>
10:42 pm - Tuesday July 5, 2022

ኢትዮጵያ 13 ህዳሴ ግድብ የሚሰራ ገንዘብ ተዘርፋለች!!! (ሸገር ኤፍ ኤም 102.1)

ኢትዮጵያ 13 ህዳሴ ግድብ የሚሰራ ገንዘብ ተዘርፋለች!!!
ሸገር ኤፍ ኤም 102.1
ኢትዮጵያ በ27 አመት ውስጥ 36 ቢሊዮን ዶላር ወይም አንድ ትሪሊዮን 80 ቢሊዮን ብር ገደማ የሚገመት ሀብት ሸሽቶባታል፡፡
ይህ የገንዘብ አቅም ወይም የሀብት አቅም በ80 ቢሊዮን ብር ሂሳብ 13 የህዳሴ ግድቦችን ለመገንባት የምችል የገንዘብ መጠን ነው፡፡
በተደጋጋሚ የውጭ ምንዛሪ ከጓዳዋ የሚጎልባት፣ ከተሰበሰበውም የሚመነተፍባት ኢትዮጵያ በተለያየ ጊዜ በግፍ እና በተጋነነ ዋጋ ሀብቷ ከሀገር ሸሽቷል፡፡ ለአንድ ሀገር ጤናማ ኢኮኖሚ መኖርም የውጭ ምንዛሪን ማስተዳደር እና መቆጣጠር እንደ ዋና ስራ ይቆጠራል፡፡
ነገር ግን ቸልታው እየበዛ ቁጥጥሩም እየላላ በመቀጠሉ ይዞ የመጣውን ችግር አፍጥጦ እያየነው ነው፡፡
ተህቦ ንጉሴ ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ ሀብቷ በምን መንገድ ሲሸሽ ቆይቷል ? ይዞ የመጣውስ ችግር ምንድን ነው? ሲል የኢኮኖሚክስ ባለሙያ ጠይቋል፡፡

https://www.facebook.com/Sheger102.1/videos/338896093367732/

አንድ ትሪሊየንማ  እንኳን ተዘረፍን  መቁጠሩም እዳ ነው!!
አሌክስ አብርሃም
በዛ ወጥቶ ብዚህ ወርዶ ሳልል አንድ ትሪሊየን ስለሚባለው ቁጥር አንዳንድ ነገሮችን እንድናገር ይፈቀድልኝ ? አመሰግናለሁ !
ወገኖቸ ይሄ  ትሪሊየን የሚባለው ቁጥር  ከቁጥር ቅዠትነት አልፎ ስጋ ለብሶ ምድር ላይ ከምድርም የኛይቱ የጉድ ምድር ላይ  ይከሰታል የሚል ህልም ሒሳብ አስተማሪ እንኳን የሚያልም አይመስለኝም!! (ሚስኪንየ አስራ ሁለት ዜሮ ያስከተለች አንድ ቁጥር በቾክ ሰሌዳ ላየ ጽፎ መገላገል እያለ ምን አሳሰበው በዛች ደመወዝ ስለትሪሊየን ላውራ ቢል እንዳንፖል ጧ በሎ ሰሌዳው ስር ኩርምት ነው የሚልብን )
እንግዲህ አገራችን ባለፉት ሩብ ምዕተ ዓመታት ይሄን የሚያክል ብር ወደውጭ አጉርፋለች ነው እየተባለ ያለው! ከምር ግን በትክክል ገብቷችኋል? ትሪሊየን እንደው መጠኑ አይምሯችሁ ውስጥ ስእሉ እንዴት ነው የሚታያችሁ? የሆነ አራት ትላልቅ ሻንጣ ሙሉ ብር ? ወይስ የጤፍ ጆንያ  ኩንታል ሙሉ ? አስር ኩንታል? እሽ ሃያ ኩንታል? አይ በቃ አምሳ ኩንታል ሙሉ ብር?ለዛኮነው በጭራሽ ልታስቡት አትችሉም ያልኳችሁ ! እኔ ራሱ አሁን አይደል እንዴ <<አንድ ትርሊየን >> ብሎ የማያርፍ ጣቴ ጎግል ላይ ጽፎ ጎግል <<ለምን ፈለከው >> አለኝ አገሬ ትሪሊየን የሚባል ነገር ተሰርቃለች ተብሏልና  መጠኑን ለማወቅ ነው አልኩ !  ጎግል << አቡቹ አገርህ አንድ ትሪሊየን ከተዘረፈች  በቁሟ ሙታለች ሬሳህን አንሳ ፣ ይሄን ሁሉ ተዘርፋ እንዳገር ከቆመች ደግሞ  ፈጣሪ በአካል ተገልጦ በተአምር ያቆማት አገር ብለህ ለመመስከር ማይክሮፎን አንሳ >> !! የሚል መልስ ሰጠኝ ካላመናችሁ እናተም ጎግልን ጠይቁት !
ኮንቴነር ታውቃላችሁ ? ይሄ በመርከብ እቃ የሚጫንበት ? በርና መስኮት ተቀዶለትና ለሶስት ተከፋፍሎ ሁለት ሱቅና አንድ ጸጉር ቤት  የሚሆነው ረዥሙ ኮንቴነር አወቃችሁት? ባታውቁት ይሻል ነበር ! አንድ ትሪሊየን ብር ማለት እንግዲህ  አስራ አንድ  ኮንቴነር ሙሉ  ታጭቆ ማለት ነው አሉ !! ቆይ አሁንም በደንብ አልገባችሁም ጓዶች በሌላ ምሳሌ ጎግል እንዳስረዳኝ ላስረዳችሁ
ለምሳሌ በዚች ምድር ላይ 80 ዓመት ትኖራላችሁ እንበል እና በሰማኒያ ዓመት የመጨረሻው ጵዋግሜ ላይ የአንድ ትሪሊየን ብር ባለቤት ለመሆን ከፈለጋችሁ ገና ከተወለዳችሁባት ቀን ጀምሮ በየቀኑ  እደግመዋለሁ በየቀኑ ወደባንክ ወላ ወደሆነ ጣና ሃይቅን ወደሚያክል ጉድጓድ እየሄዳችሁ  34 ሚሊየን ብር ለክፉ ቀን ብላችሁ ማስቀመጥ  ወላ መከዘን ይኖርባችኋል !
ቆይ ! ብቻየን ተቃጥየማ በሰላም አትሄዷትም! ለምሳሌ የወር ደመወዛችሁ 40 ሺህ ብር ነው እንበልn(ግዴለም ለዛሬ ይሁን) አንድ ትሪሊየን ብር እንዲኖራችሁ ደመወዛችሁን አምስት ሳትነኩ ስንት አመት መቆጠብ እንዳለባችሁ ታውቃላችሁ? እድሜ ይስጠን እንጅ ቀላል ነው 25 ሚሊየን ዓመት ብቻ !!
እንደው የሆነው ሁኖ ብሩን አገኘነው እንበል እና አንድ ሺህ አንድ ሺሁን በላስቲክ አስረን ወደላይ ብንከምረው ምን ያህል ሽቅብ እንደሚረዝም  ገምቱ? አንድ መቶ ኪሎሜትር !! አገራችን የተዘረፈችው ትሪሊየን የሚባለው ነገር በትንሹ ይሄ ነው !! እኔ የምለው ጓዶች እንደው እንኳን ብር የድፍን አዲስ አባባ ቆሻሻ ከያለበት ተጠርጎ ቢከመር ይሄን ያክል ይሆናል? ይሄን ክስ ይዘን ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ተዘረፍን ብለን ብንቆም ዳኛው እንዲህ የሚሉ አይመስላችሁም<< እናተ ኢትዮጲያዊያን ይሄ የክስ ፋይል ሳይሆን ቅዠት ነው ከእንቅልፋችሁ እስከምትነቁ ፍርድ ቤቱ  የአንድ አመት የጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል ጓ!! ኽረ ጓ !
Filed in: Amharic