>

የዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የአፍ ወለምታ [ኤፍሬም ማዴቦ]

ባለፈዉ ሰሞን ቻይና አፍሪካ ዉስጥ ሰላሳ አመት በማይሞላ ግዜ ዉስጥ ያደረገችዉ የኤኮኖሚና የፖለቲካ መስፋፋት ያሳሰባቸዉ የአሜሪካዉ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ምነዉ ምን አድረግናችሁና ነዉ ፊታችሁን ያዞራችሁብን ብለዉ ለመጠየቅ በርከት ያሉ የአፍሪካ መሪዎችን ቤተ መንግስታቸዉ ድረስ ጋብዘዋቸዉ ነበር። በዚህ የሃሳብ ልዉዉጥ፤ ምክር፤ የእራት ግብዣና የዋሺንግተን ዲሲን ጉብኝት ባጠቃለለዉ የፕሬዚዳንት ኦባማ ድግስ ላይ በመልካም የዲሞክራሲ ጅምራቸዉ የሚወደሱት የጋናና የደቡብ አፍሪካን መሪዎች ጨምሮ እንመራሀለን የሚሉትን ህዝብ በየቀኑ የሚያስሩት፤ የሚደበድቡትና የሚገድሉት የወያኔ መሪዎችም ተገኝተዋል። በዚህ የመሪዎች ስብሰባ ላይ ጠ/ሚ ደሳለኝ ኃ/ማሪያምን አጅበዉ ከመጡት የወያኔ ሹማምንት አንዱ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ./ር ቴድሮስ አድሃኖም ነበሩ። ዶ/ር ቴድሮስ በዋሽንግተን ዲሲ ቆይታቸዉ ብዙዎቻችንን እየዋለ ሲያድር ደግሞ እራሳቸዉንም ግራ ያጋባ የሬድዮ ቃለ መጠይቅ ሰጥተዉ ነበር።

“በአፍ ይጠፉ በለፈለፉ” የአገራችን ባለቅኔዎች አፉ እንዳመጣለትና እንዳሻዉ የሚናገርን ሰዉ . . .  ዋ ተጠንቀቅ በአፍ የሚነገር ነገር ዋጋ ያስከፍላል ለማለት የተረቱት ተረት ነዉ።  አዎ! ባለቅኔዎቹ እዉነታቸዉን ነዉ።  የሚያዳምጡንን ሰዎች ለማስደሰት ስንል ብቻ አፋችን እንዳመጣ የባጥ የቆጡን የምንዘባርቅ ሰዎች የምንላቸዉ ነገሮች እኛዉ ዘንድ ዞረዉ መጥተዉ መጥፊያችን ሊሆኑ ይችላሉ። በቅርቡ ዋሺንግተን ዲሲ ብቅ ብለዉ የነበሩትን የኢትዮጵያ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖምን ያጋጠማቸዉ ይሄዉ በጋዛ አፍ ተናግሮ የመጥፋት ቅሌት ነበር። ዶ/ር ቴድሮስ እዚህ ዋሽንግተን ዲሲ ዉስጥ መንግስታቸዉ የሰራተኛ ደሞዝና የአየር ላይ ወጪ እየከፈለ በሚያስተዳድረዉ ሬድዮ አፋቸዉን ሞልተዉ የተናገሩትን ነገር አዲስ አበባ ተመልሰዉ በፌስ ቡካቸዉ በለቀቁት መልዕክት ለማስተባበል ቢሞክሩም ነገሩ “ከአፍ ከወጣ አፋፍ” ሆኖባቸዉ በስህተት ላይ ስህተት እየፈጸሙ ይገኛሉ።

ሬድዮ አገር ፍቅር በመባል ከሚታወቀዉ ሳምንታዊ ሬድዮ ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በእስር ላይ የሚገኙት የድምጻችን ይሰማ መሪዎች የአሜሪካ መንግስት ጓንታናሞ ዉስጥ ካሰራቸዉ የአልቃይዳ አባላት ጋር ግንኙነት እንዳላቸዉ ማረጋገጫ አግኝተናል ካሉ በኋላ የአሜሪካ መንግስት ይህንን ግኑኝነት አስመልክቶ የድምጻችን ይሰማ መሪዎችን ኢትዮጵያ ድረስ ሄዶ ለማነጋገር ለመንግስታቸዉ ጥያቄ እንዳቀረበ ተናግረዋል። ያልነገሩን ነገር ቢኖር የአሜሪካ መንግስት ባቀረበዉ ጥያቄ መሰረት ቃሊቲ ድረስ ሄዶ የድምጻችን ይሰማ መሪዎችን ማነጋገሩንና አለማነጋገሩን ብቻ ነዉ።

ዶ/ር ቴዎድሮስ ብቻ ሳይሆኑ እሳቸዉ በአባልነት የሚገኙበት ህወሃት የሚባዉ ድርጅት ሃያ ሦስት አመት ሙሉ እየዋሸ የዘለቀ ድርጅት ነዉና የዶ/ር ቴድሮስ ዉሸት ብዙም ላይገርመን ይችላል። ሆኖም ግን ዶ/ር ቴድሮስ ግማሽ ደቂቃ በማይሞላ ግዜ ዉስጥ ሁለት ቱባ ቱባ ዉሸቶችን ሲዋሹ “ከማንም ጋር አንወግንም፤ የቆምነዉ ለእዉነት ብቻ ነዉ” የሚለዉ የአገር ፍቅር ሬድዮ ጣቢያ አዘጋጅ ካለምንም ተከታይ የማብራሪያ ጥያቄ የዶ/ር ቴድሮስን ቆሞ የሚሄድ ዉሸት እንዳለ ተቀብሎ ጭራሽ ዶ/ር ቴድሮስን ማመስገኑ የወያኔ ስርዐት ዉሸትና ቅጥፈትአገር ዉስጥ ብቻ ሳይሆን በዉጭ አገሮችም ምን ያክል ህብረተሰባችንን አንደበከለ ያሳያል።

የኢትዮጵያን የእስልምና እምነት ተከታዮች ከአልቃይዳ ጋር ማገናኘት እነዚህ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ያነሱትን ህጋዊ የመብትና የነጻነት ጥያቄ ላለመመለስ የሚደረግ አጉል ዉጣ ዉረድ ከመሆኑ አልፎ ማንም ማየትና ማሰብ የሚችል ሰዉ የማይቀበለዉ ከንቱ ቅጥፈት ነዉ። ደግሞም ይብላኝ ለዶ/ር ቴድሮስ አፋቸዉን ላዳለጣቸዉ እንጂ ወጣቶቹ የድምጻችን ይሰማ መሪዎችኮ የጓንታናሞ አስር ቤት ሲከፈት ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት መፍጠር ቀርቶ አልቃይዳ የሚባል ነገር መኖሩን እንኳን ሰምተዉ የማያዉቁ አንድ ፍሬ ልጆች ነበሩ።

ሌላዉ የዶ/ር ቴድሮስ ትልቁ ዉሸት የአሜሪካ መንግስት ከአልቃይዳ ጋር  የነበራቸዉን ግንኙነት አስመልክቶ የድምጻችን ይሰማ መሪዎችን የታሰሩበት ቦታ ድረስ ሄዶ ላናግራቸዉ ብሎ ጠየቀን ማለታቸዉ ነዉ። እኔ እንደሚመስለኝ ዶ/ር ቴድሮስ አደስ አበባ ከገቡ በኋላ “ምን ነካኝ” ብለዉ ዉሸታቸዉን በፌስ ቡክ ገጻቸዉ ለማስተባበል የቸኮሉት ደጋግመዉ ወዳጃችን ነዉ ብለዉ በተናገሩት በአሜሪካ መንግስት ስም የዋሹት ዉሸት ከንክኗቸዉ ይመስለኛል፤ አለዚያማ ወያኔም ሆነ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ዶ/ር ቴድሮስ በዋሹ ቁጥር ዉሸታቸዉን የሚያስተባብሉ ቢሆን ኖሮ የወያኔ አገዛዝ መሪዎች ስራቸዉ እየዋሹ ማስተባበል ብቻ ይሆን ነበር።

የሚገርመዉ ዶ/ር ቴድሮስ ከአሜሪካ ተመልሰዉ አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ የመጀመሪያዉን አንድ ሳምንት ያሳለፉት አንድም አሜሪካ ዉስጥ የዋሹትን ዉሸት በማስተባበል ሌላ ግዜ ደግሞ ሌሎች አዳዲስ ዉሸቶችን በመዋሸት ነበር። በእርግጥም ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በየአገሩ የሚገኙትን አምባሳደሮቻቸዉን ሰብስበዉ የኢትዮጵያን ህዝብ ከት አድርጎ ያሳቀ ነጭ ዉሸት ዋሽተዋል። ለምሳሌ አሜሪካ ዉስጥ የህዳሴዉ ግድብ ቦንድ ሽያጭ እጅግ በጣም ዝቅተኛ መሆኑን ከተናገሩ በኋላ ምክንያቱን ሲገልጹ የአሜሪካ ህግ ለቦንድ ሽያጩ አመቺ አለመሆኑን ገልጸዉ ይህንን ለማሻሻል መንግስታቸዉ ከአሜሪካ መንግስት ጋር አብሮ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። መቼም ለራሱ አገር ይህ ነዉ ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል ህግ አዉጥቶ የማያወቀዉ እንቅልፋሙ የኢትዮጵያ ፓርላማ የአሜሪካንን መንግስት የሚገዛ ህግ ካላወጣ በቀር ዶ/ር ቴድሮስ አደራ የተጣለባቸዉን የቦንድ ሽያጭ እንዴት አሜሪካ ዉስጥ እንደሚወጡት ባላዉቅም መንግስታቸዉ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ባለበት ቦታ ሁሉ ሁሉ ቦንድ መሸጥ ያልቸለዉ የየአገሮቹ ህግ ችግር ፈጥሮበት ሳይሆን ለወገኖቹ መብትና ነጻነት የሚታገለዉ ኢትዮጵያዊ ወንድሞቼንና እህቶቼን እየገደላችሁ የምትሸጡልኝ ቦንድ ባፍንጫዬ ይዉጣ ብሎ እምቢ ስላላቸዉ ነዉ። ይህንን ደግሞ መዋሸት እንጂ እዉነትን ሸፍኖ ማስቀረት ያልቻሉት ዶ/ር ቴድሮስም ከተባበሩትዓረብኤምሬትስበስተቀርየሁሉምአገሮችየቦንድሽያጭእጅግ በጣም ደካማእንደነበር ለሰበሰቧቸዉ አምባሳደሮች ተናግረዋል፡፡

ከዶ/ር ቴድሮስ በፊትም ሆነ እሳቸዉ እያሉ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከትዉልድ አገሩ ርቆ የሚኖረዉን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ በጥቅማ ጥቅም እየደለለ ከአገዛዙ ጎን ለማሰለፍ ተደጋጋሚ ጥረቶችን አድርጓል። በተለይ የህዳሴዉን ግድብ ቦንድ ሽያጭና  የዕድገትና ትራንስፎርሜሺኑን ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ የወያኔ/ኢህአዴግ አገዛዝ ዳያስፖራዉን አንደ ከፍተኛ የዉጭ ምንዛሬ ምንጭ ተመልክቶት ነበር፤ ሆኖም አብዛኛዉ ዳያስፖራ ከአገዛዙ ጎን ተሰልፎ ከሚያገኘዉ ግዜያዊ ጥቅም ይልቅ ዘላቂ የሆነዉን የእናት አገሩን አንድነትና የወገኖቹን ፍትህ፤ ነጻነትና እኩልነት በመምረጡ የወያኔ/ኢህአዴግ አገዛዝ ከዳያስፖራዉ እዝቃለሁ ብሎ የተመኘዉ የዉጭ ምንዛሬ ህልም ሆኖ ቀርቷል።

ሌላዉ የወያኔ/ኢህአዴግ አገዛዝ ከፍተኛ በጀትና የሰዉ ኃይል መድቦ ዳያስፖራዉን ለማማለል በሙሉ ሀይሉ የተንቀሳቀሰበት አካባቢ ቢኖር የከተማ ቦታና ቤት ሽያጭ ዘመቻ ነዉ። በእርግጥ አንዳንድ ከህዝብና ከአገር ጥቅም ይልቅ የራሳቸዉን ጥቅም ያስቀደሙ የዳያስፖራዉ አባላት ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚካሄደዉን የመሬት ቅርምት በይፋ እየተቃወሙ የቅርምቱ ድግስ የእነሱን ቤት ሲያንኳኳ ግን በራቸዉን ወለል አድርገዉ ከፍተዉ የድግሱ ተሳታፊዎች ሆነዋል። አብዛኛዉ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ግን እናትና አባቴን እያፈናቀላችሁ የምትሰጡኝን መሬትም ሆነ ቤት አልፈልግም ብሎ በቦንድ ሽያጩ ላይ የወሰደዉን ጠንካራ አቋም በከተማ መሬትና ቤት ሽያጭ ላይም ደግሞታል። የወገኖቹን ነጻነትና ፍትህ ለማስከበር በህይወቱ የተወራረደዉን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የማያወላዉል አቋም ያልተረዱት ዶ/ር ቴድሮስ ግን ያንን የለመዱትን በጥቅማ ጥቅም የመደለል ሴራቸዉን አሁንም እንደቀጠሉበት ነዉ። ለምሳሌ ዳያስፖራዉ በመጪዉ አመት በሚደረገዉ የምርጫ ድራማ ላይ ያለዉን እይታ እንዲለዉጥ ለማድረግ ሲባል ብቻ 40 በ60 በሚባለውየቤቶችመርሃግብርየታቀፉየዲያስፖራ አባላት የከፈሉበት ቤት የ2007ቱ ምርጫ ከመጀመሩ በፊት በአስቸኳይ ተጠናቅቆ እንዲሰጣቸዉ ትዕዛዝ ተላልፏል። እዚህ ላይ አንድ እጅግ በጣም የገረመኝም ያሳዘነኝም ነገር ቢኖር በአንድ በኩል ግብር ከፋይ በሌላ በኩል ደግሞ ቤት አልባ የሆነዉና እነ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም 99.6% መረጠን የሚሉት አገር ዉስጥ የሚኖረዉ ኢትዮጵያዊ ተረስቶ ትርፍ ቤት ፈላጊዉ ዳያስፖራ ቅድሚያ እንዲሰጠዉ መደረጉ ነዉ።

ለመሆኑ ዶ/ር ቴድሮስና መንግስታቸዉ ሁሌም አክራሪዉ ዳያስፖራ እያሉ የሚያሙትን ማህበረስብ ወድደዉ ሊስሙት ነዉ ወይን ተጠግተዉ ሊያልቡት እንዲህ የተንሰፈሰፉለት? የዳያስፖራዉን አባት፤ እናት፤ ወንድምና እህት እያሰሩ፤ እየገደሉና የመብትና የነጻነት ጥያቄ የሚያነሳባቸዉን የዳያስፖራ አባል ደግሞ አገርህ አትገባም ብለዉ አገር እየነሱት እነሱ ግን የልመና ኮሮጇቸዉን ተሽክመዉ አሜሪካና አዉሮፓ እየመጡ አገርህን እናሳድግልሃለን ገንዘብ ስጠን ብለዉ የሚጠይቁት በማን አገር ማን ለሚጠቀምበት ልማት ነዉ? እነ ዶ/ር ቴድሮስ እነሱን ከመሰለ ፀረ ህዝብ አገዛዝ ጋር ተመሳጥረዉ የዳያስፖራዉን አባል በህገ ወጥ መንገድ አግተዉ እየደበደቡና መታሰሩን ሰምታ ልትጠይቀዉ የሄደችዉን እህቱን ተወልዳ ካደገችበትና እትብቷ ከተቀበረበት አገር በ24 ሰዐት ዉስጥ ዉጪ ብለዉ እያስገደዱ እንዴት ቢገምቱንና እንዴት ቢመለከቱን ነዉ ዞር ብለዉ እኛኑ ገንዘብ ስጡን ብለዉ የሚጠይቁን?

ዶ/ር ቴድሮስ ከአገር ፍቅር ሬድዮ ጋር ያደረጉትን ቃለ መጠይቅ ከማጠቃለላቸዉ በፊት ደጋግመዉ የተናገሩት ኢትዮጵያን ምን ያክል እንደሚወዱና ይህ የሚወዱት አገር ህዝብ በእድገት ወደ ፊት ከገፉ አገሮች ተርታ ተሰልፎ ማየት አንደሚቸኩሉ ነዉ። መልካም ምኞት ነዉ። ሆኖም ይህ ምኞት የዚያችን የሚወዷትን አገር ህዝብ ሲናገር አፉን እየዘጉ፤ ሲጽፍ እጁን እያሰሩ፤ ሃሳቡን ሲገልጽ ማዕከላዊ ወስደዉ ሰቅለዉ እየገረፉና  ሰላማዊ ሠልፍ ተሰልፎ መብቴንና ነጻነቴን አክብሩልኝ ብሎ የጠየቃቸዉን ደግሞ ደረቱንና ጭንቅላቱን በጥይት እያፈረሱ የሚሳካ ምኞት አይደለም።  ዶ/ር ቴድሮስ በአፋቸዉ ብቻ የሚናገሩት ምኞት ዳያስፖራዉ በአፉም በልቡም ዉስጥ ያለ፤ የነበረና ለወደፊትም የሚኖር ምኞት ነዉ። ምኞታችንና ምኞታቸዉ ገጥሞ ኢትዮጵያ አድጋና በልጽጋ የምናያት  ግን ዶ/ር ቴድሮስ  እኛም እንደሳቸዉ በአገራችን ጉዳይ እንደሚያገባን በዉል ሲረዱና ይህንን ሃያ ሦስት አመት ሙሉ በችንካር ቀርቅረዉ የዘጉብንን በር ወለል አድርገዉ ሲከፍቱ ብቻ ነዉ።

የኢትዮጵያ ትንሳኤ በልጆቿ መስዋዕትነት ይረጋገጣል!!!!

ebini23@yahoo.com

Filed in: Amharic