>
5:13 pm - Sunday April 19, 1592

የኢትዮጵያ ትንታጎች ይነሡ! (ዶ/ር ዘላለም እሸቴ)

የኢትዮጵያ ትንታጎች ይነሡ!

ዶ/ር ዘላለም እሸቴ

ፖለቲካ ምድራዊ ነው። ሃይማኖት ሰማያዊ ነው። የምድሩን ማመስ አልበቃቸው ብለው፥ ተንጠራርተው ሰማይን መንካታቸው፥ እነርሱ ራሳቸው የሚበተኑበት ወቅት ጅማሬ መሆኑን ማን በነገራቸው? የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ከዓለም ካሉ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ (ሌላውን በውጭ ያሉትን ኦርቶዶክስን ጨምሮ) ለየት ያለ ነው። በዚህ ዘመን በኢትዮጵያ ውስጥ በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በጥቅም ላይ የሚውለውን የግዕዝን ቋንቋ በመጠቀም፥ በግዕዝ ቅዳሴ ከመጀመሪያው አንስቶ እስከ ዛሬ በመጠበቅ፥ የተለያየ ቋንቋ ያላቸውን ኢትዮጵያዊያንን በእኩልነት ባማከለ መንገድ ማገልገል የቻለች፥ በምንም የማትቀያየርና የማትለዋወጥ አዕማድ የሆነች ቤተክርስቲያን ናት። ከዓለም ብቸኛ የሆነች ይህች ቤተክርስቲያን ታቦትን በቤተክርስቲያን ውስጥ፥ ደግሞም ታቦትን እያወጣች (እያነገሰች) የምትገኝ፥ ለዓለም “ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች” የሚለውን የተስፋ ቃል የሚያስረግጥ፥ የቃል ኪዳን ሀገር መሆኗን ለፍጥረት ሁሉ በአደባባይ የምታውጅ ናት። ኦርቶዶክስ እንደ እኔ ላሉ የወንጌላውያን እምነት ተከታዮች እንደ እናት ቤተክርስቲያናችን የምትታይ ብቻ ሳትሆን፥ ለኢትዮጵያ ሀገር እንደ እናት ሆና በፀሎት የምትማልድ የኢትዮጵያ ስጦታ ናት።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የማንም ጥብቅና አያስፈልጋትም። የነካት ከመሠረታት አምላክ ጋር ይጋፈጣልና ተውት።

ኢትዮጵያዊነትን ለማለምለም ትንታጎች መነሳታቸው የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። ታዲያ እነዚህን የኢትዮጵያዊነት መልክተኛ ሆነው የሚንቀሳቀሱትን ለማዳከምና ተስፋ ለማስቆረጥ የሚሮጡ ካሉ እግዚአብሔር ይታረቀቻው።

አንዳንድ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ነን የሚሉ ወደ ልባቸው ተመልሰው፥ እነርሱ ባያውቁትም ያከበረቻቸውን ኢትዮጵያን ቢያቅፉና ለኢትዮጵያዊነት ልምላሜ ደፋ ቀና ቢሉ፥ ለሂስና ለትችት አይጋለጡም ነበር። ሰውን የምንቃወመው ለመግደልና ለማጥፋት ሳይሆን ለመመለስ ነው። ፅንፈኞችንና አክራሪ ዋልታ ረገጦችን የምንቃወመው፥ ኢትዮጵያን ከማፍረስ ሙሉ ለሙሉ ታቅበው፥ ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለኢትዮጵያዊነት ግንባታ ጉዞ እስኪጀምሩ ድረስ ነው። ከመካከላችን ለዘላለም ጠላታችን የሆነው ሥጋና ደም የሌለው ሰይጣን ብቻ ነው። ከዚያ በተረፈ ሁላችንም የወንድማችን ጠባቂ መሆን ይገባናል።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!

ኢሜል፥ Z@myEthiopia.com

Filed in: Amharic