>
5:13 pm - Thursday April 19, 1708

ሃገሬን ሊያጠፉ ቆርጠው ተነስተዋል!!! (ያሬድ ጥበቡ)

ሃገሬን ሊያጠፉ ቆርጠው ተነስተዋል!!!
ያሬድ ጥበቡ በድምጽ ያቀረበው
የገብረክርስቶስ ደስታን ዛሬ ቅዳሜ ኖቬምበር 26 ቀን 2016 አም የፕሮፌሰር ፀጋዬ አራርሳን “ኢትዮጵያዊነት የሚባል ማንነት የለም” የሚለውን ከ SBS ሬዲዮ ጋር ያደረገውን ቃለምልልስ ከሰማሁ በኋላና አርቲስት እይዩ ፈንገስ ያነበበውን “ሃገሬ” የተሰኘውን የገብረክርስቶስ ደስታን ግጥም ካደመጥኩ በኋላ የተሰማኝ ስሜት፣
ኢትዮጵያዬ
የኢትዮጵያዬ ጭንቋ
ግፍ አለማወቋ   ,
እንደ ሌሎች ህዝቦች፣ አለመጨፍለቋ
አለማዋሃዷ፣ አለመለንቀጧ
አንድ አለማድርጓ
በሆደ ሰፊነት ልዩነት ማክበሯ
ነው ያገሬ ታሪክ፣ ነው ያገሬ ክብሯ።
ሆኖም በዚህ ቻይነቷ የተመነደጉ
የከበዱ ያደጉ
ክብሯን ሊያሳንሱ
ታሪኳን ሊያጎድፉ
ሰንደቋን ሊያወርዱ
መዝሙሯን ሊፍቁ
ተነሰተው ቆመዋል
ይሄው ይፎክራሉ
ድምፃቸው ይሰማል
ሃገሬን ሊያጠፉ ቆርጠው ተነስተዋል።
አይሆንም እላለሁ
ኢትዮጵያ አትጠፋም ብዬ እዘምራለሁ።
ኢትዪጵያ ምንድን ናት ለሚለው ጥያቄ፣
ሃገር ናት ይሉኛል
መንግስት ናት ይሉኛል፣
ሃገሬ የፓስፖርት ሰነድ ናት ይሉኛል፣
ማንነት የሌላት፣
ካለም የተለየች፣
ሆደሰፊነቷ ምንም ያደረጋት
የአብሮነት እምነቷ ማንነት ያሳጣት
የቻይነት ብሂሏ ራሷን ያጠፋት
የማይሞትላት፣ የማይሰየፉላት
የማይራራላት፣ የማይዋደቁላት
ማንነት የሌላት፣ ምንነት የሌላት
ፈርሳ ምትሰራ፣ የሸክላ አፈር ናት
ብለው ይዘምራሉ ።
በግፍ በተሰራ ዜግነት ስር ቆመው፣
አቦሪጂን ሰልቅጦ
ቀይ ህንድ አላምጦ
ነጭ ባረገ ሃገር፣ ደመና ስር ቆመው
ያፍሪካን ጥቁርነት የወሰነችውን
ያቺን ኢትዮጵያዬን
ይወነጅሏታል፣
ስሟን ያጠፏታል፣
ማንነት የሌላት ብኩን ያደርጓታል።
እንደ ሸክላ ሰብረው፣
አድቅቀው አለንቁጠው፣
እንደ አዲስ ሊሰሯት ይመካከራሉ
አቦ፣ አይሆንም በሏቸው
እረፉ በሏቸው
የገረሱን ሃገር፣
የአቢቹን ምድር
የጃጋማን አፈር፣
የአበበ ቢቂላን፣
የጥላሁን ገሰሰን፣
የደራርቱ ቱሉን
የታላቁን ወታደር የአበበ ገመዳን
የጄኔራሎቹ ዋነኛውን ቁንጮ፣ የሙሉጌታ ቡሊን፣
ጀግናው ቀነኒሳ በደረቱ ይዞ የመረሸላትን፣
እንዴት ቢደፍሩ ነው?
ማንነት የሌላት ወድቃ ምትሰበር የሸክላ አፈር ናት
ብለው የሚያረዱን።
ለምን?
በበቀል፣ በሃይል ስላልጨፈለቀች?
በህገመንግስቷ “ያንተ ዜግነትህ፣
ሲሶ ነው፣ ሩብ ነው” ስላልደነገገች?
ወይስ እንደ ቀዩ ህንድ
በክልል አጥር ውስጥ፣ አስራ ስላልያዘች?
ከቶ ምን አጠፋች?
ምንስ ተገኘባት?
ከአለም አስለይቶ ባይተዋር ያረጋት
ማንነት የላትም የተፈከረባት
ከቶ ለምን፣ ለምን?
Filed in: Amharic