>

ቡራዩ፥ ቄሮ እና ጃዋር!   (ብስራት ወልደሚካኤል)

ቡራዩ፥ ቄሮ እና ጃዋር! 
 ብስራት ወልደሚካኤል
ለጠሚ አብይ አህምድ እና ለማ መገርሳ አሁንም ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል። እውነት ለመናገር እንደ ሀገር ኢትዮጵያን ከመምራት በስራቸው ያለውን ኢህአዴግን እና ለስልጣን ያሰፈሰፉ ተቀናቃኝ የ “ኦሮሞ” ፖለቲካ ልሂቃንን መምራት ዋነኛ ፈተናቸው ሊሆን ይችላል። ከዚህ ቀደም በክፋታቸው የረገምናቸው ህወሓቶች ላይ ብቻ ጣት ስንቀስር ባልተጠበቀ መንገድ ሌላ የለውጡ አደናቃፊ ከ”ቤተሰብ” መሀል ብቅ ማለቱን ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ. ም. መስቀል አደባባይ በዶ/ር አብይ ላይ የተሞከረውን ጥቃት ጠንሳሽ፥ አስተባባሪ፥ ተባባሪና ፈፃሚ እነማን እንደሆኑ ሲታወቅ ነገሮችን በብዙ አቅጣጫ እንድንመለከት ዕድል ሰጥቶናል። ስለዚህ ወደሌላው ላይ ብቻ ጣት መቀሰር አያዋጣም።
#Jawar_Mohammed የቡራዩን ብሔር ተኮር ጥቃት እንደተለመደው የህወሓት ፖለቲካ ነገሩን ወደሌላ ሶስተኛ ወገን ለመቀሰር መሞከሩ ትክክል አመስለኝም። ማንን ለማታለል?  ርግጥ ነው፤ የተፈፀመው ጥቃት ኦሮሞንም ሆነ ማንኛውንም ማኅበረሰብ ሊወክል አይችልም በሚለው እስማማለሁ። አሁን ባለው በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የብዙሃን ቅቡልነት እንጂ ህዝባዊ ውክልና ያለው የለምና። ምናልባት የጥቃት አድራሾቹ የቄሮ ተወካይ አይደሉም ሊባል ይችል ይሆናል፤ ነገር ግን የቄሮ አባላት አይደሉም ብሎ መደምደምና መሸፋፈን ይቻላል? አንድን ህቡዕ መዋቅር በህግና አስተዳድር ወይም ደንብ ያላደራጀኽውን እና በህግ የማትቆጣጠረውን አካል ሁሉ እንዴት ንፁህ ማድረግ ይቻላል? ቄሮስ የመላዕክት ስብስብ ነውን? (ነገሩ ከመላዕክትም መካከል ሳጥናኤልን ጨምሮ የተሳሳቱ ነገደ መላዕክት እንደነበሩ ልብ ይሏል)።
ጥሩ ነገር ሲሆን ቄሮ ነው፤ ጥፋት ሲሆን ደግሞ ሌላ …. የሚለው ትርክት አይሰራም። ኋላ ማጣፊያ እንዳይቸግር ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል። በወንጀሉ የተሳተፉ በህግ ይጠየቁ አንድ ነገር ነው፤ ጨፍኑ ላሞኛችሁ በሚል ቄሮን ከነ ሳጥናኤል በኋላ ያለ የነገደ መላዕክት ስብስብ አስመስሎ ፍፁም ነፃ ለማድረግ መሞከር ለሌላ ጥፋትም ሊጋብዝ ይችላልና ሰከን ብሎ ማየቱ ይሻላል።
ሀገራችንን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት የፖለቲካ ታሪክና ልምድ እንደሚነግረን ከሆነ ዛሬ የሰቀልከው ነገር ነገ ማውረድ እንደሚቸግርና መጨረሻም የእንቅስቃሴው ዋነኛ አካል፥ መሪዎችና ጋላቢዎችንም ጠርጎ ይዞ እንደሚሄድ ራሱን የፖለቲካ “ሳይንቲስት” ብሎ ለሚጠራ ሰው የሚጠፋው አይመስለኝም። እንኳን በህግና ስርዓት ያልተደራጀ አካል ቀርቶ በህግ አግባብ የተመሰረተም ቢሆን ሁሉም ንፁህ ሊሆን አይችልም።
ጥቃት ከመድረሱ በፊት #Tsegaye_Ararssa ጉራጌና ስልጤ ማኅበረሰብ ላይ፥ #Ayele_Degaga ጋሞ/ዶርዜ ማኅበረሰብ ላይ ያውም በራሳቸው ይፋዊ ማኀበራዊ ገፅ ላይ ሳይቀር በግልፅ የጥላቻና የዘረኝነት ጥቃት ቅስቀሳ ሲያደርጉ ነበር።  ሁለቱም ግለሰቦች ቅስቀሳውን ባደረጉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ነው ጥቃቱ የተፈፀመው። ሁለቱም የዘረኝነትና ጥላቻ ቅስቀሳ ያደረጉ ግለሰቦች መካከል አየለ ደጋጋ በድጋፍ መልክ፥  ፀጋዬ አራርሳ በቀጥታ #OMN  ላይ ተሳታፊ በመሆ  ከጃዋር መሐመድ ጋር በቅርብ የሚሰሩ ናቸው። ስለዚህ እነኚህ ሁለት ግለሰቦች ቅስቀሳ ያደረጉት አንድን “ወንጀለኛ”  ግለሰብ ለህግ እንዲቀርብ ሳይሆን፤ ኃፊነት በጎደለው መልኩ ጥቅል ማኅበረሰብን ስም በመጥራት ነበር የጥላቻ ቅስቀሳ ያደረጉት። እና እነኚህን ግለሰቦችስ ሚና  ጀዋር ወዴት አድርጎ ነው ዙሪያ ጥምጥም የሚሄደው?  እና የነኚህ ግለሰቦች ዓላማ እና ከእነዚህ ጀርባ ያለው ማን ነው? ለምን በይፋ የዘረኝነት ቅስቀሳ አደረጉ?
ሌላው ጥቃቱ ከደረሰባቸውና የጥቃቱ ሰለባ የተደረጉ ማኅበረሰብ መኖሪያ መካከል በተለይ ቡራዩ አሸዋ ሜዳ ዶ/ር መረራ ጉዲናን ጨምሮ የተለያዩ የመድረክ መሪዎች መኖሪያ ስፍራ ነው። በዕለቱ ጥቃት የደረሰበት የምዕራብ ሸዋ ተወላጅ የሆነ እና የአካባቢው ነዋሪ የሆነ የኦሮሞ ተወላጅ በአቅራቢያው ያለውን ጩኽትና የመንጋ ጥቃት ሰምቶ ከግቢው ዘሎ ሲወጣ እሱም የጥቃቱ ሰለባ ሆኖ ጳውሎስ ሆስፒታል ህክምና ርዳታ እየተደረገለት ሲሆን፤ በሁኔታው ግራ መጋባቱን ተናግሯል። የጥቃት አድራሾቹ የተደራጁና በኦሮሚኛ እየፎከሩና እየዛቱ ጥቃት መፈፀማቸውን፥ የአንዳንዶቹ የኦሮሚኛ አነጋገር ዘይቤ ጠንከር ያለና እሱ ከሚያውቀው ከቡራዩና  አካባቢው ኦሮሚኛ እንደሚለይ መታዘቡን ተናግሯል ( ተጎጂው እሱ ላይ ጥቃት ከፈፀሙት ውስጥ ቃል የተመላለሱትና የዛቱበት የየት አካባቢ ኦሮሚኛ ቋንቋ አነጋገር ዘይቤ እንደሆነ ቢናገርም እዚህ መግለፁ አስፈላጊ ስላልሆነ ነው)። ይሁን እንጂ በድርጊታቸው በመበሳጨት ሊያናግራቸውና ሊያረጋጋቸው ቢሞክርም፤ ጥቃት አድራሾቹም ” አንተ ማነህ?  ምን ልታደርግ መጣህ? ምን አገባህ? … ” በሚልና ሌላም ፀያፍ የኦሮሚኛ ቃል በመጠቀም እሱንም ደብድበው ጥለውት እንደሄዱ ተናግሯል።
በዋነኝነት ጥቃት አድራሾቹ የጋሞ፥ የጉራጌና ስልጤ ማኀበረሰብ ላይ ማነጣጠራቸው ነው የተነገረው። የጥቃቱ ምክንያት ግን እስካሁን አልታወቀም። በጥቃቱም ከ4 ዓመት ህፃን እስከ የ4 ልጆች እናት መደፈርን ጨምሮ እስካሁን ከ40 ያላነሱ  ሰላማዊ ዜጎች ተገድለዋል፥ በርካቶች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፥ በሺህዎች የሚቆጠሩ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። በተለይ ጥቃት የደረሰባችው የዓይን እማኞች እንደሚሉት ከሆነ ድርጊቱ የተፈፀመው በተደራጀ መልኩ መሆኑን ነው። የተፈፀመውን ጥቃት በማውገዝም በአዲስ አበባ የተቃውሞ ሰልፍ ተደርጓል። ሰልፉን ተከትሎም በፀጥታ ኃይል በተወሰደ የኃይል ርምጃ የ5 ሰላማዊ ዜጎች ህይወት አልፏል፥ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ በርካቶች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል።  ይህም ሌላ ተጨማሪ ጥፋት ሲሆን፤ በዶ/ር አብይ አስተዳደር የመጀመሪያ የኃይል ርምጃ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።
እንደ አካባቢው መረጃዎች ከሆነ ጥቃቱ ከመፈፀሙ ሁለት ሳምንት ጀምሮ ተደጋጋሚ ብሔር ተኮር ትንኮሳ እንደነበርና ጉዳዩም  ለፖሊስም ሪፖርት ተደርጎ እንደነበር ተሰምቷል። ታዲያ ከዚህ ጥቃት ጀርባ ማን ነው ያለው?  ለፍቶ አዳሪዎቹ ለምን እና እንዴት የጥቃቱ ዋነኛ ሰለባ ተደረጉ?
የዶ/ር አብይ እና የአቶ ለማ አስተዳደር የህግ የበላይነት ላይ ጠንከር ያለ ርምጃ እንዲወስዱ በተደጋጋሚ ግፊት ቢደረግባቸውም አደጋው አፍንጫቸው ስር እያንዣበበ ይመስላል። ዶ/ር አብይ እና አቶ ለማ ያላቸውን ህዝባዊ ቅቡልነት ተጠቅመው የህግ የበላይነትን ማስጠበቅ ካልቻሉ የሀገሪቱ የፀጥታ ሁኔታ ከቁጥጥር ውጭ ሊወጣ ይችላል። ስለዚህ በአሁን ሰዓት እነ ዶ/ር አብይ ከመቼውም ጊዜ በላይ የህዝብ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ይመስለኛል። ሌሎቻችን ግን ነገሮች ከቁጥጥር ውጭ እንዲወጡና ለሌላ ተጨማሪ እልቂት የሚጋብዙ ንግግሮችን፥ ምስልና ቪዲዮ ማጋራትን ብናቆም መልካም ነው። እነ ጠሚ አብይ  እንደተለመደው እሹሩሩ በሚል  ከወዲሁ የህግ የበላይነትን ማስከበር ካልቻሉ በዙሪያቸው እያንዣበበ ያለው ነገር ለሀገሪቷም ለራሳቸውም መዘዝ ይዞ ሊመጣ ስለሚችል መንቃት እለባቸው።
Filed in: Amharic