>

ቆርጠው የማይጥሉት የበሰበሰ  ስጋ ጤና እየነሳን ነው!!! (ሉሉ ከበደ)

ቆርጠው የማይጥሉት የበሰበሰ  ስጋ ጤና እየነሳን ነው!!!
ሉሉ ከበደ
 የትግሬ ነጻ አውጭ ነን የሚሉት ዘረኞች ሀያ ሰባት አመት የዘሩት የዘረኝነት መርዝ እነሆ ማሰብ የማይችሉ ፤ ጭካኔያቸው ከአውሬ የማይተናነስ፤ ታዳጊ ወጣቶችን ለማፍራት ችሏል። በራሳቸው አምሳል የተፈጠረውን ሰብ አዊ ፍጡር  በጃቸው ገዝግዘው ማረድ የሚችሉ፤ በዱላ ቀጥቅጠው አሰቃይተው መግደል የሚችሉ፤ከገደሉም በኋላ ዘቅዝቀው መስቀል የሚችሉ አውሬ ነክ ታዳጊ ልጆችን ማፍራት ችለዋል።
በቅርቡ ጂጂጋ ውስጥ የተፈጸመው ዘግኛኝ እልቂት የተከናወነው  ፤ ባለፉት ሀያሰባት አመታት ውስጥ በተወለዱ ልጆች እጅ ነው። ሀዘኑ ከውጣችን ሳይወጣ እንደገና በቡራዩና በአሽዋ ሜዳ ደግመው አሳዩን። እነማን ናቸው እነዚህን ሮጠው ያልጠገቡ ህጻናት ለዚህ ጥፋት አሰልጥነው የሚያሰማሯቸው?
በመጀመሪያ ደረጃ ከአምስት ወራት ወዲህ እያየን ያለነውን የለውጥ ጭላልጭል፤  የሰላም ተስፋ ፤ አጥብቀው የሚጠሉት  ጨርሶ የማይፈልጉት፤ የኢትዮጵያን ህዝብ በሰላም በአንድነት መኖር የማይወዱት እነማን ናቸው? አቅማቸውስ ምንያህል ነው? የሚለውን ጥያቄ ሰው ሁሉ ራሱን ይጠይቅና ለራሱ መልስ ይስጥ። እኔም በበኩሌ የማስበው ነገር አለ።
የህውሀትን ሰዎች በተለይ እናስቀምጣቸው ። ምክንያቱም ዋናው የሃገሪቱ እና የህዝቡ ጠላቶች እነሱ ስለሆኑና ወደር የሌለው ሀብትም ዘርፈው የያዙ ስለሆነ፤ ለውጡም የመጣው በነሱ ላይ ስለሆነ  የዚያ ድርጅት መስራቾችና አንቀሳቃሾች ከኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ተወግደው ጥልቅ ጉርጓድ እስካልገቡ ድረስ እናም እነሱ የተሸከሙት ቫይረስ የዘር ፖለቲካ ከኢትዮጵያ ምድር ከስሩ ተነቅሎ አብሮ እስካልተቀበረ ድረስ ህዝቡ መበከሉና ሁሉም በሽተኛ መሆኑ  የማይቀር ነገር ነው።
የህውሀት ምኞት ምኞታቸው የሆነ፤ የህውሀት እድል እንዲገጥማቸው ሲታገሉ ኖረው ያልተሳካላቸው ፤ ግን በባህሪም በግብርም በጭካኔም አንድ አምሳል የሆኑ በውጭም ያሉ አሁን በተከፈተው የመቻቻል ፖለቲካ ሰበብ ተደምረናል እያሉ ተግተልትለው ወደ ሀገር የገቡት የህውሀት አምሳል ተውሳካት የኦሮሞ ጽንፈኞች ሰብእናቸው እንደ ወያኔ ከሰውነት የወረደ ግለሰቦች አምስት አይነት የኦሮሞ ድርጅት ሆነው ገብተዋል። የገቡት የለውጡ አንቀሳቃሽ ሀይሎች ይዘው የተነሱትን የቅን ፖለቲካ ፤ የኢትዮጵያ አንድነት ፤ የህዝብ ወንድማማችነትና አብሮነት ማርኳቸው ፤  የነዶክተር አብይንና የህዝቡን ራእይ እውን ለማድረግ ለመስራት ሳይሆን ፤ የኛ ነው የሚሉት ህዝብ መካከል ተገኝተው ያንን የማይድን በሽታቸውን የዘረኝነት የመበታተን ልክፍታቸውን  ሊያስፋፉ መሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። በቀላሉ ለመረዳት ጁሃር መሀመድ የተባለው የኦሮሞው መለስ ዜናዊ ሰሞኑን በቴሌቪዥናቸው የሚናገረውን ማድመጥ በቂ ነው።
አብዲ ኢሌ የጅጅጋውን ሰርቷል ከህውሀት ጋር። የቡራዩውን ጃዋር የለበትም ብሎ ማሰብ ጅልነት ነው።
ሌላው ሶስተኛው ወገን በባንዳነት ሲያገለግል የኖረው ነው። ሀያ ሰባት አመትታት ሙሉ ህውሀት እንደ በሬ ቀንበር ውስጥ አስገብቶ ፤ ሲያርስባቸው የቆዩ በኦህዲድ በአማራው እና በደቡብ ህዝቦች ድርጅት ውስጥ ተሰልፈው የነበሩና ያሉ ሰዎች በህውሀት ትንፋሽ ይወድቁ ይነሱ የነበሩ ግለሰቦች ናቸው። አሁን የተራገፉትም ሆነ እስካሁን ያልተነኩት  ለነሱ ደህንነትና ቀጣይነት ዋስትና የነበረው አሰራር የህውሀት የበላይነት ቢመለስላቸው የሚመኙ ናቸው። እናም የህዝቡን ሰላምና ደህንነት የሚያውክ ማናቸውንም ወንጀል ለማቀናበር የማይተባበሩበት የማይሰሩበት ምንም ምክንያት የለም።
ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዳይመጣ የሚፈልጉ የቅርብና የሩቅ ባእዳን እንደሚኖሩም ማወቅ ያስፈልጋል። የጽንፈኛ ኦሮሞዎች ሁለተኛው ቤት ካይሮ ነው።  ግብጽ ያባይን መገደብ በደስታ ተቀብሎታል? እርግጥ ይህን  ፕሮጀክት ህውሀት ከህዝቡ ገንዘብ ሊዘርፍበት ቢያቋቁመውም ፤ የማታ ማታ  ኢትዮጵያዊ መንግስት ሲፈጠር መገንባቱ አይቀርም። ያ እንዳይሆን መስራት የግብጽ ብሄራዊ ግዴታ ነው። ያንንም የሚያደርጉት ሀገር ውስጥ ካሉት ሽርካዎቻቸው ጋር በመደጋገፍ ነው። በስንቅም በትጥቅም ይረዳል ሰው።የወያኔ ሁለተኛ ቤት የሌባ ተቀባይ ቻይና ነው። ሌሎችም  መንግስታት እንደሚኖሩ መገመት ያስፈልጋል። ዜጎቻቸውን ኢትዮጵያ ውስጥ አስፍረው የኢትዮጵያዊነትን መብት እስከመንጠቅ የደረሱ ባእዳን ረጅም እጅ ያለው ጠባቂ መንግስት አላቸው። ሀገራችን ውስጥ በህዝብ ፍቃድ የሚንቀሳቀስ መንግስት የተቋቋመ ቀን የዜጎቹን መብት ለማስከበር ሲል ከወያኔ ጋር የጥቅም ጡት የተጣቡ ባእዳን ብዙ እንደሚያጡ ግልጽ ነው። ያ እንዳይሆን ከወያኔ ጋር መስራት ያስፈልጋል። በኦጋዴን የነዳጅ ድፍድፍ መኖሩ ተረጋግጧል። ይህ ነዳጅ መውጣት ቢጀምርና የገበያ ሽሚያ ውስጥ ብንገባ የመካከለኛው ምስራቅ ጎረቤቶቻችን ይወዱታል?  ስለዚህ ያልተረጋጋች ኢትዮጵያን መፍጠር የብዙ ወገኖች የቤት ስራ ሊሆን እንደሚችል አትጠራጠሩ።
ኢትዮጵያ እንዳትረጋጋ ይህ ለውጥ እንዳይሰምር ከውስጥም ከውጭም አምርረን የምንታገላቸው ሀይሎች መኖራቸውን ኢትዮጵያዊ ሁሉ ማወቅ አለበት። ለዚያም ሁለንተናዊ ትግል መዘጋጀት ያስፈልጋል። አንድነታችንን ማጠንከር።
መንግስት የልምምጥና የቸልታ አቋሙን ማስወገድ አለበት። የህግ ተቋማትን ማጠናከር። የፖሊስና የደህንነት ሀይሎችን ማጠናከር። መከላከያ ሰራዊቱን ማጥራት መቀጠልና ማጠናከር። እርግጥ ከመከላከያ ሰራዊቱ የሚወገዱት የህውሀት ሰዎች የትግራይን ክልል የጦር ክፍል ገብተው የማጠናከር ስራ እንደሚቀጥሉ ቢታወቅም ብቻ ከብሄራዊ ጦር ውስጥ ይቀነሱ። በተረፈ ህዝቡ አሁንም በሙሉ ልብ ከዶክተር አብይ ጎን መቆሙን እንዲቀጥል  እመክራለሁ።
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
Filed in: Amharic