>
5:16 pm - Thursday May 23, 1811

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከእስክንድር ነጋ ጋር ለመወያየት እንደሚፈልጉ ገለጹ

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከእስክንድር ነጋ ጋር ለመወያየት እንደሚፈልጉ ገለጹ

 

 ኢሳት

 

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ከጋዜጠኛና የሰብአዊ መብት ታጋዩ እስክንድር ነጋ ጋር ለመወያየት እንደሚፈልጉ አስታወቁ።

ዶክተር አብይ አህመድ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን አስመልክቶ ከ40 በላይ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን፥ምሁራን እንዲሁም ታዋቂ ሰዎች በጽሁፍ ላቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።

እስክንድር ነጋን በተመለከተ በኢትዮጵያ ሰላምና ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ሰብአዊ መብትም እንዲከበር ያደረገውን አስተዋጽኦ እኔም የማደንቀው ነው ብለዋል።

ባነሣቸው ሐሳቦች ምክንያት በመንግሥት በኩል በጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ላይ ምንም ዓይነት ጫናና ችግር አይደርስበትም ሲሉም ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምሁራኑና ታዋቂ ሰዎች በጻፉት ደብዳቤ ለሀገራችሁና ለሕዝባችሁ በመቆርቆር፣ ሀገራችሁም የተሻለችና የሠለጠነች እንድትሆን በማሰብ የጻፋችሁትን መልእክት እንደ እናንተ ካሉ በሳል ዜጎች የሚጠበቅ ነው ብለኣውል፡፡በዚሁም መሰረት  ችግሮችን በጨዋነት በመመካከርና የተሻለ የመፍትሔ ሐሳብ በማቅረብ መፍታት እንደሚገባ የእናንተ ተግባር አርአያነት ያልው ነው ሲሉ በምላሻቸው ገልጸዋል፡፡

በሀገራችን የተፈናቀሉ ዜጎችን በተመለከተ ያነሣችሁት ሐሳብ ሁላችንም የምንጋራው ነውም ሲሉ ነው የገለጹት፡፡ እናም በሕዝባችን የተጀመረውን የለውጥ ተስፋ ለማጨለም በሚሠሩ አካላት፣ በሌላ በኩል ደግሞ በቢሮክራሲው ውስጥ ያሉ ኃላፊዎች ችግሮችን በእንጭጭነታቸው ለመፍታት ባለመረባረባቸው የተነሣ የዜጎቻችን መፈናቀል መከሠቱ እኛንም ያሳዝነናል ብለዋል፡፡ይሕንኑም ችግር ለመፍታትና ተፈናቃዮችን ልመመለስ እየተረባረብን ነው ሲሉ ነው የገለጹት። እንደ ታማኝ በየነ ያሉ የወገኖቻቸው ሁኔታ የሚያሳስባቸው ዜጎች ታሪካዊ ኃላፊነታቸውን ሲወጡ እያየን በመሆኑ ችግሮቻችን እድሜያቸው እንደሚያጥር ርግጠኞች ሆነናል ሲሉም ገልጸዋል።

እስክንድር ነጋን በተመለከተ በኢትዮጵያ ሰላምና ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ሰብአዊ መብትም እንዲከበር ያደረገውን አስተዋጽዖ እኔም የማደንቀው ነው፡፡ ለዚህ ተጋድሎውም ተገቢው አክብሮት አለኝ፥ ያነሣቸውን አንዳንድ ሐሳቦች በተመለከተ ግን መፍትሔው ውይይት ነው ብለዋል፡፡ በቅርቡም ባነሣቸው ጉዳዮች ላይ እንደምንወያይ ተስፋ አደርጋለሁ ሲሉም ነው የገለጹት።

ባነሣቸው ሐሳቦች ምክንያት በመንግሥት በኩል የሚደርስበት ምን ዓይነት ጫናና ችግር አይኖርም ሲሉ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡

ረዥሙን የለውጥ ጉዞ ጀመርን እንጂ አልጨረስነውም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ካሳለፍነው ይልቅ ከፊታችን ያለው ረዥም ነው ነው ብለኣዋል፡፡ እንዲህ እንደናንተ ያገባናል የሚሉ ዜጎች በሰከነ መንገድ ለሀገራቸው የሚችሉትን ሁሉ ሲያበረክቱ ነገ ከትናንት የተሻለ ይሆናል ሲሉም ደብዳቤውን ለጻፉላቸው ምሁራን ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል ፡፡

Filed in: Amharic