>
5:14 pm - Thursday April 20, 9284

ዳግማዊ ምኒልክና  ዳግማዊ አባ ጅፋር በጅማ!!! (አቻምየለህ ታምሩ)

ዳግማዊ ምኒልክና  ዳግማዊ አባ ጅፋር በጅማ!!!
አቻምየለህ ታምሩ
ኦሕዴድ ዘጠነኛ ድርጅታዊ ጉባኤውን በጅማ እያካሄደ ይገኛል። ይህን ተከትሎ ኦሕዴድን ጨምሮ የእሕት፣ የአጋርና የተፎካካሪ ድርጅቶች ወኪሎች ነን ያሉ ግለሰቦች ወደ መድረክ እየወጡ ለታዳሚውና በቴሌቭዥን ለሚከታተለው «ምዕመን»  መልዕክት እያስተላለፉ ነበር። ከተላለፉት መልዕክቶች መካከል «በታላቁ በአባ ጅፋር ከተማ በጅማ»  የኦሕዴድን ጉባኤ ለመሳተፍ በመታደላቸው መደሰታቸውን የገለጹበትና  « በምኒልክ ተወረን ስንጨቆን ኖረን ነጻ ወጣን»  እያሉ ራሳቸው  «ከተጨቆኑት ወገን»  ያደረጉ  ካድሬዎች  የተናገሩት ዲስኩር  ትኩረቴን ሳበውና አንድናንድ ነገር ማለት ፈለግሁ።
ዳግማዊ አባ ጅፋር  በምስራቅ አፍሪካ ወደር የማይገኝለት ባሪያ ነጋዴ ነበሩ። በነገራችን ላይ በተለምዶ  አባ ጅፋር የምንላቸው ዳግማዊ አባ ጅፋር ናቸው።  አያታቸው ቀዳማዊ  አባ ጅፋር  የጅማን ንጉሣዊ  መንግሥት የመሰረቱት ናቸው።  ዳግማዊ አባ ጅፋርን በ1904 ዓ.ም. በሚኖሩበት ጅማ  ሄዶ የጎበኛቸው ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ተክለ ማርያም አባ ጅፋር «ከአንድ ሚሊዮን በላይ የአካባቢውን ሕዝብ በባርነት ሽጦ እንደጨረሰው»  ኦቶባዮግራፊ [የሕይወቴ ታሪክ] በሚል ባዘጋጀው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ አስፍሯል።
በ1916 ዓ.ም. ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት[League of Nations] አባል ለመሆን  ባመለከተችበት ወቅት በእንግሊዝ  መንግሥት ከፍተኛ ተቃውሞ ቀርቦባት ነበር። የኢትዮጵያን መንግሥት  የአባልነት ማመልከቻ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት [League of Nations]  ለማስገባት  ወደ ጀኔቫ የተላከው ቡድን መሪ የነበሩት  ራስ ናደው አባ ወሎ በፈረስ ስማቸው «አባ መብረቅ» እንግሊዝ  ኢትዮጵያ የመንግሥታቱ ማኅበር አባል እንዳትሆን የተቃወመችበትን ምክንያት ለንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ በላኩት የቴሌግራም መልዕክት ላይ እንዲህ ሲሉ አስረድተዋል፤
«እንግሊዝ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሐን የዘገቡትንና በሱዳን፣ በኬንያ፣ በኤደንና በግብጽ ባሉት የቅኝ ግዛት መንግሥቱ በኩል የሰበሰበውን ማስረጃ በማያያዝ በደቡብ ኢትዮጵያ እየተካሄደ ስለነበረው የባርያ ንግድ ሁኔታ፤ በተለይም የጂማው አባጅፋር በከፋ፣ በማጂ፣ በጊሚራና በጉራፈርዳ ሕዝብ ላይ እየካሄዱት ያለው መጠነ ሰፊ የባሪያ ንግድ ለማኅበሩ የፖለቲካ ኮሚሲዮንና ለጠቅላላ ጉባኤ  በማቅረብ አባል እንዳንሆን ከፍተኛ ተቃውሞ አቅርቦብናል»
ለዚህ ለራስ ናደው አባ ወሎ ቴሌግራም የአልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን መንግሥት አፋጣኝ ምላሽ ሰጠ። ኢትዮጵያ ውስጥ በአባ ጅፋር አማካኝነት  የሚካሄደው የባርያ ንግድ ባጭር ጊዜ ውስጥ ጨርሶ እንዲታገድና የሰው ልጅ መብት በመላው የአገሪቱ ግዛት እንዲከበር የአልጋወራሽ ተፈሪ መንግሥት ለመንግሥታቱ ማኅበር ቃል በመግባት ኢትዮጵያ ያቀረበችው የአባልነት ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ ከመስከረም 17 ቀን 1916 ዓ.ም. ጀምሮ ኢትዮጵያ የመንግስታቱ ማህበር 57ኛ አባል ሆና መመዝገቧ በይፋ ታወጀላት።
አባ ጅፋር ጅማን ያስፋፉት በአካባቢው የነበሩ እንደ የምና ጌራ አይነት ነገዶችን  በመውረርና በማጥፋት የተረፈውን  ሕዝብ ደግሞ ባሪያ  አድርገው በመሸጥ ነበር። አባ ጅፋር ባሪያ አድርገው የሸጡት ኦሮሞን  ጭምር ነበር።  ዳግማዊ ዐጤ ምኒልክ  አባ ጅፋር ሰውን ባሪያ እያሉ እንዳይሸቱ በተደጋጋሚ ትዕዛዝና ማስጠንቀቂያ ከዚያም እስከካሰር ድረስ ደርሰው ነበር።  ከዚህ በተጨማሪም  ዳግማዊ አባ ጅፋር  ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ በ1881 ዓ.ም.  ኩሎና  ኮንታን፤  በ1886 ዓ.ም.  ወላይታንና  በ1889  ዓ.ም. ካፋን  ወደ ማዕከላዊ መንግሥት አስተዳደር መልሰው ባስገቡ ጊዜ አባ ጅፋር የዘመቻው ቀዳሚ ተካፋይ ነበሩ።
ከአንድ ሚሊዮን በላይ የጅማን አካባቢ ሕዝብ  ባሪያ አድርገው የሸጡትና  የምስራቅ አፍሪካው ታላቁ የባሪያ ነጋዴ አባ ጅፋር ናቸው እንግዲህ ዛሬ በጅማው የኦሕዴድ መድረክ  «ታላቁ አባ ጅፋር» ተብለው ተንቆለጳጵሰው አባ ጅፋር የባሪያ ንግድ እንዲያቆሙ ያደረጓቸውንና በባርነት ሰንሰለት አስረዋቸው የነበሩት  የአካባቢውን ነገዶች ከባርነት ነጻ  እንዲሆኑ ያደረጉትን  ዳግማዊ ዐጤ ምኒልክ ደግሞ  ጨቋኝ  አድርገው  የሚያወገዙት። አባጅ ጅፋር «ታላቅ» ተብለው የባሪያ ንግዳቸውን እንዲያቆሙና በባርነት ሰንሰለት ያሰሯቸውንም ነገዶች ነጻ እንዲለቁ ያደረጉት ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ  «ጭራቅ» ተደርገው ሊቀርቡ የሚችሉት በዘረኞች ሚዛን ብቻ ነው። ከዚህ ውጭ ባለ መስፈርት  አባ ጅፋር «ታላቅ» ተብለው  የባሪያ ንግዳቸውን ያስቆሟቸውና በሰንሰለት የያዟቸውንም ነጻ እንዲለቁ ያደረጓቸው ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ግን  «ጭራቅ» ሊሆኑ አይችሉም!
ከታች የታተመው የዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ደብዳቤ አባ ጅፋር ኦሮሞን ባሪያ አድርገው ሲሸጡ ኦሮሞን ባሪያ አድርገው መሸጣቸውን እንዲያቆሙ የጻፉት ደብዳቤ ነው።  ዳግማዊ ምኒልክ ወደ አባ ጅፋር የላኩት ደብድዳቤ «ይድረስ ካባ ጅፋር» ብሎ ይጀምራል።  የዘመኑ ደብዳቤ እንዲህ ነበር የሚጻፈው።  በዚያ ዘመን አማርኛ  «ይድረስ ካባ ጅፋር»  ማለት በዛሬ  ዘመን አማርኛ «ይድረስ ለአባ ጅፋር» እንደ  ማለት ነው። ይህ የዐፄ ምኒልክ ደብዳቤ በጽሕፈት መኪና ተገልብጦ  ጳውሎስ ⶉⶉ «ዐጤ ምኒልክ» በሚል በጻፉት  መጽሐፍ ገጽ 32 ላይ ይገኛል።
ታላቁን የምስራቅ አፍሪካ የባሪያ ካፒታሊስት  አባ ጅፋርን «ታላቁ አባ ጅፋር» እያሉ   ዐፄ ምኒልክን ግን «ጭራቅ» አድርገው ዛሬ ላይ  እያወገዙ የሚገኙት አንዳንድ አክራሪ ብሔርተኞች  ከታች በታተመው  የዐፄ ምኒልክ ደብዳቤ በአባ ጅፋር ባሪያ ተደርገው  ከመሸጥ የተረፉ አያቶችና ቅድመ አያቶች የልጅ ልጆች ናቸው!
ደብዳቤውን የጳውሎስ ኞኞ «ዐፄ ምኒልክ» መጽሐፍ  ገጽ 32  ላይ ታገኙታላችሁ 
ይሄንንም ማድመጥ ይቻላል:-
https://www.youtube.com/watch?v=IZkHuwnqmV4
Filed in: Amharic