የሚደረገው አሳፋሪ የታሪክ ሽሚያ አቁሞ ጠሚ አብይ እንዳሉት የሕዝቡን መሰረታዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች ለመፍታት ብንሞክር የተሻለ ነው::
ሌላው የአዲስ አበባ ሕዝብ ሕልውና በእጃችን ነው የሚለው የልጆች ቅስቀሳና ለውጡን እኛ ነን ያመጣንው የሚለው መሰረት የለሽ ትምክህት ገደብ አድርጎ የተገኘውን የለውጥ ጭላጭል ወደ ሰፊ ብርሃን ለማሸጋገር ተደጋግፈን ብንቆም አትራፊ ያደርገናል::

Filed in: Amharic