>

እስክንድር ነጋ ትንቢቶች አንድ በአንድ እየተፈጸሙ ነው!!! (ዘመድኩን በቀለ)

እስክንድር ነጋ ትንቢቶች አንድ በአንድ እየተፈጸሙ ነው!!!
ዘመድኩን በቀለ
• ዐማራን በተመለከተ የተናገረው – ተፈጽሟል!
• አማርኛን በተመለከተ የተነጋረው – ተፈጽሟል!ይፈጸማል!!!
• ታከለ ዑማን በተመለከተ የተናገረው በቅርቡ ይፈጸማል ተብሎ ይጠበቃል። 
•••
ጋዜጠኛ ነው። ያውም ወኔ ያለው፣ ደመሙቅ፣ ቀበቶው ያልላላ፣ ያልተፈታ የጠበቀ፣ የአባቶቹም ልጅ የሆነ ጋዜጠኛ ነው። ትውልዱና እትብቱ የተቀበረው አዲስ አበባ ሸገር አዱ ገነት ነው። ዕድል አሜሪካ የወሰደው። በዚያም ሰው የደረሰበት የደረሰ ምሁርም ነው። ነገር ግን በዚያው ቀልጦ አልቀረም። ሀገሬን ብሎ፣ ኢትዮጵያን ብሎ ለሥጋ ሁሉ ሙሉ ሁሉ ዝግጁ ከሆነችው ሀገረ አማሪካንን እርግፍ አድርጎ ትቶ እትብቱ ወደተቀበረባት አዱ ገነት ጠቅልሎ ገባ።
•••
እነ መለስ ዜናዊ አባቶቻችን በታላቅ መስዋዕትነት አስከብረው ያቆሟትን ሀገር አንዴ በሰሜን ቆርሰው ሲሸጡ፣ አንዴ በምሥራቅ ሊሸጡ ሲያስማሙ፣ ደቡብንና ምዕራቡን እንደ ገና ዳቦ ሊቆራርሱና ሊያቆራቁሱ ሲደክሙም አየ። ተመለከተም። በተለይ ሀገር መሥራቹ ዐማራ ላይ የተለያዩ የዳቦ ስሞች በማውጣት ግፍ ሲሠራ፣ ዘሩ ከምድረ ኢትዮጵያ ሊጠፋ ሲወሰንበትም አየ፣ ተመለከተም።
•••
ነደደው፣ ቆጨው፣ በገነ፣ አረረም። እናም ወሰነ፣ ቆረጠ፣ ትጥቁንም ታጥቆ ተነሳ። መትረየስ፣ ጀትና ታንክ ከታጠቀው የህወሓት ሰው በላ ሥርዓት ጋር ባዶ እጁን ሊፋለም ተነሣ። ልክ አባቶቹ እነ እምዬ ምንሊክ የህወሓትን አያቶች እነ ፋሽስት ኢጣልያን ዓድዋ ላይ ጭስ በጠገበ ጎራዴና ጋሻ መድፍ ተሸክሞ የመጣውን ወራሪ ልክ እንዳስገቡት እስክንድርም እነ መለስ ዜናዊን ልክ ሊያገባ ብዕሩን ብቻ ጨብጦ ተነሣ።
•••
ውጊያው ተጀመረ። ትምህርት ጠሏ ህውሓት የለመደችው ቆረጣ ነው፣ በገንዘብ ደልላ ሆዳም ጀነራል መማረክ ነበር ልማዷ። ያ ሁሉ ትምህርት ጠልቶ ጫካ ከርሞ የመጣ ባንክ ዘራፊ ወንበዴ ሁላ በአዲስ አበባ ፈተና ገጠመው። ህወሓት የለመደችው ዓይነት የቆረጣ ውጊያ መሃል ከተማ ላይ አልጠበቃትም። የእስክንድር የውጊያ ስልት የማይታይ ረቂቅ ነበር። በብዕር ብቻ የሚዋጋ ጀነራል ገጠማት። ከደቃቃ ሰውነት አውቶሚክ ቦንብ የመሰለ ብዕር የሚተፋ ተዋጊ ገጠማት። ትምህርት ጠሉ ባንክ ዘራፊው የህወሓት ቡድን እስክንድርን እንዴት ይግጠመው። እሷም እንዴት ትዋጋው። ምሽግ አትይዝ፣ ጀት አታስነሳ፣ ታንክ አታሰማራ ጨነቃት። ጠበበባት።
•••
በዘመነ ህወሓት ትግሬ፣ በዘመነ ኦህዴድ ኦሮሞ የሆኑት የአሁኑ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየው ወ/ኪዳን ያንጊዜ የፌደራል ፖሊስ አዛዥ ነበሩና እስክንድርን ቢሮአቸው ድረስ ጠርተው “ ስማ እኛ አንተን ማሰር ሰልችቶናል። ታርፍ እንደሁ እረፍ። ያለበለዚያ… …”  አሉት። እሱ እቴ አላግጦባቸው ወጣ። እጁን ቢሠብሩት፣ ከርቸሌ ቢያወርዱት። አባቴ ይሙት አልፋታችሁም አላቸው። ወጥሮ ተገተጋቸው።
•••
እስክንድር ጋዜጠኛ ብቻም አልነበረም፤ ነቢይም ጭምር እንጂ። እስከአሁን ሁለት ትንቢቶቹ ሲሰምሩለት ዓይቻለሁ፣ ታዝቤያለሁ፣ አረጋግጫለሁም። ሦስተኛውኛው ትንቢቱም በቅርቡ የተናገረው ስለሆነ ጊዜውን ጠብቆ ይፈታል ባይ ነኝ።
ትንቢት ፩ ዐማራው ታሪኩን ያድሳል። 
•••
ይህ የመጀመሪያው የእስክንድር ትንቢት ነው። የዐማራን ስም መጥራት በሚያስቀስፍበት በዚያ በእነ መለስ በረከት ዘመን ነው እሱ ራሱ በሚያዘጋጃት ምንሊክ በተሰኘችው ጋዜጣው ላይ በየሳምንቱ በመፈክር መልክ ይዟት የሚወጣው። ምንሊክና ዐማራ አንድ ላይ ሲጠሩ የሚነስረው የህወሓት ሥርዓት ሱሪው ረጠበ። ዐማራውን ነፍጠኛ አውሮፕላን አብራሪ፣ ስመጥር ሃኪም ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስን ቋንጣ አድርጎ፣ አድርቆ የበላው የመለስ በረከት ሥርዓት በእስክንድር ላይም ተቆጣ። ደበደቡት፣ አሰሩት። ወይ ፍንክች አለ እሱ።
•••
ኋላ ላይ ግን ጊዜውን ጠብቆ ዐማራውን እቀብራለሁ ያለው መለስ ተቀብሮ፣ ዐማራውን እናጠፋዋለን ያሉት ጓደኞቹ እንደ ጠዋት ጤዛ እልም ብለው ተንነው ጠፍተው፣ ዐማራውን ሲያስር የከረመው በረከት ቃሊቲን እንኳ ተነፍጎ ባህርዳር በጋራ ሽንት ቤት በፖሊስ ጣቢያ ታስሮ ይኸው ዐማራ ታሪኩን ያድሳል የሚለው የእስኬው የትንቢት ቃልም ተፈጽሞ ታየ። አሁን አዲሱ የዐማራ ትውልድ ታሪኩን ለማደስ ከጫፍ እስከጫፍ ቃሉን እንደ መፈክር ይዞ እየተነቃነቀ ይገኛል።
ትንቢት ፪ አማርኛ ቋንቋ የአፍሪካ የሥራ ቋንቋ ይሁን።
•••
ይሄኛው ትንቢት ደግሞ ሁለተኛው የማስታውስለት የእስክንድር የትንቢት ቃሉ ነው። ዐማራንና አማርኛን ለማጥፋት የመለስ በረከት ሥርዓት መከራውን በሚበላበት ሥርዓት ውስጥ ሆኖ እንደ ጋዜጠኛ ሳይሆን እንደ ሀገር መሪ ብቻውን ድምፁን ያሰማ ጋዜጠኛ ነው። ከዛሬ 15 ዓመተት በፊት አማርኛን የኅብረቱ የሥራ ቋንቋ ለማድረግ ብቻውን የተንቀሳቀሰ ሰው ነው እስኬው። ቀናት ቀናትን ወልደው ዓመታትም ተፈጥረው የአማርኛ ጠላቶች ገሚሱ ከመቃብር ወርዶ፣ ገሚሱ ባህርዳር 9ነኛ ፖሊስ ጣቢያ ታስሮ፣ ገሚሱ መቐለ አክሱም ሆቴል የቁም እስር ራሱን በራሱ አስሮ፣ ገሚሱ በትግርኛ፣ ገሚሱ በኦሮምኛ እሪሪ ቋ ቀምበጭ ቢልም ኃያሉ አማርኛ ሁሉን ድል አድርጎ በጋዜጠኛው ንፁሕ ትንቢት በነብዩ እስክንድር ነጋ የተጀመረው ትግል በዛሬው ዕለት ፍሬ አፍርቶ በጠሚዶኮ አቢቹ አቅራቢነት ትንቢቱ ፍጻሜውን አግኝቷል ተብሏል።
•••
ይህም ዜና እውነት ከሆነ የጎበናን ልጆች ማመስገን ግድ ይለናል። ጠሚዶኮ ዐብይ አህመድ አሁንም ለዚህኛው ሥራህ ካለሁበት ቦታ ከራየን ወንዝ ዳር ሆኜ ጎንበስ ብዬ እጅ እነሳለሁ። በእነ አቢቹም ጥረት ይሁን በሌላ ብቻ ዛሬ በአፍሪካ ኅብረት በነበረው የመሪዎች ስብሰባ ላይ አማርኛ 6 ተኛው የአፍሪካውያን ኦፊሴሊያዊ የሥራ ቋንቋ ሆኖ እንዲሠራበት ተወስኗል። ይሄ ጉዳይ በተነሣ ጊዜ ሁሉ ጠሚዶኮ ዐቢይ አህመድም የማይሞት ስም ተክሎ በኢትዮጵያውያን ሁሉ ዘንድ ስሙ ሲነሣና ሲወሳ ሲዘከርም ይኖራል። አከተመ ።
•••
አሁን ኦሮሞን በማይወክሉ ጥቂት የህወሓት ዲቃላዎች ዘንድ ጫጫታው በርትቷል። እንዴት ምን ሲባል አማርኛ አለቃችን ይሆናል በሚል ደም እያስመለሳቸውም፣ እያስቀመጣቸውም ነው። ምንም ማድረግ አይቻልም። አንዳንዶቹማ ይገርሙኛል ምን የመሰለች ውብ ቆንጆ የዐማራ ሴት አግብተው አቅፈው እያደሩ። ምንምን የመሰሉ ውብ ልጆች ከዐማራዋ ሚስታቸው ወልደው እያሳደጉ፣ ራሳቸውም ወይ በአባታቸው፣ ወይ ደግሞ በእናታቸው ከዐማራው ነገድ ተወልደው ሲያበቁ ዐማራ ይጥፋ፣ ዐማራ ጨቋኝ ነው ሲሉ ሚስታቸው፣ ልጆቻቸውና ወላጆቻቸው ይታዘቡናል አለማለታቸው ነው የሚደንቀኝ። ጃዋር መሀመድ በእናቱ እኮ ዐማራ ነው። ወዳጄ በክልሎች እንዳይነገር የቁም እስር የተፈረደበት አማርኛ ጭራሽ የአፍሪካውያን የሥራ ቋንቋ ሆኖ አረፈው። ህወሓት እንኳ በትግርኛ ብቻ መደስኮሩ አላዋጣት ሲል አፏን ሬትሬት እያላትም ቢሆን በትግራይ ቲቪ አማርኛ ፕሮግራምን ማቅረብ ግድ ብሏታል። ግድ ነው።
•••
አማርኛ በዐማራዎች ይፈጠር እንጂ የዐማራዎች ንብረት አይደለም። አማርኛ የኢትዮጵያ ኃብት ነው። የኦሮምኛም፣ የትግርኛም፣ የጉራጊኛም፣ ወዘተ ባለቤቷ ኢትዮጵያ ናት። ምድረ ብሶተኛ ሁላ በኢትዮጵያ የሆነ መንደር ውስጥ ስለተወለደ ብቻ ቋንቋውን ራሱ ፈጥሮ ጠፍጥፎ የሰጠን ይመስል የእኔ፣ ነው የእንትና ነው እያለ ሲለፋደድ ይውላል። ወፏ ግን ሁሉንም በጭባጫ ከአፋቸው ነጥቃ አማርኛን በአፍሪካ ሰማይ ላይ ሰቀለችው። ማንም ከማይደርስበት ማማ ላይ ሰቀለችው። ወፏ። አከተመ።
•••
* ካናዳና ጀርመን ምእራባውያኑ ግዕዘን በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ማጥናት ጀምረዋል።
 * ፖላንድ ዋርሶ ዩንቨርሲቲ የግዕዝ ቋንቋ ራሱን በቻለ ዘርፍ ያስተምራል።
በአውሮጳ ግዕዝ የሚናገሩ፣ የሚጽፉ ነጮችን ማየት ብርቅ አይደለም ።
ኢትዮጵያን ግን ለግዕዝ ባይተዋር አደረግናት። የወላድ መካን አደረግናት። ስንትና ስንት የረቀቁ ምስጢሮችን የያዘ ቋንቋ በባንዳ የልጅ ልጆች ይወቀጣል። ይሰደባል። ይረገጣል። የህዋ ሳንይስ፣ የስነፈለክ ተመራማሪዎች፣ የዕጸዋት ሳይንስ፣ የህክምና፣ የከርሰ ምድር፣ የጠፈር ምርምር፣ የእምነት ምስጢር፣ የመድኃኒት ቅመማዎችን አካትቶ ሌላ ሌላም የረቀቁ ምስጢሮችን የተሸከመው ጥንታዊውና ሰማያዊውን ቋንቋን ትራስ አድርጎ ተኝቶ፣ የዛሬ 8 ሺ ዓመት የተፈጠረውን ግዕዝን፣ የዛሬ 8እና 9 መቶ ዓመት አካባቢ የተፈጠረውን አማርኛን ንቆና ትቶ አዳሜ የዛሬ 20 ዓመት ፈረንጆቹ ፈጥረው በሰጡትና የራሱ ባልሆነ የቅኝ ገዢዎች ቋንቋ በማያውቀውም የላቲን ቋንቋ መከራውን ስቢላ ይውላል፣ ያድራልም። ጭቡጦውን የተቀማ ትውልድ።
•••
የእስክንድር ትንቢት ቀጥሏል። እስክንድር ከእስራኤል ዳንሳ ይበልጣል። ከኢዩ ጩፋም ይበልጣል። አንዲት ቃል ባወጣ ቁጥር ሺዎች ይንበጫበጫሉ። ይለፈልፋሉም። እስክንድር መስቀል የተሸከመ ጋዜጠኛ ነው። የዲሞክራሲ ቡዳዎች፣ የዲሞክራሲ አጋንንት በፊቱ ሊቆሙ አይደፍሩም። ምክንያቱም እስክንድር በእሳት የተፈተነ ነቢይ ነው። አከተመ።
•••
በህይወቴ እስክንድርን ያገኘሁት ሁለት ቀን ብቻ ነው። አንደኛውን ቀን የመብረቅ ጋዜጠኛ የነበረውና አሁን ካናዳ ከሚኖረው ከመብረቅ ጋዜጣ ባለቤት ከነበረው ከጋዜጠኛ ሰይፈ ጋር ሲሆን በሌላው ቀን ደግሞ አሁን የዘ ሐበሻ ድረገጽ ባለቤት ከሆነው ከጋዜጠኛ ሔኖክ አለማየሁ ጋር ሆኜ ነበር ያገኘሁት። ከሰይፈ ጋር ያገኘሁት ቀን ረዘም ላሉ ደቂቃዎች የተጨዋወትን ሲሆን ከሄኖኬ ጋር ያገኘሁት ቀን ግን ብዙም የማውራት ዕድል አላገኘሁም። አንድ ቀን ደግሞ በድጋሚ እንደማገኘው ግን ተስፋ አደርጋለሁ።
•••
“ነቢዩ እስኬው” ታከለ ኡማ ይሄን ይሄን ልዩ ጥቅም የሚል ነገር ካላቆመ በድምጻችን እንቀጣዋለን በማለቱ እንዴት አቧራው እንደጨሰ ዓይተናል። እናም ይሄ የእስክንድር ትንቢት እንዳይፈጸምበት ታከለ ኡማ ከአሁኑ ቢነካው ይሻለዋል ባይ ነኝ። ውኃ ጠብሰው የሚበሉ አዲስ አበቤዎችን አጃጅላለሁ ማለት ትርፉ ኪሳራ ነው።
በመጨረሻም ስለአማርኛ ቋንቋ ጋዜጠኛ በየሺሀሳብ አበራ እንዲህ ሲል የከተበውን ጽሑፍ አቅርቤላችሁ እንሰነባበታለን።
#አማርኛ~
★ ከምዕራብ አፍሪቃው ሀውሳ እና ከምሥራቅ አፍሪቃው ስዋህሊ ቋንቋ ቀጥሎ የአፍሪቃ ትልቁ ቋንቋ ነው፡፡
★ ከሰሜቲክ የቋንቋ ቤተሰቦች በስፋት በመነገር ከዐረብኛ ቀጥሎ ሁለተኛ ቋንቋ ነው፡፡
★ ከ85.6 ሚሊየን በላይ ተናጋሪ አለው።
★ ከ1272 ዓም ጀምሮ የኢትዮጵያ የመንግሥት የሥራ ቋንቋ ነው፡፡
★ ከአፍሪቃ ብቸኛው ባለፊደል ቋንቋ ሲሆን፣ ብዙ ፊደላቱን ከወንድሙ ከግዕዝ ተውሷል፡፡(ግዕዝ የአማርኛ አባት አይደለም፡፡ ሁለቱ ቋንቋዎች በሰዋሰው መዋቅር እና በስነ ልሳን ትንታኔ ልዩነት አላቸው፡፡
★ አማርኛ በቋንቋ መዋቅሩ ከሴሜቲክ ቋንቋዎች ይልቅ ወደ ኩሽቲክ ቋንቋዎች የቀረበ ነው፡፡
★ የላንቃ ድምፆችንም ራሱ ፈጥሯል ፡፡
( ሸ፣ጨ፣ዠ፣ቸ፣ጀ፣)
★ 85 ከመቶው ኢትዮጵያውያን በአፍ መፍቻ አሊያም በሁለተኛ ቋንቋነት ይናገሩታል ፡፡
★ ከአፄ ቴዎድሮስ መነሳት ጀምሮ በስፋት ወደ ጽሑፍ ቋንቋነት አድጓል፡፡
★ አሁን ላይ የዐማራ፣ የጋምቤላ፣ የቢሻንጉል ጉምዝ፣ የደቡብ ክልል፣ የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳድሮች የሥራ ቋንቋ ነው፡፡
★ የኢትዮጵያም የሥራ ቋንቋ ሲሆን፣ አማርኛ በአሜሪካ መንግሥትም በአንዳንድ ግዛቶች የሥራ ቋንቋ እንዲሆን ተፈቅዷል፡፡
★በአሜሪካ ብቻ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተናጋሪዎችም አሉት፡፡
★ ለአብነት በ2016 የአሜሪካ ምርጫ አማርኛ በሚኒሶታ ግዛት የምርጫ ካርድ በአማርኛ ቋንቋ ተዘጋጅቷል ፡፡፡
★ ከ1981 ዓም ጀምሮ አማርኛ በዶክተር አበራ ሞላ አማካኝነት እስከ ሙሉ ፊደላቱ የኮምፒውተር ቋንቋ ሁኗል ፡፡
★ ከመጋቢት 10 2008ዓም ጀምሮ ደግሞ የጎግል መተርጎሚያ ቋንቋ ሁኗል፡፡ አሁን ላይ በጎግል አማካኝነት አማርኛን ወደ ማንኛውም ቋንቋ መተርጎም ይቻላል ፡፡
★ ፌስቡክም አማርኛን መጠቀሚያ ቋንቋ ዝርዝር ውስጥ አስገብቶታል፡፡ (ከፌስቡካችሁ ታች ላይ አረጋግጡ፡፡ ፌስቡክ መተግበሪያን በአማርኛ ማድረግም ይቻላል ፡፡)
★ አማርኛ በዓለም ላይ ያሉ ነገሮችን 95 ከመቶው በላይ መግለፅ ይችላል ፡፡
★ አማርኛ አሁን ደግሞ የአፍሪቃ የሥራ ቋንቋ እንዲሆን በተጠየቀው መሠረት ለወደፊት የአፍሪቃ ኅብረት የሥራ ቋንቋ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። ያንጊዜም አፍሪቃ እውነትም ከቅኝ ግዛት መላቀቋን ታሳያለች።
★ ጭንቅላታቸው በጥላቻ የተሞላ አንዳንድ ሰዎች ዐማራን የጎዳን መስሏቸው አማርኛን ሲያንቋሽሹ ይስተዋላል። ይህ ፍፁም ስህተት ነው።
★አማርኛ ከዐማራው ነገድ የተገኘ ይሁን እንጅ የኦሮሞው፣ የጉራጌው፣ የሱማሌው፣ የጉሙዙ የተንቤኑ፣ የኩናማው፣ የጋምቤላው፣ በአጠቃላይ የሁሉም ኢትዮጵያውያን የእኔ የአንቺ የአንተ የሁላችንም ሀብት ነው። ከልሳነ ግእዝ ቀጥሎ የኢትዮጵያ ምስጢራትን ከትቦ የያዘ ስለሆነ እንወቀው እንንከባከበውም።
በምንጭነት
-በባህርዳር መካነ አእምሮ በተለያዩ ጊዜያት በአማርኛ ቋንቋ ላይ የተካሄዱ ጥናቶች
-የፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ – መጽሐፍ
-የዲያቆን ዳንኤል ክብረት – ጥናት ተጠቅሟል።
ወዳጄ ሆይ !
★ ዐማራም ታሪኩን አድሷል
★ አማርኛም የአፍሪካውያን የሥራ ቋንቋ ሆኗል።
★ የግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሃውልትም ንጉሡን ባይመስልም በስማቸው ግን ሃውልት ቆሟል። ድል ለዲሞክራሲ። ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር።
ሻሎም!  ሰላም ! 
ጥር 3/2011 ዓም
ከራየን ወንዝ ራዶም
Filed in: Amharic