>

የኦህዴድ የሱሪ ለውጥ!!! (ሀይለገብርኤል አያሌው)

የኦህዴድ የሱሪ ለውጥ!!!
ሀይለገብርኤል አያሌው
ሕወሃት ወያኔ እንደ ጭቃ አቡክቶ እንደ ብረት ቀጥቅጦ የፈጠረው ኦህዴድ የተሰፋለትን ጥብቆ  አውልቆ የራሱን ሱሪ መታጠቁ ይበል የሚያሰኝ ነው:: ብአዴንና ደህዴግም የሕወሃትን ውራጅ ጥብቆ ጥለው የራሳቸው ሱሪ ባለቤት እንደሚሆኑ እንጠብቃለን::
ኦህዴድ በሕወሃት ዘንድ የተናቀ የምርኮኛና ተንበርካኪ የከተማ ምስለኔዎች ተሞልቶ በወያኔ ሳንባ እየተነፈሰ ሁለት አስዕርተ አመታት ጸጥ ለጥ ብሎ አገልግሏል:: ይህ የዘመናት የባርነት ሰንሰለት ተበጥሶ ነጻነት ይመጣ ዘንድ የኦሮሞ ወጣቶች (ቄሮ) ወደር የለሽ መስዋዕትነት ከፍሏል:: የኦሮሞ ሕዝብ መከራ የከበዳቸው የድርጅቱ አመራሮች የቲም ለማ ተከታዮች ለውጡ መሬት የቆነጠጠና ተራማጅ በማድረግ ታሪካዊ አሻራቸውን አስቀምጠዋል:: የለማና አብይ ቡድን ከብአዴን ጋር ተቀናጅተው የተስፋ ጎህ እንዲፈነጥቅና የለውጥ ሁኔታዎችን በተግባር በማሳየት መላው ኢትዮጵያውያንን ከጎናቸው ማንቀሳቀስና ማሰለፍ ችለዋል::
የትላንቱ ልፍስፍና ተላላኪው ኦህዴድ ይህው ዛሬ አብይን የመሰለ ዘመን ተሻጋሪ አስተሳሰብ ያለው ሃገራዊ መሪና ለአፍሪካ ተስፋ የሆነ አስተዋይ አፍልቆ ታሪክ ለማስመዝገብ በቅቷል:: ሌላም የኦሮሚያ ክልል ፕሬዜዳንት ለማ መገርሳ የተወዳጅነቱ አድማስ ከሚመራው ክልል የራቀ ከመተማ እስከ ጋንቤላ የሚያስተጋባ ሆኖል::
ኦህዴድ ሕወሃት የሰየመለትን ስም ትቶ የራሴ የሚለውን ስም ማውጣቱ ለድርጅቱና ለሚወክለው ማህበረሰብ ክብርም ታሪክም ለውጥም ነው::
ኦሮሞ የኢትዮጵያ ማዕዘን ነው የምንለውም ለዚህ ነው:: በአድዋ በማይጨው በኦጋዴና በኤርትራ የተዋደቀው የኦሮሞ ጀግና ለእናት ሃገሩ ነጻነት ነው:: ይህን መሳይ ጀግኖች የሚፈልቁበት የኦሮሞ ሕዝብ በስሙ እየተነሱ የሚነግዱትን ሕዝብን ከህዝብ የሚያጋጩትን ጠባቦች የጠላት ተላላኪ ተንበርካኪ ሎሌዎችና ምርኮኞች በስሙ እንዳይነግዱ ሊታገላቸው ይገባል::
መላው ሕዝባችን መራራ መስዋዕትነት ከፍሎ ያስገኘውን የለውጥ ሂደት ለመቀልበስ የሚሯሯጡት ጸረ ሕዝቦች በንቃት በመከታተል ከለውጡ መሪዎች ጎን በመቆም በሃገራችን የሰላም አየር እንዲሰፍን በጋራ መቆም ይኖርብናል::
Filed in: Amharic