>
5:28 pm - Sunday October 10, 9424

ጀዋር አሜሪካ እና ኢትዮጵያ  (ናሆም ዳኜ)

ጀዋር አሜሪካ እና ኢትዮጵያ
ናሆም ዳኜ
ጀዋርን Oromo First. Ethiopia out of Oromia በሚለው እና በሜጫ እንላቸዋለን በሚሉት ሶስት ንግግሮቹ ብዙዎች ሲተቹት አውቃለሁ። ጀዋር ቄሮን በመምራት የወያኔ አንባገነን ስርዓትን በመደርመስ ትልቅ ሚና ተጫውቷል። OMN በማቋቋም እና የኦሮሞ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ እኩልነት ትግል መሬት ማስነካት የቻለ ወጣት ወደፊትም ለኢትዮጵያ ጥሩ ተስፋ ሊሆን የሚችል ነው። ነገርግን አገር ቤት ከሄደ ጀምሮ እያስተላለፈ ያለው ትዕቢት የተሞላበት መልዕክት እና በተደጋጋሚ ያለውን ስርዓት እመክራለሁ እገስፃለሁ በሚል የሚያደርገው የዶክተር አብይን መንግስት ማንኳሰስ ስታዘብ ብቆይም ትላንት ለ OMN የሰጠው ቃለመጠይቅ አገሪቱን በእውነተኛ ዲሞክራሲ ላይ ለመገንባት ፍላጎት እንደሌለው አስገንዝቦኛል። ራሱን በማመፃደቅ የተለያየ ስም ሲሰጥ የቆየው ጀዋር ወያኔዎች ሰሞኑን በሰጡት ፌደራሊስት ስም ተሞካሽቶ ዛሬም የኦሮሞን ህዝብ ድል በሰሜኑ ፖለቲከኞች ወጥመድ ውስጥ እየከተተው ነው።
ብዙ ጉራጌዎች የሚደግፉት ይህ የእኩልነት ትግል ግብ መምታት የሚችለው ኦሮሞን በዜጋ ደረጃ ፍላጎቱን ማሟላት ስትችል ቢሆንም ቄሮን ደምሮ በእጁ ላይ ያለ ዕቃ ማድረጉ ሳያንሰው ራሱን ዳግም እንደ ሌንጮ ሊጫወቱበት የተዘጋጁትን ማየት አለመቻሉ እና ጭብጨባ አስክሮት ይህን ትነኳትና ወዮላችሁ ወደሚል አደገኛ አቅጣጫ በመሄድ ላይ በመሆኑ ከወጣትነቱ በተሻለ የኢትዮጵያን ጉዳይ ማየት ባለመቻሉ ምክንያት ዛሬ ጀዋር ዴሞክራሲን ሳይሆን መከራን ሊያመጣ እንደሚችል  ተረድቻለሁ።
አሁንም ዜጎች በኦነግ እና ወያኔ የተጫነብንን ህገመንግስት በድምፃችን የማንፈልገውን አውጥተን እንድንሄድ መድረኩ እንዲመቻችልን መጠየቅ በተለይ ከምርጫ በኋላ ደማችንን እንዳይጠጡት የሚያደርግ በመሆኑ ተጠንቅቀን ማየት አለብን።
ጀዋር የኦሮሞ ትግል ጥያቄ ሲመለስ የሙስሊሙም ጥያቄ ይመለሳል ብሎን ነበር። እሱ የወጣበት አካባቢም ዘጠና ዘጠኝ በመቶ ሙስሊም እንደሆነ ነግሮናል። ይህ ጥሩ ነው ነገር ግን እንዴት ነው በአንድ ፌደራል ክልል ይህን ማስተናገድ የሚችለው? ጀዋር ከዚህ በኋላ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ተስፋ እንዲሆን ዜግነትን የሚያስቀድም እውነተኛ ፌደራሊዝም እንዲመጣ መስራት አለበት። አሁንም ጀዋር ማወቅ ያለበት የኢትዮጵያ አንድነት ምርጫ የሌለው መሆኑ ብቻ ሳይሆን ወደፊትም ይህ የአንድ ኦሮሞ ፌደራል ስርዓት የሚያጫርስ መሆኑን ነው።
Filed in: Amharic