>

ግንቦት 20 ለኔ ፤ ያኔም ሆነ ዘንድሮ (መስፍን ማሞ ተሰማ)

ግንቦት 20 ለኔ ፤ ያኔም ሆነ ዘንድሮ

መስፍን ማሞ ተሰማ

ሠላም ለናንተ ይሁን!

በአምባ ገነኑ የደርግ ዘመነ መንግሥት እስከ ግንቦት 20/1983 ዓ/ም ኢትዮጵያውያን (ከዘር ሀረጋቸው በፊትና በላይ በኢትዮጵያዊነታቸው የሚያምኑና የማይደራደሩ፣ ታሪካቸውን በታሪክነት ተቀበሰለው የታሪክ ቂም በቀል ያልወረሱና ለዚህም ያልዘመቱ ሁሉ) ሀገር ነበራቸው፤ መቀመጫ። ሰሜን ብንወጣ ጎጆ ብንቀልስ፤ ደቡብ ብንወርድ ስራ ብንፈልግ፤ ምሥራቅ ብንቀመጥ ሱቅ ብንከፍት፤ ምዕራብ ብንኖር ብንነግድ/ብናስተምር ማንም መጤ፥ ማንም ሠፋሪ እያለ አያፈናቅለንም፥ በገጀራና በቀስት አይፈጀንም ነበር።

እንደ መንግሥት ደርግ ሁሉንም ዘር ማንዘር ሳይዘረዝር በሥልጣኑ የመጣበትን ሁሉ ፈጅቷል አስሯል አሳዷል። እኔም በወጣትነት ዘመኔ ደርግን ለመጣል ከህይወት መትረፍ በመለስ መራር መከራ ተቀብያለሁ፤ ለዓመታት በወህኒ በመማቅ ወጣትነት ዘመኔን ገብሬያለሁ፤ መስዋዕትነት ከፍያለሁ። ያም ሆነ ይህ ግን በደርግ አገዛዝ ዘመን ሀገርና ታሪክ ነበረኝ/ነበረን። ከሁሉም በላይ ደግሞ ኢትዮጵያዊነታችንን ደርግ አልገፈፈንም። በዘር ማንዘር ክልል ሸንሽኖ ከሰውነት ተራ አላወረደንም።

ግንቦት 20 ግን በኢትዮጵያ የዘመናት ታሪክ የተለየ ነው፣ የጣልያን ቅኝ ገዢ እንኳን ያላደረገውን የወያኔ ኢህአዴግ ቅኝ ገዢዎች ግፍና ዘመን ወለድ ታሪካቸውን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ማርከው ቅኝ ያደረጉበት ወቅት።

በአጭሩ ወያኔ መራሹ ኢህአዴግ ኢትዮጵያን የማረከበት ጊዜ ነው፥ ግንቦት 20 ። ኢትዮጵያ እስከ አንገቷ ለሰጠመችበት የዘርና የመጠፋፋት ቂም በቀል አረንቋ ብቸኛው ተጠያቂ በግንቦት 20/ 1983 ዓ/ም የኢትዮጵያን መንበር የማረከው ኢህአዴግ የተባለ የዘረኞች ስብስብ ነው። ኢህአዴግ አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ሲገባ ኢትዮጵያን ለመማረክ የዘመተበትን የዘር ማንዘር አሸን ክታብ አራግፎ በምትኩ ኢትዮጵያዊነትን ተላበሶና አትዮጵያዊነቱን እንዳለ ተቀብሎ ከዘር ቆጠራ ከአጥንት ለቀማ ተላቆ እና የዘር ችግኝ እየዘራ ከመኮትኮት፤ ጥላቻ ወለድ ታሪክ ከመፈብረክ ይልቅ ብሄራዊ ህብረትንና ኢትዮጵያዊነትን ቢኮተኩትና ቢያሳድግ ኖሮ ዛሬ ይህ ሁሉ ዘረኝነት ዋይታ ግፍ እልቂትና መፈናቀል አይኖርም ነበር!!

አዎ! በግንቦት 20 ኢትዮጵያን የተቆጣጠረው የዘር ድርጅቶች ስብስብ ኢህአዴግ በመላዋ ኢትዮጵያ የዘረጋው ዘረኛ ሥርዓት ባይኖር ኖሮ ዛሬ መጤ፤ ሰፋሪ፤ ወራሪ፤ ክልል፤ ብሄር ብሄረሰብ ህዝብ የሚለው እጅግ ከፋፋይ እና ሁዋላ ቀር መለያ መታወቂያችን አይሆንም ነበር። ይህ ሁሉ ግን ግንቦት 20 ያፈራው አሜኬላ ነው!!
እና ይህንን የግፈኞችና የወራሪ ሥርዐት ነው በበኩሌ ሀገሬን ከለቀቅሁበት የግንቦት 20 ዋዜማ ጀምሮ በስደት ዓለም አቅሜ በፈቀደው ሁሉ ስታገለው የኖርኩት። የተሰደድኩትም ሆነ የታገልኩት ኢህአዴግ ከነ ሥርዐተ ማህበሩና አብዮታዊ ዲሞክራሲ ግሳንግሱ ጋር እንዲቀየር ነው።

እርግጥ ነው ከመጋቢት 2010 ጀምሮ ወያኔ መራሹ ኢህአዴግ በፈላጭ ቆራጭነት አራት ኪሎ ባይኖርም ቅሉ እነሆ ፍፁማዊ ትዕቢትና አይነኬነት የሚያትት መግለጫ የሚያወጣው ወያኔ አሁንም የኢህአዴግ አከርካሪ ነው። የአራቱ ድርጅቶች አንደኛው አካላቸው ህወሃት ነው። ሳጠቃልል ግንቦት 20 ኢትዮጵያና ዜጎቿ ኢትዮጵያውያን በኢህአዴግ የተማረኩበት እንጂ ነፃ የወጣንበት አይደለም፤ በግንቦት 20 ላይ አቋሜ በ1983 ዓ/ም ላይ ይኸው ነበር ዛሬም በ2011 ዓ/ም አቋሜ ይኸው ነው!!

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር
ግንቦት 20/2011 (ሜይ 28/2019)
ሲድኒ አውስትራሊያ
mmtessema@gmail.com

Filed in: Amharic