>
5:13 pm - Wednesday April 19, 9719

አቶ ታዬ ትዕቢት የሰነፎች ጊዜያዊ ጉልበት ነው! (መሳይ መኮንን)

አቶ ታዬ ትዕቢት የሰነፎች ጊዜያዊ ጉልበት ነው!
መሳይ መኮንን
 
ከተቀመጡበት ወንበር እኩልነትን እንጠብቃለን። ከጨበጡት ሃላፊነት ሚዛናዊ ፍርድ እንሻለን። ተራ ብሽሽቅ ውስጥ ተነክረው፡ የቃላት ጦርነት ላይ መጠመዳቸውን ያቁሙት። ቢያንስ ለወንበራቸው ክብር ዘብ ይሁኑ!
 
ለተቀመጡበት ወንበር የሚመጥን ምላሽ ከመስጠት ይልቅ የብሽሽቅ ፖለቲካ ውስጥ ተነክረዋል። እልህ ሲተናነቃቸው ፌስቡክ ከፍተው እንዳለ እንደወረደ ይዘረግፉታል። ትላንት የረገሙትን ወገንተኝነት ዛሬ እሳቸው ያቀነቅኑት ጀምረዋል። ትላንት የተጠየፉትን ኢፍትሀዊነት ቋንቋ ሳይቀይሩ እንዳለ ገልብጠው እያሳዩን ነው። ጊዜው የእኛ ነው በሚሉ የብሄር አቀንቃኞች ዜማ መደነስን መርጠዋል። ማዳላት አይበጅም እያሉ በማዳላት ተጠምደዋል። እሻጥርን እያወገዙ በአሻጥር የተንቆጠቆጠ የፖለቲካ መስመር ላይ ሽምጥ እየጋለቡ ነው። በግማሽ መላጣ ሆነው ጎፈሬውን እያብጠለጠሉት ነው። ‘ህገወጥነት’ ብለው የሚከሱትን አካል በህገወጥ መስመር ለማረም ወገባቸውን ታጥቀው ተነስተዋል። ይህን ሁሉ የሚያደርጉት የመንግስትን ትልቁን ሃላፊነት ተሸክመው ነው። ያውም ፍትህን በእኩልነት ያሰፍናል ተብሎ በሚጠበቅ የሃላፊነት ወንበር ላይ ተቀምጠው።
አቶ ታዬ በዚሁ መቀጠል የሚገባቸው አይመስለኝም። ስሜታቸውን መቆጣጠር ካቃታቸው፡ ነጻ ግለሰብ ሆነው እንደፈለጋቸው ሀሳባቸውን የሚያስተላልፉበትን፡ አቋማቸውን የሚያንጸባርቁበትን፡ ወገኔ ለሚሉት አካል የሚቆሙለትን ሌላ መንገድና ቦታ ቢፈልጉ ለእሳቸውም፡ ለጤናቸውም፡ ለድርጅታቸውም፡ ለመንግስታቸውም የሚበጅ ይሆናል። ከተቀመጡበት ወንበር እኩልነትን እንጠብቃለን። ከጨበጡት ሃላፊነት ሚዛናዊ ፍርድ እንሻለን። ተራ ብሽሽቅ ውስጥ ተነክረው፡ የቃላት ጦርነት ላይ መጠመዳቸውን ያቁሙት። ቢያንስ ለወንበራቸው ክብር ዘብ ይሁኑ።
አንድ ተጨማሪ ወንድማዊ ምክር። እንዲህ እልህ ሲተናንቅዎት ከፌስ ቡክ አከባቢ ይራቁ። ሰውነትዎን ላላ አድርገው፡ ቀዝቃዛ ውሃ ፈልገው ትንሽ ጎንጨት ይበሉ። እርስዎ ዘንድ ያለው አይበገሬነት ሌላውም ጋር መኖሩን እንደማይዘነጉ ተስፋ አደርጋለሁ። የጊዜ እንጂ የሰው ጀግና የለም። ጊዜው የእኛ ነው የሚለው ጋርዮሻዊ አስተሳሰብ ብዙ ርቀት አይወስድም። የህወሀት ባለሟሎች የትዕቢት ተራራ እንዴት እንደተናደ ከእርስዎ የተሰወረ አይመስለኝም። ትዕቢት የሰነፎች ጊዜያዊ ጉልበት ነው።
ቤተመንግስት የሚገኘው የለውጥ ሃይል በከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ደረጃ የሚተላለፉ መልዕክቶች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ያደርግ ዘንድ ይጠበቃል። ዜጎችን በእኩል አይን መመልከት የሚገባቸው የመንግስት ሃላፊዎች ደምና አጥንት እየቆጠሩ ፍርድ የሚሰጡ ከሆነ ውጤቱ ለሁላችንም አይበጅም። የህወሀት መሪዎችም እኮ ኢትዮጵያውያን ናቸው። ያወገዝናቸው፡ የታገልናቸው፡ እኩል ስለማያዩን ነበር። ውድቀታቸውን በጸሎትና በእልህ አስጨራሽ ትግል እንዲመጣ የናፈቅነው እኮ የበላይና የበታች መሆንን ተጠይፈን፡ አንገሽግሾን ነው።
ስሜታቸውን በማይቆጣጠሩ፡ ከሀሳብ ይልቅ ዘርና ብሄር እየጠሩ የሚሰብኩ፡ የሚፈርዱ መሪዎችን አደብ ማስገዛት የመንግስት ሃላፊነት ነው።
ለግንዛቤ እንዲረዳው አቶታዬ በገጻቸው ይህንን ነው ያሰፈሩት
 
ስለ አዲስ አበባ ወጣት አሻጥር አይሰራም!
ታዬ ደንደአ
ተጠርጣሪን ይዞ መመርመር ደግሞ ያለ እና የሚኖር  ህጋዊ ህደት ነዉ። ማንም ቢሆን ያለወንጀሉ መታሰር የለበትም። ወንጀል የፈፀመ ደግሞ ቲፎዞ ቢኖረዉም ባይኖረዉም በህግ አግባብ ይጠየቃል!!!
መስከረም መጀመሪያ ላይ በአዲስ አበባ ችግር መፈጠሩ ይታወሳል። በዝያ ችግር ምክንያት የሰላማዊ ሰዉ ህይወት ጠፍቷል። በንብረት ላይም ጉዳት ደርሷል። ሁኔታዉ ከቁጥጥር በላይ ሆኖ የበለጠ አደጋ እንዳይከሰት እና ጥፋተኞቹን ለህግ ለማቅረብ ሲባል ፖሊስ የጠረጠራቸዉን ሰዎች ይዟል። አሁን ነገሩ ተጣርቶ አብዘኞቹ የሚለቀቁ ሲሆን የቀሩት ለህግ ይቀርባሉ። በቅርብ ቀን ሁሉም መስመሩን ይይዛል። ይህ መረጃ በዉስጥ መስመር የደረሳቸዉ ሰዎች ደግሞ  “አስፈታናችሁ” ለማለት የFB ዘመቻ ከፍቷል። “ፍትህ ለአዲስ አበባ ወጣት” የሚለዉ ዘመቻ ታሳሪዎቹን ለማስፈታት ሳይሆን ለሚቀጥለዉ የፖለቲካ ንግድ ግበአት መሰብሰብ ላይ ያተኮረ አሻጥር ነዉ።
ፍትህ ለሁሉም ዜጋ መሆን አለበት። በዝህ ላይ ግልፅ መሆን ያስፈልጋል። ማዳላት ያስተዛዝባል። ለታሰረዉ ስንከራከር የተገደለዉን እና አካለ ጎዶሎ የተደረገዉን ወገን መዘንጋት የለብንም። ከአዲስ አበባ ስለተያዙ ሰዎች ስናወራ ከቡራዩ ስለታሰሩት ወጣቶችም ማሰብ አለብን። በምስራቅ እና በምዕራብ ከቤት ንብረታቸዉ ተፈናቅለዉ በችግር ላይ ያሉ ዜጎችም ፍትህ ይፈልጋሉ። ተጠርጣሪን ይዞ መመርመር ደግሞ ያለ እና የሚኖር  ህጋዊ ህደት ነዉ። ማንም ቢሆን ያለወንጀሉ መታሰር የለበትም። ወንጀል የፈፀመ ደግሞ ቲፎዞ ቢኖረዉም ባይኖረዉም በህግ አግባብ ይጠየቃል። ግማሽ ተላጭቶ ግማሽ ማጎፈር አይቻልም። የተሟላ አስተሳሰብ ያስፈልጋል! በተዛባ ሚዛን አንጠቀም!
ለማንኛዉም ፍትህ ለፖለቲካ ንግድ አይዉልም!ፖለቲካችንን ከአሻጥር እናፅዳዉ። ያ ካልሆነ በስተቀር ወደፊት መሄድ አይቻልም። ሁሉም ተንኮሎች አርጅቷል!
ፖለቲካዉ ገብቶናል!
Filed in: Amharic