>
9:47 am - Saturday November 26, 2022

ኢትዮጵያችን ‹‹ሰንበት›› እንድታደርግ (ከይኄይስ እውነቱ)

ኢትዮጵያችን ‹‹ሰንበት›› እንድታደርግ

 

ከይኄይስ እውነቱ

በዚህ አስተያየት አግባብ ‹‹ሰንበት›› የሚለው ቃል ዕረፍት፣ ኅድአት/ፀጥታ፣ ርጋታ እፎይታ፣ ሰላም፣ የሚሉትን አሳቦች ይወክላል፡፡
ኢትዮጵያችን በተለይ ላለፉት 3 ዐሥርታት በዘመነ ሀውክ ወጸብእ /ሁከት÷ ብጥብጥ÷ አምባ ጓሮ÷ሽብር /፣ በዘመነ ቀጠና ወብድብድ /ረሃብ÷ቸነፈር÷መቅሠፍት÷ችጋር/፣ በዘመነ ምንዳቤ ወዐጸባ /ችግር÷ድኽነት/ በዘመነ ጻማ ወጻዕር /መከራ÷ሥቃይ÷ጭንቅ÷ጣር/፣ በዘመነ መንሱት ወዕለታተ እኪት /ፍጹም መከራ÷ፈተና÷የከፉ ቀናት/ በዘመነ ጽማዌ /ድንቁርና/፣ ባጠቃላይ በዘመነ ጽልመት ውስጥ ትገኛለች፡፡ በሌላ አነጋገር የሰላምና የፀጥታ እጦት ጓዛቸውን ጠቅልለው የሰፈሩባት አገር ሆናለች ማለት ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር (ለልባችን÷ኅሊናና አእምሮአችን መታመን ካለብን) ከተስፋ ይልቅ ቀቢፀ ተስፋ የነገሠባት ምድር ሆናለች፡፡

በዚህ ደረጃ ወደ ጥልቁ በርባሮስ የወረድንበት ምክንያቶች ከዘመን ዘመን ሲንከባለሉ የመጡ ድምር ጥፋቶች እንዳሉ ቢታሰብም፣ ያለፉት 3 ዐሥርታት ግን በታሪካችን ተወዳዳሪ በሌለው መልኩ ከዘመን ዘመን የተላለፉልን በጎ እሤቶችንና አገርን ለማጥፋት ራሱን በመንግሥትነት የሰየመው አካል፣ በውስጥም በውጭም በ‹ነፃ አውጪነት ስም› የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችና ግብር አበሮቻቸው ያላቸውን አቅም ሁሉ አሟጠው ለጥፋት በመጠቀማቸው ትልቁን ድርሻ እንደሚወስዱ ብዙዎችን የሚያስማማ ይመስለኛል፡፡
አገራችን ከምትገኝበት አስከፊ ዘመናት ወጥታ÷ከዕብደትና ድንቊርናው ባንነን ቢያንስ ሰላምና መረጋጋት ለማግኘት በእኔ እምነት የሚከተሉት ከኢትዮጵያ ምድር መነቀል ያለባቸው ይመስለኛል፡፡

1ኛ/ ወያኔ ኢሕአዴግ የሚባለው ድርጅት ከማዕከል እስከ መጨረሻው የገጠር ቀበሌ፤
2ኛ/ ወያኔ ያቆመው የይስሙላ ‹‹ሕገ መንግሥት›› እና ይህንኑ መሠረት አድርገው የወጡ አገር አጥፊ ‹ሕጎች›፤
3ኛ/ ከ1ኛውና 2ኛው ጋር ተያያዥነት ያለው ‹‹ክልል›› የተባለው መርዛማ የእሾኽ አጥር፤
4ኛ/ አሁንም ከ1ኛውና 2ኛው ጋር ተያያዥነት ያለው የጐሣ/የዘር ፖለቲካ፤

ከዚህ የመንደርተኝነት ፖለቲካ ጋር በተያያዘ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ማስተላለፍ የምፈልገው አንድ መልእክት አለ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኅትመትም ሆነ በኤሌክትሮኒክስ ብዙኃን መገናኛዎች ‹‹አክራሪ ወይም ጽንፈኛ ጐሠኞች/ዘረኞች›› የሚል ቋንቋ እሰማለሁ፡፡ የማይድን ጽኑዕ ደዌ የሆነው የጐሠኝነት አስተሳሰብ ከመነሻው የከረረና ጽንፍ የያዘ በመሆኑ በጐሠኞች መካከል ልዩነት በማድረግ የማስታመሙ አካሄድ ባስቸኳይ ሊቆም ይገባዋል፡፡ በየትኛውም ማኅበረሰብ ይራመድ ጐሠኝነት ልንጸየፈው የሚገባ ግለሰባዊና ማኅበረሰባዊ ሕማም ነው፡፡
5ኛ/ በሙያና በብቃት ላይ መልሶ ከሚደራጅ (ጎን ለጎን አዳዲስ መልምሎ ከማሠልጠኑ ጋር) ሕግ አስከባሪ የፖሊስ ሠራዊት ውጭ በየክፍለሃገሩ ያለውን ‹‹ልዩ ኃይል›› በሚል የተደራጀውን ‹ጦር› በሙሉ ማፍረስ፤
እነዚህን በሥር ነቀልነት ካስወገድን በኋላ፣
ሀ/ መሠረታዊ በሆነ መልኩ ‹‹በአገር መከላከያነት›› ስም ያለውን ሠራዊት በሙያና በብቃት መልሶ ማዋቀር÷አዳዲስም በማሠልጠን ኢትዮጵያዊ አቋም ያለው ለፖለቲካ ድርጅት ሳይሆን ለሕዝብና ወደፊት በሕዝብ ፈቃድ ለሚቆም ሕገ-ኢትዮጵያ የሚታመን የመከላከያ ሠራዊት መገንባት፤ በ‹ሕዝብ ደኅንነት ስም› ያለውን የፀጥታ መ/ቤትም ከዘር አስተሳሰብ በጸዳ መልኩ በሙያ ብቃት÷ በአገርና ሕዝብ ወዳድነትና በጥሩ ሥነምግባር ላይ መልሶ ማነፅ፤ አዳዲሶችንም መልምሎ ማሠልጠን ያስፈልጋል፡፡
ለ/ አገርን የማረጋጋቱ ሥራ (እንደአስፈላጊነቱ የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ በማወጅም ጭምር) ከተሠራ በኋላ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚሳተፉበት አገራዊ የሽግግር ጉባኤ በማቋቋም ሕገመንግሥት (ሕገ ኢትዮጵያን) የሚጽፍ አካል ማዋቀር፤ በሙያተኞች በመታገዝ የሽግግሩን ዘመን የሚያልፍ አገራዊ ፍኖተ ካርታ በሁሉም ዘርፎች (በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማኅበራዊው መስኮች) ማዘጋጀት፤ለእውነተኛ፣ ነፃና ፍትሐዊ አገር አቀፍ ምርጫ ዝግጅት በማድረግ ምርጫውን ለሚያሸንፍ የፖለቲካ ድርጅት የአገር አመራሩን ኃላፊነት አዲሱ ሕገ መንግሥት በሚፈቅደው መሠረት ማስረከብ፡፡
በውይይት፣ በመመካከርና በመደማመጥ፣ በሃሳብ ልዩነት በመከባበር ከፍ ብለው የተመለከቱትን ዐበይት ቁም ነገሮች መፈጸም ከቻልን ኢትዮጵያችን የምንመኘውን ሰነበት/ዕረፍት ማግኘት ትችላለች የሚል እምነት አለኝ፡፡
በተጨማሪም ወንጀለኛውና ነውረኛው (በእኔ ጽኑ እምነት ምጽአት ቢመጣ ሊለወጥ የማይችለው) ቀደም ሲል በሕወሓት አሁን ደግሞ በኦሕዴድ የሚመራው የወያኔ ድርጅት አመራር አባላት (በወንጀል መጠየቃቸው እንደተጠበቀ ሆኖ) ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ቢጦሙ ወይም ‹ሰንበት› ቢያደርጉ ለአገር ትልቅ ውለታ እንደሠሩ እቈጥረዋለሁ፡፡

ልዑል አምላክ እንደ ግንቦት 20 ካለ የዕለት እኪት ይሠውረን፡፡

Filed in: Amharic