>

ተከሳሾች ላይ ሽንት በመሽናት፣ ጥፍር በመንቀል የተጠረጠረችው ዋና ሳጅን እቴነሽ አረፉዓይኔ 11 ክሶች ተመሠረቱባት!!! (ታምሩ ጽጌ)

ተከሳሾች ላይ ሽንት በመሽናት፣ ጥፍር በመንቀል የተጠረጠረችው ዋና ሳጅን እቴነሽ አረፉዓይኔ 11 ክሶች ተመሠረቱባት!!!

ታምሩ ጽጌ

በሽብር ወንጀል ተፈርጀው ታስረው በነበሩ የኦነግና አርበኞች ግንቦት ሰባት አባላት ላይ ሽንት በመሽናት፣ ጥፍር በመንቀልና በሌሎችም ዘግናኝ የተባሉ የወንጀል ድርጊቶች ተጠርጥራ የታሰረችው፣ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ የቀድሞ አባል ዋና ሳጅን እቴነሽ አረፉዓይኔ 11 ክሶች ተመሠረቱባት፡፡

ተከሳሿ በተለምዶ ማዕከላዊ ይባል የነበረውና በቅርቡ በተዘጋው የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ የምርመራ ቡድን መሪና መርማሪ ሆና ስትሠራ፣ ካልተያዙ ግብረ አበሮቿ ጋር በመሆን በሽብር ተግባር ወንጀል ተፈርጀው በታሰሩ ዜጎች ላይ ፈጽማለች የተባለችውን የወንጀል ድርጊት፣ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያቀረበው ክስ ያስረዳል፡፡

ተከሳሿ ተመስገን ፀጋዬ፣ ወርቁ ፈረደ፣ ዘመነ ምሕረት፣ ሀብታሙ ሚልኬሳ፣ ዳንኤል እንየው፣ ጌትነት አማረ፣ አንሙት ታምሩ፣ ሽመልሽ አድማሴና ሌሎች ተጠርጥረው የታሰሩ ግለሰቦች ላይ የመመርመር ሥልጣን ሳይኖራት፣ ሌሊት በመጥራት ማሰቃየቷን፣ በሐሰት የእምነት ቃል እንዲሰጡና ሳያነቡ እንዲፈርሙ፣ ያልተያዘ ኤግዚቢት ላይ እንዲፈርሙ ስታስገድድና ስታስፈርም እንደነበር ክሱ ይገልጻል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ምንም ዓይነት ድርጊት እንዳልፈጸሙ ምላሽ ሲሰጧት፣ በማስመሪያ ፊታቸውን እንደመታቻቸው፣ በአፍንጫቸው እስክርቢቶ በማስገባትና ለረዥም ጊዜ እጃቸውን አሥራ በማንጠልጠልና ራቁታቸውን በጠባብ ክፍል ውስጥ ታስቀምጣቸው እንደነበር በክሱ ተገልጿል፡፡ ፂማቸውንና የብብታቸውን ፀጉር ፒንሳ በሚመስል ነገር  በመንቀል ራሳቸውን ስተው ሲወድቁ ውኃ በመድፋትና ‹‹ገና አፍህ ላይ እሸናብሃለሁ›› በማለት፣ ፊታቸው ላይ ሽንቷን መሽናቷንና ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸሟን ክሱ ያብራራል፡፡

‹‹የግንቦት ሰባት አርበኞች አባል ነን›› ብለው እንዲያምኑ ሱሪያቸውን በማስወለቅና የውስጥ ሱሪያቸውን በአፋቸው ውስጥ በመጠቅጠቅ፣ ብልታቸውን በማስመሪያ ትመታቸው እንደነበርም አክሏል፡፡ ተጠርጣሪዎቹን ከባድ ስፖርት በማሠራትና በመደብደብ፣ እንዲሁም ሁለት እጆቻቸውን በካቴና በማሰርና በግንብ ላይ በተሰካ ብረት ላይ በማንጠልጠልና በኤሌክትሪክ ገመድ በመግረፍ ቃላቸውን እንደተቀበለቻቸውም ክሱ ያስረዳል፡፡

ታሳሪዎቹን በጠረጴዛ ላይ በማስተኛት፣ በጥፊ በመምታት፣ ላያቸው ላይ ሽንቷን በመሽናት፣ የቪዲዮ ማስረጃ፣ መጻሕፍትና የኦነግ ዓርማ ከእነሱ እጅ የተገኘ መሆኑን አምነው እንዲፈርሙ ታስገድዳቸው እንደነበር ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡ በስቴፕለር መምቻ ጭንቅላታቸውን በመምታትና ጎናቸውንም በመርገጥ ታሰቃያቸው እንደነበርም አክሏል፡፡

መርማሪዎቹ በጋራ በመሆን የታሳሪዎቹን እጆች በማሰርና በእጃቸው መሀል እንጨት በመክተት ገልብጠው በማቆየት፣ ውስጥ እግራቸውን በኤሌክትሪክ ገመድ እንደገረፏቸውና እንዳሰሯቸው ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቁሟል፡፡ ተከሳሿ ተጠርጣሪዎቹን በኤሌክትሪክ ገመድ ከመግረፏም በተጨማሪ፣ በብረት ጉጠት የአውራ ጣታቸውን ጥፍር መንቀሏንም ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቁሟል፡፡

በጠረጴዛ መካከል በማስገባት መዘቅዘቅ፣ ሽንቷን በሰውነታቸው ላይ መሽናት፣ በብልታቸው ላይ ውኃ  በማንጠልጠል የሰብዓዊ መብጥ ጥሰት ስትፈጽም እንደነበር ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡ በአጠቃላይ ተካሳሿ ሥልጣኗን ያላግባብ በመገልገል በዋና ወንጀል አድራጊነት በፈጸመችው የማይገባ አሠራር መጠቀም ወንጀል መከሰሷን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡  

Filed in: Amharic