>

የታገቱ  እህቶቻችን  እና አክራሪ ብሄርተኞች (ዶ¦ር በቃሉ አጥናፉ ታዬ)

የታገቱ  እህቶቻችን  እና አክራሪ ብሄርተኞች

 

ዶ¦ር በቃሉ አጥናፉ ታዬ

ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ

 

በአንድ ሉዓላዊት አገር ላይ አጋች ኃይል አቅም ፈጥሮ ዜጎችን ማገት ከቻል የአገሪቱን የመከላከያ አቅም ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ጉዳይ ነው፡፡ የአጋች-ታጋች ክስተት አብዛኛውን ጊዜ የጨነገፉ አገራት መገለጫ ባህሪ ነው፡፡  ዳሩ ግን በእኛ አገር የሴት እህቶቻችን የዜግነት መብት ተገፎ በአጋቾች ስር ለሁለት ወራት ያህል መቆየታቸው የመንግስትንም ሆነ የመከላከያ አቅምን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ጉዳይ ሳይሆን ሸፍጥ የተሞላበትን የፖለቲካ ሂደት አመልካች ነው፡፡

የኢትዬጲያ ሰራዊት በዓለም አቀፍ የሰላም አስከባሪ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ኃይል እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ታዲያ ይህ ሰራዊት በተወሰኑ አክራሪ ብሄርተኞች የተያዙትን እህቶች ለማስለቀቅ አቅም ያንሰዋል ብሎ መገመት የኢትዬጲያ የተንኮል ፖለቲካ ካለመረዳት የሚመነጭ እሳቤ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ በይበልጥ የሚመለከታቸው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት እና የፌዴራል መንግስቱ መንግስታዊ ተቋማት (የመከላከያ ሚኒስቴር መ/ቤት፤ የፍትህ ሚኒስቴር) በጎሳ ፖለቲካ ጥብቆ ተኮትኩተው ያደጉ ስለሆን ብሄርን እንጅ ሰብዓዊነትን አያውቁም፡፡ አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ የሚለው ብሂል ለዚህ ጉዳይ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት እና በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ውስጥ የሚገኘው የደንቢደሎ ዩኒቨርስቲ ኃላፊዎች ጉዳዩን እንደማያውቁት ሲገልፁ ሲሰማ ደግሞ በእኛ እና በነሱ የፖለቲካ ፅንፈኝነት ተጠልፈው ሰብዓዊነት ክዶዓቸው፣ ዕውነት ከአዕምሮዓቸው እንደፈረጠጠች እንረዳለን፡፡ 

ከረጅም ጊዜ ዝምታ በኃላ  የፌዴራል መንግስቱ ወይም የጠቅላይ ሚኒስቴሩ ፕረስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን በሚዲያ ቀርበው ታጋቾች ተፈተዋል ብለው ስለቦታው ክብር ሳይጠነቀቁ ሲዋሹ ስንሰማ የስርዓቱ አስከፊነት እስከ አጥንታችን ዘልቆ ይሰማናል፡፡  

ይህ በእንዲህ እንዳለ  የኢትዬጲያው የአጋች-ታጋች ሰቆቃ የዓለም አቀፍ የዘገባ ሽፋን እንዳያገኝ ጉዳዩን ለመሸፋፈን የሚደረገው ጥረት እጅጉን ያሳዝናል፡፡ እ.ኤ.አ.በ2014 በናይጀሪያ ፅንፈኛው የቦኩ-ሀራም ቡድን የታገቱትን ተማሪ ልጃገረዶች ለማስለቀቅ አለም አቀፍ ማህበረሰቡ ሰፊ ርብርብ አድርጎ ነበር፡፡ የኦባማ ባለቤት ሚሸን ኦባማም በሴት ልጆች ላይ የተካሄደውን ግፍ አውግዛ ነበር፡፡ ኢትዬጲያዊ ሴት ባለስልጣናት ምነው አፋችሁ ተለጎመ? ርዕሰ- ብሄርዋ ሴት ናቸው፣ የፍ/ቤት ፕረዘዳንትዋ ሴት ናቸው፣የሰላም ሚኒስቴሯ ሴት ናቸው)፣ ከ50% በላይ በሴቶች የተሞላ ካቢኔ እንዳለ ይታወቃል፤ ታዲያ ምነው ለነዚህ እህቶች መጮህ ተሳናችሁ? የእምነት ተቋማትስ የት ነው ያላችሁት? የተቃዋሚ ፓርቲዎችስ የት ገባችሁ? አዴፓስ እወክለዋለሁ የምትለውን አማራ ከማስጨረስ መቸ ነው የምትታቀበው? በርካታ አገር በቀል ሴት እና ወንድ ምሁራንስ የት ናችሁ? 

ከብሄር እና ከሀይማኖት ማንነታችን ይልቅ ሰብዓዊ ማንነታችን በልጦብን ለተጠቁ ዜጎች ድምፅ መሆን ካልቻልነ፣የዜጎቻችንን ህመም እንደ ራሳችን ህመም፣ ቁስላቸውን እንደ ቁስላችን ሊሰማን ካልቻለ፣ በታገቱት ሴት ተማሪዎችና በቤተሰቦቻቸው ቦታ ሁነን ስሜቱን መጋራት ካልችልን፣ ሰው የመሆናችን ሚስጥር የቱ ጋ ነው? 

ታጋች ሴት ተማሪዎችና ቤተሰቦቻቸው ክፉ ቀን ገጥሟው፣ ሰሚ ጀሮ አጥተው፣ ከደመና በታች ረዳት ርቋቸው፣ ለልባቸው ጥያቄ መልስ ተነፍጎዓቸው፣ የአንጀታቸውን ልቅሶ የሚያቋቁማቸው ጠፍቶ ግራ በተጋቡበት ጊዜ እንዴት ለድምፅ አልባዎች ድምፅ ለመሆን ቢያንስ እንዴት መጮህ አቃተን?   ወደድንም ጠላንም እንደ ሰው ማሰቡ ነው የሚሻለን፤ እባካችው ሁላችንም እንጩህ ድምጽ እንሁናቸው፡፡   

Filed in: Amharic