>
5:01 pm - Tuesday December 3, 4047

ለታላቅ ወንድማችን ታማኘ በየነ፣ (ኤርሚያስ ለገሰ ዋቅጅራ)

ለታላቅ ወንድማችን ታማኘ በየነ፣
ኤርሚያስ ለገሰ ዋቅጅራ
 ኪሱ ሁሌም ቀዳዳ ነው። ያሳዝነኛል። ለነገሩ በእሱ ውስጥ አተኩሬ የማያት ኢትዮጵያም ታሳዝነኛለች። ርግጥም የኢትዮጵያን ጉዳይ በኢትዮጵያዊነት ስሜት ውስጥ ሆኖ እንደማየትና ማሰላሰል ህሊና የሚያቆስል ነገር የለም።”
ብዙ ጊዜ አንተን በአደባባይ ማመስገን ” ለራስ ሲቆርሱ…” ይሆንብናል በማለት የሆዳችን በሆዳችን እንይዛለን። አለፍ ካለም እኛ የኢሳት ቤተሰቦች እርስ በራስ አውርተን የጋን መብራት እናደርገዋለን።
ዛሬ ግን በፍፁም አልቻልኩም። አረፋፈዱ ላይ የዜና ዝግጅት ክፍላችን ያዘጋጀውን ዜና ሶስት ጊዜ ለማስተካከል መገደዱን ነገረን። የመጀመሪያው ዜና ” በአርቲስት ታማኝ በየነ የቀረበውን ጥሪ ተከትሎ በአለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት በተከፈተ የጐ ፈንድ ሚ የገንዘብ ማሰባሰብ ዘመቻ ለቡራዮ ተፈናቃዮች በ6 ሰአት ውስጥ ብቻ 20ሺህ ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ተሰበሰበ” የሚል ነበር። ሁለተኛው ዜና በ12 ሰአት ውስጥ ከ130ሺህ በላይ ተሰበሰበ በሚል ተቀየረ። ሶስተኛው ዜና በ24 ሰአት ውስጥ 250ሺህ ዶላር ደረሰ ወደሚል ተቀየረ። አሁን ዜናው ተሰርቶ ከተነበበ በኃላ 260ሺህ ዶላር ደርሷል። ገና ይቀጥላል። የሚገርም ነው።
እናም ታማኝ ዘር ቀለም ሳትለይ በኢትዮጵያዊነት ይሄን በማድረግህ እናመሰግንሃለን። እንደ ትላንቱ እንኮራብሃለን። በግሎባል አሊያንስ ውስጥ አብረው የሚሰሩ ባልደረቦችህንም ከልባችን እናመሰግናለን። የኢትዮጵያዊ ክብራችን መግለጫዎች በመሆናችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እንፈልጋለን።
ታላቅ ወንድማችን ታማኝ! በዚህች አጭር ጊዜ የተሰበሰበው ገንዘብ ከችግራችን ስፋት አንፃር ሊሸፍን የሚችለው ከኩሬ ውስጥ በጭልፋ መዝገን ያህል ሊሆን ይችላል። ነገር ግን አንድምታውን ስንመለከተው በጣም ብዙ ነው። እስቲ በአንድ ድንጋይ ቢያንስ ሶስት ወፎችን እንደመታህ ላንሳ፣
#አንድ: -በኢትዮጵያውያን ዘንድ ሲነርጂ እንዲፈጠር ያደርጋል። “አዎንታዊ መደመር” በኢትዮጵያውያን ዘንድ መተማመን እንዲፈጠር በር ይከፍታል። ሲነርጂው የሚፈጥረው ጉልበት በቸልተኝነት እዳር ቆመው የነበሩትን ወደ ” አዎንታዊ መደመር” ጐትቶ ያስገባቸዋል። ያገባኛል የሚል ስሜት ይፈጥራል።
ሁለት:- በቀጣይ ማህበራዊ ንቅናቄ ለመፍጠር መደላድል ይሆናል። ለምሳሌ አልባሳት፣ መጫሚያ፣ የትምህርት መሳሪያዎች የማሰባሰብ ዘመቻ ለመክፈት መነሻ ሆኖ ያገለግላል።
#ሶስት: – መንግስት ያጋጠመውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለማቃለል የሚያደርገውን ጥረት ያግዛል። ይህም በመንግስት ውስጥ ያለውን የለውጥ አራማጅ ተስፋ እንዲሰንቅ ያደርጋል። ይህም ለለውጡ የበለጠ ተነሳሽነት እንዲኖራቸው ያደርጋል። እርግጥም ድልድዩን የሚገነቡ ኢትዮጵያዊያን ከጐናቸው መሰለፋቸውን ያረጋግጣሉ።
ወንድም ታማኝ! ደጋግሜ እንደተናገርኩት እና እንደከተብኩት እንዲህ አይነት ታላላቅ ተግባራት ሊፈፀሙ የሚችሉት ልዩ ችሎታ ባላቸው ጥቂት ሰዎች ብቻ ነው። …ልዩ ችሎታው ዘር፣ ቀለም፣ ሐይማኖት፣ ፓለቲካ፣ ጾታ፣ እድሜ ሳይለዩ ከመላ ኢትዮጵያውያን ጐን የመሰለፍ ተቀባይነት ማግኘት መቻል ነው። …ልዩ ችሎታው ሁለንተናዊ እይታ ይዞ የዛፎቹ ሲነርጂ ጫካውን እንደፈጠረ፣ ጫካው ያለ ዛፋ…ዛፋ ያለጫካው እንደማይኖር አውቆ መንቀሳቀሱ ነው። …ልዩ ችሎታው ራስን ሆኖ መገኘት ነው። …ልዩ ችሎታው አገናኝ እና የኔታ ሆኖ መራሩን ሀቅ ለመጋፈጥ የአቋም ሰው መሆን ነው።…
ልዩ ችሎታው ሰብአዊ መሆን ነው። ” ጥላሁን ያረፈ ቀን” የሚለው መጽሐፍ ገፅ 270 እንዲህ ይላል፣
  ” የዚህ ማስታወሻ ፀሀፊና ባልደረቦቹ ከታማኝ በየነ ጋር በነበረን ማህበራዊ ህይወት ሩህሩህነቱና ሰው ወዳድነቱን ተመልክተናል። ጨዋታ በጋራ ሒሳብ በግል የሕይወት መመሪያ በሆነባት አገረ አሜሪካ ታማኝ በየነ ጋር ሲደረስ አይሰራም። አንገቱ ይቆረጣል እንጂ ማንም ታዳሚ የራሱ ኪስ እንዲገባ እድል አይሰጥም። ኪሱ ሁሌም ቀዳዳ ነው። ያሳዝነኛል። ለነገሩ በእሱ ውስጥ አተኩሬ የማያት ኢትዮጵያም ታሳዝነኛለች። ርግጥም የኢትዮጵያን ጉዳይ በኢትዮጵያዊነት ስሜት ውስጥ ሆኖ እንደማየትና ማሰላሰል ህሊና የሚያቆስል ነገር የለም።”
Filed in: Amharic