>
5:13 pm - Saturday April 18, 9987

ጠ/ሚሩ በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ካነሷቸው ነጥቦች...!!! (ኤልያስ መሰረት)

ጠ/ሚሩ በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ካነሷቸው ነጥቦች…!!!
.ኤልያስ መሰረት ከስፍራው 
 
– ስለ ጄነራል ሰአረ መኮንን ገዳይ: ወታደሩ (ጠባቂው) አሁን በህክምና ላይ ይገኛል፣ አንገቱ ላይ ቆስሏል። ከሱ ጋር ግንኙነት የነበራቸው ተይዘዋል። ጥቃቱ የተፈፀመ ቅፅበት “(ጥቃቱ ሲፈፀም) ደውለህ ትነግረኛለህ” ብሎ ነገሮት በሁዋላ ደውሎ የነገረው ተይዟል።
– የሰኔ 15ቱን ሁኔታ አቅልሎ ማየት ልክ አይደለም። እንቅስቃሴ ሲደረግ የነበረው ተጨማሪ ጀነራሎችን ጭምር ለመግደል እንደነበር መረጃ ደርሶናል።
– እኔ በፊት የተለየ የህዝብ ተቀባይነት የነበረኝ፣ አሁን ደሞ የተለየ ተቀባይነት የሌለኝ ነበርኩ ብዬ አላስብም። ተቀባይነቱ ቀነሰ የሚሉ ምን መረጃ ኖሯቸው እንደሆነ አላውቅም።
– የዲያስፖራ ትረስት ፈንድ ገንዘብ አሰባሰብ እኔን ከመደገፍ እና ካለመደገፍ ጋር መያያዝ የለበትም። ሆኖም ከነበረ መሆን አልነበረበትም።
– በሰብአዊ መብት አያያዝ ዙርያ: አሁን ጭለማ ቤት ታስሮ ያለ የለም፣ ሰው አይገረፍም፣ ጥፍር አይነቀልም።
-ምርጫ: በኢህአዴግ ዘንድ ምርጫው አይደረግ የሚል አንድምታ የለም። ምርጫው ይካሄዳል ብለን እየተዘጋጀን ነው።
– ኢንተርኔት መዘጋት: መዘጋቱ ያስፈለገው የሰዎችን ህይወት እና ንብረት ከጥቃት ለማትረፍ ነው። ኢንተርኔት ውሀ ወይም አየር አይደለም። ለመዝጋት ምክንያት የሆኑንን ምክንያቶች ካልፈታን ለሳምንት ሳይሆን እስከ ወዲያኛው ሊዘጋ ይችላል።
– አሜሪካ ኤምባሲ ለፕሬዝደንት ፅህፈት ቤትነት ተገንብቶ የነበረው ህንፃ ለሰላም እና እርቅ ኮሚሽን ቢሮ ሆኗል።
– መከላከያ ትልቅ እና ውብ ህንፃ እየገነባ ነው፣ በቅርቡ ይጠናቀቃል።
– INSAም የራሱን ህንፃ ቦሌ መድሀኒአለም አካባቢ እየሰራ ነው። ሁሉንም በመጪው አመት ለመጨረስ ታስቧል።
– ኢህአዴግ ምርጫው ጊዜውን ጠብቆ እንዲካሄድ አቋም አለው –
የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ሀገራዊ ምርጫው ጊዜውን ጠብቆ እንዲካሄድ አቋም አለው
– በአሁኑ ወቅት ምርጫ ይራዘም የሚሉ እና ወቅቱን ጠብቆ ይካሄድ የሚሉ የራሳቸው ምክንያት ያላቸው አካላት እንዳሉ አንስተዋል።
ነገር ግን የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባደረገው ስብሰባው ምርጫ ከማካሄድ ጋር በተያያዘ በዝርዝር እንደተወያየበትና ምርጫው አይደረግም የሚል አቋም እንደሌለው አስታውቀዋል።
ኢህአዴግ ምርጫው ጊዜውን ጠብቆ እንዲካሄድ አቋም አለው ለዚህም በቂ ዝግጅት እያደረገ ነው።
ይሁን እንጂ ኢህአዴግ ምርጫው ይካሄድ የሚለው ላይ ብቻውን ውሳኔ ማሳለፍ አይችልም ያሉ ሲሆን፥ ሁሉን የፖለቲካ ፓርቲዎች በማሳተፍና በህዝቡ ይሁንታ የምርጫው ሁኔታ ላይ ከስምምነት በመድረስ እንደሚከናወንም አብራርተዋል።
ከዚህ ጋር አያይዘውም አዲስ የምርጫ ህግ እየተዘጋጀ መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ህጉ ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሚመለከታቸውን አካላት ባሳተፈ መልኩ መዘጋጀቱን አንስተዋል።
የህወሃትና አዴፓ መግለጫዎች
ሰሞኑን በህወሃትና በአዴፓ መካከል ባለው ፖለቲካዊ ጉዳይ ላይ ለቀረበላቸው ጥያቄም፥ ህወሃትና አዴፓ በየፊናቸው ያወጡት መግለጫ በፖለቲካው ዓለም የሚያጋጥም መሆኑን አንስተዋል።
ሁለቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለረጅም ዓመታት ለህዝብ ጥቅም ሲሉ አብረው ታግለዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክትር አብይ፥ በዚህ ሁሉ ጊዜ ውስጥ ግን እንዲህ አይነት ንትርኮች አልታጡም ብለዋል።
አሁንም በህወሃትና አዴፓ መካከል የተፈጠረው ነገር የሚያጋጥም መሆኑን በማንሳት፥ መግለጫው ግን በዚያ መንገድ ባይሆን ይመረጥ እንደነበረ አንስተዋል።
ነገር ግን ጥይት እስከሌለው ድረስ በፖለቲካ ውስጥ የሚፈጠሩ አለመግባባቶች አስደንጋጭ ሊሆኑ እንደማይገባም ነው ያስታወቁት።
በቀጣይም የመግለጫ ምልልሱን እንዴት እንፍታው የሚለው ላይ የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች ትኩረት ሰጥተውበት እድሚሰሩ ገልፀዋል።
የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች ሁለቱ ድርጅቶች ልዩነቶቻቸውን በውይይት እንዲፈቱ መድረክ እንደሚዘጋጅ አስታውቀዋል።
የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች ውህደትን በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፥ ውህደቱን በተመለከተ ጥናት ሲደረግበት እንደቆየ እና ወደፊትም ሰፋፊ ውይይቶች እንደሚካሄዱበት ጠቅሰዋል።
ከእህት ድርጅቶች ዘንድ ከውህደቱ በፊት መስተካከል አለባቸው በሚል የተነሱ ነጥቦች እንዳሉ በመጠቆም፤ ነገር ግን ውህደቱን መቀበል የማይፈልጉ ፓርቲዎች አሉ በሚል መውሰድ አይገባም ብለዋል።
ከሰብዓዊ መብት አያያዝ ጋር ተያይዞም ከዚህ ቀደም ከፍተኛ ተቀባይነት እንደነበረ አሁን ግን እየተሸረሸረ መጥቷል በሚለው ለቀረበላቸው ጥያቄም፥ ተቀባይነት እንደነበረ አሁን ግን እየተሸረሸረ መጥቷል በሚለው በማስረጃ የተደገፈ አይደለም ብለዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ እንደማሳያ መቅረብ እንደሌለበትና፤ ዳያስፖራው ለሀገሩ ሲል ትረስት ፈንዱን መደገፍ እንዳለበት ተናግረዋል።
አሁንም ቢሆን ከሰብአዊ መብት አያያዘ ጋር ከለውጡ ወዲህ ወደኋላ የተመለሰ ነገር እንደሌለና እሳቸውም ይሁን ሀገርን የሚመራው ድርጅት በሰብአዊ መብት አያያዝ ላይ ተመሳሳይ አቋም እንዳላቸው ገልፀዋል።
ከህግ ማስከበር ጋር ተያይዞ ሁሉም ህግ ይከበር ይላል እንጂ የራሱን ወንጀለኛ አሳልፎ ለመስጠት ፍቃደኛ አይደለም ያሉ ሲሆን፥ በአሁኑ ወቅት ህግ ይከበር በሚል የሚነሱ ቅሬታዎች እንደ ቂም መወጣጫ እየተቆጠሩ መምጣታቸውን አንስተዋል።
ይሁን እንጂ መንግስት ህግ መከበር አለበት የሚል አቋም እንዳለው እና ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጠል አስታውቀዋል።
ከኢኮኖሚው አንፃርም በተለይም ከውጭ ምንዛሬ አንፃር በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከዚህ በፊት ከነበሩ ዓመታት በተሻለ ገቢ መግባቱን በመጥቀስ፤ ነገር ግን የፍላጎት መጨመር ክፍተት ፈጥሮ እንደነበረ አስታውሰዋል።
በውጭ ምንዛሬ ረገድ የተሰራውን ስራ በማጠናከር ችግሮቹን መቅረፍ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም አስታውቀዋል።
የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ
የሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄን በተመለከተም፤ ክልል የመሆን ጥያቄው ለረጅም ዓመታት የነበረ መሆኑን እና ከለውጡ በኋላ ጎልቶ መውጣቱን አንስተዋል።
– የክልልነት ጥያቄው ከፖለቲካ በተጨማሪ የሀብት ክፍፍል እና ህጋዊ ሂደቶች ያስፈልጉታል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፥ የክልልነት ጥያቄውን መሰረት በማድረግ ህዝበ ውሳኔው ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እንደሚከናወንም አስገንዝበዋል።
– ከችግኝ ተከላ ጋር በተያያዘ ህዝቡን በድጋሚ በማመስገን በቀጣይም ህዝቡ በተከላው ያሳየውን ርብርብ ችግኞቹን ተንከባክቦ ማሳደግ ላይ እንዲደግመውም ጥሪ አቅርበዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ የችግኝ ተከላውን ለማስፈጸም የተቋቋመው አብይ ኮሚቴ የተተከሉ ችግኞችን የመከታተል ስራ እና ለቀጣይ ዓመት ችግኝ ተከላ ከወዲሁ ሰፋፊ የቅድመ ዝግጀት ስራዎችን ቀጥሎ እንደሚሰራም አስታውቀዋል።
Filed in: Amharic