>

ዶ/ር ብርሃኑ በሎሳንጀለሱ ስብሰባ የእስክንድር  ስም በመነሳቱ ጋዜጠኛዋን ዘለፉ!!! (ወንድወሰን ተክሉ)

ዶ/ር ብርሃኑ በሎሳንጀለሱ ስብሰባ የእስክንድር  ስም በመነሳቱ ጋዜጠኛዋን ዘለፉ!!!
ወንድወሰን ተክሉ
የዶ/ር አቢይ የአእምሮ ውጤት የሆነውን  በዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የሚመራው ኢዜማ በሰሜን አሜሪካ ሎሳንጀለስ ባደረገው የመጀመሪያ የህዝብ ለህዝብ ስብሰባ ላይ የድርጅቱ መሪ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ ጥያቄ ላቀረበችላቸው ታዳሚና ጋዜጠኛ ሰብለወንጌል «ይህ የፌስ ቡክ ጫጫታ ነው፡እስክንድር አንድሺህ ሰው ሰብስቦ የባለአደራ ምክርቤት ነኝ ሊል አይችልም!»በሚል ዝልፊያ ቀመስ ንግግር ጋዜጠኛዋን ማሸማቀቃቸውን በስፍራው ተሳታፊ ከነበሩት ከእነ ቶሎሳ ኢብሳና ከራሷም ከጋዜጠኛዋ አንደበት ለመስማት ችያለሁ፡፡
በስብሰባው ላይ አንዳችም ቀረጻ እንዳይካሄድ ከማገዳቸውም በላይ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ለሴት ልጅ መሰጠት የሚገባውን ክብር በመንፈግ ጋዜጠኛዋን ከማመናጨቃቸውም በላይ የቀረጸችውንም እንድትሰርዝ አስገድደዋታል ሲልም ቶሎሳ ተናግሯል፡፡
በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ ለቀረበላቸው ጥያቄ መመለስ የተሳናቸው የኢዜማ አመራሮች ጥያቄውን ባቀረበው ላይ የማጣጣልና የማመናጨቅ ተግባር እንደፈጸሙ ቶሎሳ ገልጾ በተለይም እስክንድር ነጋ ላይ ያወረዱት ውርጅቢኝ ዶ/ር ብርሃኑን በርቀት ለሚያውቅ የሚያስደነግጥና ከእሳቸውም ስብእና እማይጠበቅ ነው ሲል ቶሎሳ ኢብሳ ገልጿል፡፡
የኢዜማ ቃለ አቀባይ ሆኖ ስለድርጅቱ እንዲያብራራ በስብሰባው ላይ የታደመው ናትናኤል ለቀረበለት ጥያቄ ከባድ ነው በማለት ሳይመልስ ያለፈ መሆኑን የገለጸው ቶሎሳ የግንቦት ሰባት ቃለአቀባይ የተባለውን አበበ ቦጋለን ዘርፈ ብዙ አፍራሽ ተግባራቶቹንና አገላለጹን ጠቅሶ የዛሬውም ኢዜማ የባሰ እንጂ የተሻለ ቃለአቀባይ ይዞ አለመምጣቱን በሎሳንጀለስ አይተናል ሲል ቶሎሳ ይናገራል፡፡
በሴትነቴና በኢትዮጵያዊነቴ አልተከበርኩም ያለችን ጋዜጠኛ ሰብለወንጌል በስብሰባው ላይ ያየሁት አምባገነንነትና እኛ የምንላችሁን ብቻ ስሙን ነው እንጂ ለሚቀርብላቸው ጥያቄ ለመመለስ የሚተባበሩ አይደሉም ስትል ትገልጽና ለእኔ በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ ከገዢው መንግስት ጋር አቻ ተመሳሳይ አቋም የያዘን ድርጅት ተቃዋሚ ብዬ መጥራቱ ይከብደኛል ስትል ገልጻለች፡፡
ድርጅቱ በዲሲና በተለያዩ ከተሞችም ዝግ ስብሰባ ለማካሄድ እንዳቀደ ማወቅ ተችሏል፡፡
Filed in: Amharic