>

የጃዋርና የቄሮን ነገር ጠቅላዩ ምን ያድርግ? (ሌሎችንስ?) (ሙክታሮቪች)

የጃዋርና የቄሮን ነገር ጠቅላዩ ምን ያድርግ? (ሌሎችንስ?)
(ሙክታሮቪች) 
ለውጡን ተከትሎ የህግ የበላይነትን ወዲያው የማስከበር ሂደት ውስጥ እንዳንገባ ያገደንና ያዘናጋን ወደ መንግስትነት የመጡ አካላት የሚጠቀሙበት የቃላት አጠቃቀም ህገወጥነትን እና አመፃን የሚታገስና ሰላማዊነትን እና ህግ ማስከበርን የማያበረታታ መሆኑ ነው። አሁንም ይስተዋላል።
“ሆደ ሰፊነት”
“የለውጥና የሽግግር አውዱን ለማስፋት”
“ለዘመናት የታፈነ ቤት በነፃነት ሲከፈት ሽታ ይኖረዋል”
“የለውጡ ባለቤት የሆነው ቄሮ፣ ለውጡን በንቃት ከመቀልበስ ይጠብቅ”
“በወንድማማች መካከል መገዳደል ሳይኖር በእርቅና በሽምግልና ጉዳዩን እንይዘዋለን”
“ምንም ጋዜጠኛና ፖለቲከኛ ያልታሰረባት ሀገር”
“የፀጥታ ሀይሎች ከቄሮ ጋር አብረው እጅለጅ ተያይዘው (ደሮ ከህዝቡ ጋ ይባል ነበር አሁን ሚናው ለወጣቶች ተሰጠና አረፈው)
“ፀጉረ ልውጥን ወጣቶች ነቅተው እንዲጠብቁ (የፀጥታ ማስከበር ሚናን ከፖሊስና የፀጥታ ሀይሎች ወደ ወጣት የለውጥ ጠባቂዎች ያለአዋጅ መሸጋገሩ”
ስርዓቱን ለመጣል የመንግስትን የቢሮክራሲ አሰራርና ተቋማትን መጠቀም በወቅቱ አስፈላጊ የነበረ ቢሆን እንኳ ወዲያው ተቋማቱን በፍጥነት መልሶ በማደራጀት ሚናቸውን የሚወጡበትን መንገድ ማበጀት ይገባ ነበር።
የፀጥታ አካላትን እና ተቋማቸውን ማዳከም ፍርድቤቶችና ማረሚያ ቤቶችን ማዳከምን ስላመጣ በተለይ ባንዳንድ ኦሮሚያ ዞኖች ፍፁም ህገወጥነትና የመንጋ ፍርድ ሊስተዋል ችሏል።
በቅርቡ በነበረው ጃዋር ለምን ተነካብን ቁጣ በሀረርጌ በፖሊስ ጣብያ የተጠለለ ሰው ወጣቶች አውጥተው መግደላቸው የተቋማቱ መሽመድመድን በሚገባ የሚያሳይ አብሪ የማንቂያ ደውል ነው።
የዶክ አብይ መንግስት ከምርጫ በፊት ተቋማትን መልሶ በሚገባ ለማደራጀት የሚከተለውን እርምጃ መውሰድ አለበት።
• ወጣቶች በህቡዕ መደራጀታቸውን በህግ በመከልከል የቄሮን የወጣት እንቅስቃሴ በመደበኛ የህግ ማዕቀፍ ስር በማደራጀት፣ ህግና ደንብን የሚከተል መሪዎቹ በይፋ የሚታወቁ የሲቪክ ማህበር፣ አልያም ወደ ስልጣን የመምጣት ፍላጎት ካለም አዲስ የፖለቲካ ድርጅት ወይም አሁን ባሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ስር በመታቀፍ የሚንቀሳቀስ በህግ ጥላ ስር ማድረግ ይገባዋል።
• እንደ ጃዋር ያሉ ሚናቸው በግልፅ ያልተለዩ ግለሰቦችን ሃይ የሚያስብል አሰራር መዘርጋት አለበት። ጥምር ዜግነት በማትፈቅድ ሀገር ውስጥ የውጭ ዜጋ ሆኖ በሀገር ውስጥ ፖለቲካ በዚህ ደረጃ የሚዲያ ባለቤት በመሆን አድራጊ ፈጣሪ፣ ትዕዛዝ ሰጪና ከልካይ፣ አባል ያልሆነበት ፓርቲ በሚያካሂደው የውህደትም ሆነ የመፈንዳት ውሳኔ ላይ እንደ አንድ ፖለቲከኛ አስተያየት ከመስጠት አልፎ ህዝብን አላግባብ ማነሳሳትና ለአመፅ ማሰናዳት እንደማይችል ቀጭን ትዕዛዝ ማስተላለፍ።
 የዜግነት ጉዳይን በተመለከተም በዲፕሎማሲ ከአሜሪካ ጋ በመጨረስ ይህን መሸሸጊያ ካባ በማስወለቅ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ እንዲንቀሳቀስ ማድረግ። “ትሰሙኛላችሁ ቄሮ!” እያለ መልዕክት የሚያስተላልፍለት አካል ለሚወስደው እያንዳንዱ ህገወጥ ተግባር በህግ ተጠያቂ የሚሆንበትን አግባብ በማፅናት ሀገርን በሰከነ መንገድ ወደ ሰላማዊ ምርጫ መምራት ያስፈልጋል።
ከላይ የገለፅኩት ለቄሮና ለጃዋር በምሳሌነቱ እንጂ በነሱ ላይ ብቻ ትኩረት እንዲደረግ አይደለም። ኤጀቶ፣ ፋኖና ዘርማ እየተባሉ የሚንቀሳቀሱ ሁሉ በህግ ጥላስር ተጠያቂነትና ሀላፊነት ባለበት ድርጅት ይሰባሰቡ ወይ እንዲበተኑ የሚያደርግ አስቾካይ ህግ ያስፈልጋል።
በሀገሪቱ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ሌሎች ጋዜጠኞች፣ አክቲቪስቶች፣ የፖለቲካ አመራርና ታዋቂ ሰዎችን የሚዲያ እንቅስቃሴ ላይ የሚድያ ህግ፣ የፀረጥላቻ ንግግር ህግና የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ህግ ደርጅቶ እስኪወጣ የሽግግር ጊዜ ህግን በአስቸኳይ በማውጣት ሀገርን ማረጋጋት እጅግ አስፈላጊ ነው።
Filed in: Amharic