>
5:13 pm - Sunday April 20, 6330

ፓርላማው ቤተ ክርስቲያንን የሚያይበት መነፅር ወልቋል!!!  (አባይነህ ካሴ)

ፓርላማው ቤተ ክርስቲያንን የሚያይበት መነፅር ወልቋል!!! 

 

 

አባይነህ ካሴ
 
* ፓርላማው ውስጥ ኦርቶዶክስ ጠሉ በዝቷል
 
ፓርላማው የቤተ ክርስቲያን ሰው ያቃዠዋል
የዛሬዎቹ የፓርላማ አባላት አፈ ጉባኤያችሁ አባ ዱላ በፓስተር ቅባት ሲነከሩ የት ነበራችሁ? በፓርላማው ወንበር ውስጥ አባ ዱላ ገመዳ የሀገር ቤቶቹ አይረቡም ብለው ከውጭ ሀገር ድረስ ፓስተር አስመጥተው “አንብሮተ ዕዳ” ሲደረግላቸው ይህን ሁሉ አንደበት ማን ነበር የዘጋው?
የሦስቱ ከሳሾች ቃል በአጭሩ 
• አንደኛውን (ዲያቆን ዳንኤልን መኾኑ ነው) ካታጎሪካሊ እቃወማለሁ፡፡ . . . የሃይማኖት እኩልነትን የማያምኑ አንዱን ሃይማኖት በሌላው ላይ የሚቀሰቅሱ፡፡ እንደዚሁም በዜጎች መካከል ክፍፍል እንዲፈጠር የሚሠሩ ግለሰብ ናቸው፡፡
• አንድ በሃይማኖት ልዩነት የሚያምን በቪድዮም ይሁን በቀጥታ ሥርጭትም ጭምር ማኅበረሰባዊ ተጽዕኖ የሚፈጥር አካል የፕሬስ ድርጅት እንዲኾን በግሌ አልፈቅድም፡፡
• እነ ዳንኤል ክብረት አገር ሊበትኑ ነው ወይስ ሊያዋጉን ነው ወደ ሥልጣን እየመጡ ያሉት? የሚል ነው፡፡
አንቱ ኹለተኛው ከሳሽ መጀመሪያ ለፕሬስ ድርጅት የቦርድ አመራርነት እንጅ ለፕሬስ ድርጅትነት ዕጩ ኾኖ አልቀረበም፡፡ አጀንዳው ሳይገባዎት ለምን ጥላቻ ገፍቶዎት በስሜት ይቀዝፋሉ፡፡ ግዴለዎትም ዝቅ ብለው ይብረሩ፡፡ ሲቀጥል ከተቋሙ በላይ የሚገዝፍ ነውና ዳኒን በተቋምነት ማሰብዎ መጥፎ አይደለም፡፡
ሙሐዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረት ለቦርዱ አባልነት የተሰየመው ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም፡፡ አዎ እናንተ ጊዜ ዐይቶ ተናጋሪዎች  ያኔ የት ነበራችሁ?
ድራማውም እንደገና ይቆጠርልን አቤቱታውም አልሠራላችሁም፡፡ የድጋፍ ድምጹ ፻፵፮ (146) የነበረው ፻፵፰ (148) ኾኖ መጣ፡፡ በመቃወማችሁ ድምጹን ከፍ አረጋችሁት፡፡ አያችሁ በግፍ ስትቃወሙ ከእጃችሁ ነጥብ ትጥላላችሁ፡፡ ድምጻችሁ እየሰለለ ይሔዳል፡፡ ሦስተኛ ይቆጠር አለማለታችሁ በጀ እንጂ ጨምሮ ይመጣ ነበር፡፡ ስትቃወሙ የሚያድግ እንጅ የሚቀጭጭ ሰብእና የለውም፡፡ የመውጊያውን ብረት እንዲለው መጽሐፉ፡፡  የሰው አድባር ያውቃል፡፡ ለቀዳሚ ሙፍቲ ያሳየውን አክብሮት አንድ ጳጳስ ሲሳለም በሚያቀርበው አትሕቶ ርእስ መጠን እንደኾነ ፎቶው ይናገራል፡፡ እናንተ ግን አትመጥኑትም ታንሱበታላችሁ፡፡ ሹመታችሁም በዚያው ልክ ታናሽ ነው፡፡ እንኳንም አልሾማችሁት ! ታላቁ በታናሹ እንዴት ይሾማል?
ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የዐደባባይ ሰው ነው፡፡ በየጊዜው አቋሙን ሁሉ በገሃድ ሲያንጸባርቅ የኖረ፡፡ እናንተ ስትልጎመጎሙ ሮጣችሁ የምታነብቡት የእርሱን ጦማር እንደኾነ ታውቁታላችሁ፡፡ ሲገፋ የኖረ ሲገፉት እየጠነከረ የሚሔድ የአደባባይ ሰው ነው፡፡ ተደብቆ አልኖረም፡፡ ከተደበቃችሁበት ግን አወጣችሁ፡፡ እኛም ዐወቅናችሁ፡፡ መንፈሳዊ ሰው ያቃዣችኋል ማለት ነው፡፡ ፕርላማው የእኛ አለመኾኑንም በቻለው መጠን ነግሮናል፡፡ በዲያቆን ዳንኤል ላይ በር መዝጋት አይቻልም፡፡ በዚህ ሲዘጉበት በዚያ ከፍቶ ይወጣል፡፡ ይህንን ሲያስጥሉት ሌላ ይዞ ይነሣል፡፡ የአናብስት ጉድጓዱም የሰው ማደሪያውም ይመቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ያገኙ መስሏቸው ተረባረቡ። ሲያምራቸው  ይቅር!እንኳን እርሷን እርሱንም አላገኙት።
ግን በአንድ በኩል እናመሰግናችኋለን፡፡ በፊት ለፊት ለቤተ ክርስቲያን ያላችሁን ጥላቻ ስለተናገራችሁ፡፡ የምትቃወሙት ማን ሲኾን እንዳላየ የምታልፉት ማን ሲኾን እንደኾነ ነገራችሁን፡፡ ምርጫ ላይ እንገናኝ፡፡ ካልኩሌተራቸው የጠፋባቸው ሰዎች አብላጫ ድምፅ ምን እንደኾነ ጠፍቶባቸው እስካሁን መደመር መቀነስ እየሠሩ መኾናቸውም ታውቋል፡፡ ሒሳብ ተምራችሁ እስክትመጡ ብዙ ሠርቶ ይጠብቃችኋል እናንተ ግን አስቀድማችሁ ሒሳብ ተማሩ፡፡
Filed in: Amharic