>

ያመነችው ፈረስ በደንደስ የጣላት ህወሃት!መጨረሻዋ ምን ይሆን?!? (መስከረም አበራ)

ያመነችው ፈረስ በደንደስ የጣላት ህወሃት!መጨረሻዋ ምን ይሆን?!?

መስከረም አበራ
የህወሃት አልከስምም ማለት የኦነግን ትጥቅ አልፈታም ማለት ያስታውሰኛል፣የኦነግ ትጥቅ አልፈታም ማለት የሲሳይ አጌናን ትንታኔ ለመጀመሪያ ጊዜ “Seriously wrong” ነገር እንደገጠመው የተረዳሁበትን ቀን ያስታውሰኛል? በዛው ይቀጥላል ብዬ ግን አላሰብኩም ነበር :)…..ይሄ ትጥቅ አልፈታም ዶክተር ኢንጅነር የተባለ አስማት ቀላጅ ፌስቡከር ስለ ትጥቅ መፍታት የቀለዳትን እርጉም ቀልድም ያስታውሰኛል።
ህወሃት አብዮታዊ ዲሞክራሲ ትጥቋ ነው -የማትፈታው!እሱን የፈታች ዕለት እንደ ሳምሶም ፀጉሯን የተላጨች ይመስላታል። ስለዚህ አልከስምም፣የማልከስመው ደሞ ጠቅላላ ጉባኤ ስላልጠራሁ ነው ፣የተቀሩት ፓርቲዎች አከሳሰማቸው መርህ ያተከተለ ስላልሆነ ነው፣የማልከስመው ፌደራሊዝሙን ለማን ጥዬ ብዬ ነው ትበል እንጅ ዋናው ምክንያቷ ስልጣኗን አስራበት የነበረው የነተበው አብዮታዊ ዲሞክራሲ መመሪያ ባለመደረጉ፣እሷም ሶስት አባል አምስት አጋር ፓርቲዎች ሽር ብትን እያሉ ሲላላኳት የነበረው ዘመን ውል እያላት፣”ደጉ ዘመን ምነው አይመጣ?” በሚል  ነው።
 የሆነው ሁሉ የሆነው በህልሟ ይሁን በእውኗ የሚለውም ትንሽ ሳያደናግራት አልቀረም። የዚህ ምልክቱ የጌታቸው ረዳ መላ ቅዱሱ የጠፋ መዘላበድ፣የደፂ ሃምሌ ሲጋመስ የመሰለ ፊት፣የአዲስአለም ባሌማ እንባ ያነቀው ገፅታ፣የኬሪያት መንቆራጠጥ፣የሞንጆሪኖ ጥርስ ማፋጨት፣የአባይ ነፍሶ አንጋጦ መቅረት ወዘተ ነው።
አሁን ደሞ  የፌደራሊስት ሃይሎችን ሰብስቤ እንደ አቅሚቲ ሁለተኛ የበላይነት ሙከራ ላድርግ አይነት ነገር ጀምራለች ክርስቲያን ባትመስለኝም ተስፋ የማትቆርጠዋ ህወሃት። ያለውንም የሞተውንም አጠረቃቅማ እንደ ምንም 139 ፓርቲ (?) አድርሳ ” 500 ብር የቀን አበል እከፍላለሁ በሞቴ መቀሌ ድረሱልኝ” ስትል ስብሳቦ ጠርታለች።እነዚህ አካላት ግራ በመጋባት ህወሃትን ሳይበልጧት አይቀሩም።የጥሪው ደብዳቤ ሲደርሳቸው “የሞተ እንትን ወደመሰልኩ እኔ ህወሃት ትመለከት ዘንድ ከቶ እኔ ማን ነኝ ሳይሉ ይቀራሉ?”
“ችግር ነው ጌትነት” የሚለው:) ተረት እንደ ህወሃት የደረሰበት የለም።የኖረችበት ጌትነት በእኩልነት ቦታ ለመቀመጥ በጄ አላላትም! ያመነችው ፈረስ በደንደስ የጣላት፣ጌትነቷ መቅረቱን ባሰበች ጊዜ እርር ብላ የምታለቅስ ቆዛሚ የድሮ ጌታ  የድሮውን እያሰበች ዛሬን የጠላች መናኝ – ህወሃት!መጨረሻዋ ምን ይሆን?
አሁን አሁን የእብድ ገበያ እየመሰለኝ ያለው post-TPLF የተቃውሞው ጎራስ እንዴት ነው?ደህና ነው? እኔ ብቻ ነኝ በዚህ ጎራ Eventful ነት ግራ ተጋብቼ ዝም ያልኩት? መጨረሻችንን ያብጀው!
Filed in: Amharic