>

‘’ሥራህን ሥራ ! ’’ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ  (በዲያቆን ዳንኤል ክብረት)

‘’ሥራህን ሥራ ! ’’ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ
 ዲያቆን ዳንኤል ክብረት
 ኢትዮጵያን ከነፍሳቸው በላይ የሚወዷት ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ ዛሬ በሕይወት ኖረው ዶክተር ዐቢይን እንዲህ ሲያዝን ቢያዩት ኖሮ ከሠላሳ ዓመታት በፊት ያስተማሩትን ይህን ጠንካራ መልእክት ይልኩለት ነበር፡፡ 
 
~ እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ ሰው ሥራ ሰጥቶታል፣ ያንን መሥራት የእሱ ፈንታ ነው፡፡ ቢቻለው እሱን ማገድ የዲያቢሎስ ሥራ ነው፡፡ በእርግጥ ሥራው እግዚአብሔር እንደሰጠህ ያህል ሰይጣን ሊያግድህ ይጥራል፡፡ ሌላ ነገር በበለጠ ደስ የሚያሰኝ ሊያቀርብልህ ይጥራል፡፡ በዓለማዊ ተስፋዎች ያባብልሃል፡፡የሐሜት ጐርፍ ያስወርድብሃል፡፡
ደራስያን እንዲጠይቁህ እጅግ ስመ ጥር ሰዎችም በክፉ እንዲናገሩብህ ይጠቀምባቸዋል፡፡ ጲላጦስ፣ ሄሮድስ፣
ሐናንያ፣ ቀያፋ ሁሉም በአንተ ላይ ያድማሉ፡፡ ይሁዳም በአጠገብህ ቆሞ በሠላሳ ብር ሊሸጥህ ይከጅላል፡፡ ይሄ ሁሉ የደረሰብህ ሰይጣን በዚህ ከሥራህ ሊስብህና እግዚአብሔርን ከመታዘዝ ሊያሰናክልህ መሆኑን ልትገነዘብ አትችልምን? አንተ ግን ሥራህን ሥራ!
አንበሳው ሲያጓራ ፍንክች አትበል፣ የሰይጣንን ውሻዎች ለመውገር አትቁም፡፡ ጥንቸሎቹንም በማባረር ጊዜህን አታጥፋ፡፡ ሥራህን ሥራ! ዋሾች ይዋሹ፣ ጠበኞች ይጣሉ፣ ማኀበሮችም ይወስኑ፣ ደራሲዎችም ይድረሱ፣ ሰይጣንም የፈለገውን ያድርግ፣ አንተ ግን ምንም ነገር እግዚአብሔር የሰጠህን ሥራ ከመፈጸም እንዳያግድህ ተጠንቀቅ፡፡
ገንዘብ እንድታተርፍ አልተላክም፣ እንድትበለጽግም አልታዘዝክም፣ ለክብርህ ተከላከል ብሎ አልነገረህም፣ ሰይጣንና አገልጋዮቹ የሚነዙትን የሐሰት ወሬ እንድታስተባብል አልተጠየቅክም፣ እነዚህን ሁሉ ነገሮች ብታደርግ ሌላ ሥራ ልትሰራ አትችልም፣ ይህም ብቻ ሳይሆን ለራስህ እንጂ ለእግዚአብሔር አልሠራህም፡፡
ዓላማህ እንደ ኮከብ የጸና ይሁን ፤ ተወው ዓለም እንደፈለገው ይነታረክ፣ ይጨቃጨቅ፣ ጥቃት ይደርስብህ ትበደል፣ ትሰደብ፣ ትታማ፣ ትቆስልና፣ ትናቅ ይሆናል፡፡ ኃይለኛ ያጐሳቁልህ፣ ወዳጆች ይተውህ፣ ሰዎችም ይንቁህ ይሆናል፡፡
አንተ ግን በጸና ውሳኔ የማያወላውል ቅናት በመጨረሻ ላይ ጸንተህ፣ የሰጠኸኝን ሥራ ፈጸምኩ ሃይማኖትንም ጠበቅሁ ለማለት እስክትችል ድረስ የሕይወትህን ዓላማ እና የተፈጠርክበትን ግብ ተከተል!
ሥራህን ሥራ!
Filed in: Amharic