>

ኤርምያስን አስሮ የአሊባባ የአፍሪካ ውክልናውን መንጠቅ  የሴራ ፖለቲካ ነው!!! (ያሬድ ጥበቡ)


ኤርምያስን አስሮ የአሊባባ የአፍሪካ ውክልናውን መንጠቅ  የሴራ ፖለቲካ ነው!!!
ያሬድ ጥበቡ
ኤርምያስን ወደ ወህኒ የወረወሩት መንግስታዊ ሃይሎች፣ ኤርምያስን በእስር በማቆየት እርሱ ከአሊባባ ጋር ፈፅሞት የነበረውን የአፍሪካን ውክልናውን ውል ማስፈረስና መንጠቅ የቋመጡ ሃይሎች ይመስሉኛል። ይህን ግባቸውን እስኪመቱም በእስር አቆይተው በመጨረሻ ያለምንም ክስ ይፈቱታል!!!
ይህን የጠቅላይ ሚኒስትሩን የአሊባባ ጉብኝት ዜናና ምስል ሳይ ትልቅ የፍትህ መጓደል ይሰማኛል። እዚህ ጉብኝት ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎን መገኘት የነበረበት የቢዝነስና ፋይናንስ ባለሙያው አቶ ኤርምያስ አመልጋ ነበር። ሆኖም በአሁኑ ወቅት ኤርምያስ እስር ቤት ነው። በጠቅላይ ሚኒስትሩ እስር ቤት።
ኤርምያስን ከሜቴክ ብክነት ጋር ለማያያዝ ጥረት ቢደረግም እስካሁን የተገኘበት ወንጀል የለም ። እኔ ከዚህ በፊትም እንደጠረጠርኩትና ይፋ እንዳደረግኩት፣ ኤርምያስን ወደ ወህኒ የወረወሩት መንግስታዊ ሃይሎች፣ ኤርምያስን በእስር በማቆየት እርሱ ከአሊባባ ጋር ፈፅሞት የነበረውን የአፍሪካን ውክልናውን ውል ማስፈረስና መንጠቅ የቋመጡ ሃይሎች ይመስሉኛል። ይህን ግባቸውን እስኪመቱም በእስር አቆይተው በመጨረሻ ያለምንም ክስ ይፈቱታል።
የኤርምያስ እስራት የአሊባባ የአፍሪካ ወኪል ከመሆኑ ጋር የተያያዘና ከሜቴክ ጋር  የተገናኘ እንዳልሆነ የሚጠቁሙ ብዙ ምክንያቶች አሉ ። በቅርቡ ከአስርቤት ባወጣው “ቲፒንግ ፖይንት” በተሰኘው መፅሃፉ ይፋ እንዳደረገው ለሜቴክ በሸጠው የኢምፔሪያል ሆቴል ጉዳይ ከዚህ በፊት ተጠይቆበት መንግስት ከጥርጣሬ ያለፈ መረጃ ስለሌለው ውድቅ አድርጎ የተወው ጉዳይ ነበር ። በተጨማሪም አክሰስ ካፒታል ከኢምፒሪያል ሆቴል ሽያጭ አንዲት ሳንቲም አላተረፈም ። በሶስተኛ ደረጃ ቢያተረፍ እንኳ አንድ የቢዝነስ ተቋም የገዛውን አትርፎ ስለሸጠ ወንጀል አይሆንም ። በአራተኛ ደረጃ ከቢዝነስ ልውውጡ አመራሩ በቀጥታ በግል ተጠቃሚ ሆኗል የሚል ማስረጃ እስከሌለ ድረስ በሙስና ጉዳይ በቢዝነስ መሪዎች ላይ የእስራት እርምጃ መውሰድ ተገቢ አይደለም። በመጨረሻ፣ ኤርምያስ የታሰረው ከአሊባባ ጋር ውሉን ፈፅሞ ሥራውን ለማካሄድ የሚያስፈልገውን የባንክ ድጋፍ ለመነጋገር ከንግድ ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት የሆነ ባለሥልጣን ጋ ቆይቶ እንደተመለሰ ነው ። አሁን በእስር ላይ እያለም የሚጠየቀው በነጄኔራል ክንፈ ላይ የወንጀል ምስክር እንዲሆን ነው።
ባለፈው ሳምንት የልብ ጥገና ባለሙያው ዶክተር ፍቅሩ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ቃለምልልሳቸው እንደነገሩን የኤርምያስም ክስ ተመሳሳይ ነው። ዶክተር ፍቅሩ ባልፈፀሙት ወንጀል፣ በጉምሩክ ባለሥልጣናት ላይ ምስክር እንዲሆኑ ስለተፈለገ ብቻ ከአራት አመታት በላይ በእስር ማቅቀዋል። እርሳቸው በእስር ላይ እያሉም የልብ ባትሪያቸውን በመቀየር ብቻ ሊድኑ የነበሩ ሃያ በሽተኞቻቸው ሞተዋል። ዶክተሩ ፍርድቤቱ ፍቃድ ሰጥቷቸው የታማሚዎቻቸውን ባትሪ እየቀየሩ ወደእስር መኝታቸው እንዲመለሱ ያቀረቡትን አቤቱታ ዳኞቹ ውድቅ አድርገውታል ። በዚህም የሰዎች ህይወት ጠፍቷል ። ዳኞቹም ለወንጀላቸው ተጠያቂ አልተደረጉም፣ አሁንም በፍርድ ችሎት ላይ ተቀምጠዋል ።
የኤርምያስ አመልጋም ጉዳይ በብዙ መልኩ ከዶክተር ፍቅሩ ጋር ተመሳሳይ ነው። ልክ እንደ ዶክተር ፍቅሩ ኤርምያስም ባልተሰራ ወንጀል እነጄኔራል ክንፈ ላይ እንዲመሰክር እየተጠየቀ ነው ። ኤርምያስ እንደ ዶክተር ፍቅሩ የእምነት ሰው በመሆኑ ለዚህ መንግስታዊ ወንጀል አልተባበርም ብሎ ግፍ እየተቀበለ ነው ። የኤርምያስን ግፍ እጥፍ ድርብ የሚያደርገው ግን፣ በእርሱ እስራት ሃገራችን የምታጣው የሃያ ልብ ህሙማንን ህልፈተ ህይወት ብቻ ሳይሆን፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወጣት ሥራአጦችን ህይወት ነው። ኤርምያስ ለነዚህ ወጣቶች የሚሆኑ ሥራዎች እንዴት እንደሚፈጠሩ፣ የስቶክ ማርኬት እንዴት እንደሚጀመር፣ እንደ ቴሌኮም ያሉ የህዝብ ንብረቶች በምን ጥንቃቄና ቅድመ ዝግጅት ከሙስናና ወንጀል በፀዳ መልክ ወደግል ሊዘዋወሩ እንደሚችሉ ወዘተ ወዘተ ብዙ ለሃገር የሚጠቅሙ ሃሳቦች ያሉት ዘመናዊ ምሁር ነው። ዛሬ ኤርምያስ በፅልመት ሃይሎች ደባ በወህኒ ጨለማ ይማቅቃል። ለምን?
እርሱን ወደ ወህኒ በወረወሩ ማግስት ወደ ዳቮስ ሄዶ ከአሊባባ ዋና ሥራአስኪያጅ ጋር ፎቶ መነሳት ምን ዓይነት መሪር ቀልድ ነው? ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይወቁትም አይወቁትም በዙሪያቸው ወንጀል የሚሰሩ ባለሥልጣናት ለመኖራቸው የኤርምያስ አመልጋ እስራት አመላካች ነው። ዛሬም ኢትዮጵያ ለፍትህ ትጮሃለች። በግፍ ያሰራችሁትን ልጄን ፍቱና የአቅሙን ለሃገሩ ያበርክት ትላለች። ከማንም በፊት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን የኢትዮጵያ ጩኸት መስማት አለባቸው። ከጠቅላይ ሚኒስትሩም ቀጥሎ ወይዘሮ መአዛ አሸናፊ ይህን የኢትዮጵያ ጩኸት ሊያደምጡ ይገባል። ወይዘሮ መአዛ የወዳጄ የዶክተር አርአያ ባለቤት ናቸው። በጣም በትንሹም አውቃቸዋለሁ። በሹመታቸውም ከተደሰቱ ሰዎች መሃል ነኝ ። ዓይኗን የተሸበበችው የፍትህ እመቤት ምሳሌ አድርጌ ልቤ በደስታ ተመልታ ነበር ። ሆኖም በኤርምያስ ላይ የተደረገውን የፍትህ መዛባት ለማስቆም ባለመቻላቸው አዝኜባቸዋለሁ። አሳሪዎቹን ባለሥልጣናት ፈርተው ዝምታን የመረጡ መስሎ ተሰምቶኛል። አዲስ አበባ እስክመጣ ኤርምያስ ካልተፈታ በጉዳዩ ላይ ወይዘሮ መአዛን ለማነጋገርና ፈቃደኛ ከሆኑም አብረን ሄደን ኤርምያስን ለማናገር ውጥን አለኝ። እስከዚያው ከእስርቤት የፃፈውን መፅሃፉን የኪንድል ህትመት በዘጠኝ ዶላር ገዝተው እንዲያነቡት በህዝብ አደባባይ መማጠን እወዳለሁ። እግረ መንገዴንም በአዲስ አበባ ቆይታዬ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለማህበራዊ ሚዲያ በተደጋጋሚ ስለሚያሰሙት ቅሬታና መፍትሄውን በተመለከተ ለማነጋገር ፍላጎት አለኝ ። ዋሽንግተን አዲስ በመጡት አምባሳደር በኩል ቀጠሮ ለመያዝ እሞክራለሁ ። አበቃሁ! ቸር ይግጠመን
 
በጠ/ሚ ዐቢይ የተመራው ልዑክ #የአሊባባን ኩባንያ ጎበኙ 
P.M.O Ethiopia
በኤሌክትሮኒክስ-ንግድ (E –commerce) ጉምቱ የሚባዉ አሊባባ ኩባንያ ዋና መስሪያ ቤት በቻይና ሀንግዙ ይገኛል፡፡ የኩባያዉ መስራችና ባለቤት ጃክ ማ “እንኳን ደህና መጣችሁ” የሚል አማርኛ ፁሁፍ በስክሪን አፅፈዉ ለጠ/ሚንስትሩና ልኡካቸዉ አቀባበል አድርገዉላቸዋል፡፡
በዚሁ የፈረንጅ አመት መጀመሪያ አካባቢ በሲውዘርላንድ ዳቮስ ጠ/ሚር ዐቢይ አሕመድና የአሊባባ ኩባንያ ሊቀመንበር የሆኑት ጃክ ማ ተገናኝተው ከተወያዩት የቀጠለው ይህ ጉብኝት የኢትዮጵያ ልማትና እድገት ለመደገፍ የተጀመረውን ወዳጅነት አመላካች ነው።
ጃክ ማ እንዳሉት በኢትዮጵያ እየተካሄዱ ባሉት ለውጦች መደነቃቸውንና ኢትዮጵያ ለኩባንያቸው ቁልፍ አጋር በመሆኗም በዚህ አመት መጨረሻ የኢትዮጵያ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ገልፀዋል።
Filed in: Amharic