>

ኢትዮጵያ ውስጥ በኮሮና ቫይረስ የተያዘ ሰው መገኘቱ ተረጋገጠ!!! (ዮናስ ሀጎስ)

ኢትዮጵያ ውስጥ በኮሮና ቫይረስ የተያዘ ሰው መገኘቱ ተረጋገጠ!!!

ዮናስ ሀጎስ
የጤና ሚንስትሯ ዶ/ር ልያ ታደሰ በሰጡት መግለጫ በቫይረሱ የተያዘ ሰው አዲስ አባ ውስጥ ተገኝቷል ብለዋል። የሚያሰጋ የጤና ችግርም እስካሁን አልታየበትም።  አፍሪካዊ ቀለም ያላቸውን እምብዛም አይዳፈርም የሚለውን /አዘናጊ እንዳይኾን እያሰብን/ እግዚአብሔር እውን እንዲያደርገው ከመጸለይ ጋር ጥንቃቄ እናድርግ።
የ፵፰ ዓመቱ ሰው ጃፖናዊ ሲኾን በመግለጫው መሠረት የመጣው ከቡርኪና ፋሶ መኾኑ ተረጋግጧል። አየር መንገዱ ማን ነው? አልተነገረም።  ግን ያው የፈረደበት መኾኑ ይታወቃል። ንክኪውን ዝውውሩን ማሰብ ነው እንግዲህ። ለማንኛውም የካ ኮተቤ ሆስፒታል ለሕክምናው አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጓልም ተብሏል።
፩ ማንኛውንም ነገር በእጅ ከነኩ ዐይን፣ አፍ እና አፍንጫዎን እንዳይነኩ መጠንቀቅ
፪ ቶሎ ብሎ እጅን ለ፳ /20/ ሰከንድ በሳሙና መታጠብ። ቢቻል በሙቅ ውኃ።
፫ ሲያስነጥሱ ቢቻል በሶፍት አለበለዚያ አፍና አፍንጫዎን በክናድዎ በውስጠኛው ሸፍነው ቢኾን ይመረጣል። ሶፍት ከተጠቀሙ ወደ ቆሻሻ ገንዳ መጣል።
፬ ከቤተ ክርስቲያን በስተቀር ሕዝብ በሚበዛበት አካባቢ አለማዘውተር።
፭  በሥራ ወይም በቤት በቂ አየር እንዲናፈስ ማድረግ
የመጀመሪያም የመጨረሻም ፈጣሪ በዓለም ላይ ያዘዘው መቅሰፍት ነውና አጥብቆ መጸለይ !
—                —-          —-
መንግስት ከሌሎች ሐገራት መንግሥታት ምን መኮረጅ ይችላል?
ኮቪድ_19
በመግለጫው ላይ የተሰማው የኢትዮጵያ መንግስት የቫይረሱን መዛመት ለመቆጣጠር እየሰራ ያለው የስራ ሂደት አስደሳች ነው። በበለጠ ደሞ ከታች የተጠቀሱት ነገሮች ላይ ብዙ ማሻሻያ በማድረግ ስርጭቱን በቀላሉ መቆጣጠር ይችላል ብዬ አምናለሁኝ።
1) 8335 ነፃ የስልክ መስመር መጨናነቅ ስለተፈጠረበት ተጨማሪ ነፃ የስልክ መስመሮች ማዘጋጀትና ስራ ላይ እንዲውሉ ማድረግ።
2) የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ወሳኝነት ባላቸው የፋርማሲቲዩካል ምርቶች ላይ ከዋጋ መተመን ጀምሮ ሙሉ በሙሉ የገበያ ቁጥጥር ማድረግና ይህን ተላልፈው የተገኙ ፋርማሲዎች ላይ ከባድ ቅጣት ለመጣል የሚያስችለው ረቂቅ ሕግ አዘጋጅቶ በፓርላማው ማስወሰን። በተለይ በአውቶቡስ የሚጓዙ ሰዎች ካለው መጨናነቅ የተነሳ የግድ ሰርጂካል ማስክ መጠቀም ስለሚኖርባቸው በዚሁ ቁስ ላይ ቢቻል መንግስት ሰብሲዳይዝ በማድረግ እጅግ በጣም በረከሰ ዋጋ ለሕዝቡ በራሽን መልክ ማቅረብ።
3) በጣም አስፈላጊ ከሆኑ ጉዳዮች በቀር ማናቸውንም ሕዝባዊ ስብሰባዎች ሙሉ ለሙሉ ማገድ።
4) በመንግስት መ/ቤቶች፣ የግል ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች፣ ማረምያ ቤቶችና ሌሎችም ሕዝብ በብዛት የሚገኝባቸው ቦታዎች ላይ ሰርኩላር አዘጋጅቶ በመበተን ከስራ ሰዓት፣ ከትምህርት ሰዓት ተቀንሶ ስለ ቫይረሱ ወቅታዊ መረጃ በሳምንት አንድ ጊዜ የሚነገርበት ቻናል መፍጠር።
5) በቦሌ ኢንተርናሽናል ኤርፖርት ካለው ቁጥጥር በተጨማሪ የመጡ መንገደኞች ሐገሪቷ ውስጥ እግራቸው ከረገጠበት ጊዜ ጀምሮ ለ14 ቀናት በየቀኑ አጠቃላይ እንቅስቃሴያቸውን ለግብረሐይሉ ሪፖርት የሚያደርጉበት ሲስተም አዘጋጅቶ ስራ ላይ ማዋል። ይህ በቀላሉ በሚዘጋጅ ዌብሳይት አሊያም የሞባይል አፕሊኬሽን ወይንም በአጭር የፅሁፍ መልዕክት ሊደረግ ይችላል። እንደ ጃፓናዊው ዓይነት ችግር ሲፈጠር ከየለቱ የእንቅስቃሴያቸው ሪፖርት በመነሳት በቀላሉ ከማን ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንደነበራቸው ለይቶ ወደ ስራ ለመግባት ይቀላል።
6) ከሩዋንዳ ልምድ በመውሰድ አዲስ አበባና አብዛኞቹ ከተሞች ያለውን የውኃ እጥረት ግንዛቤ ውስጥ ባስገባ መልኩ በተለያየ የአውቶቡስ ማዞርያዎች ላይና ሌሎች አደባባዮች ላይ የእጅ መታጠቢያ ጊዜያዊ ቁሳቁሶች ቢዘጋጁ…
እንግዲህ እኛ ባለንበት ሐገር ከሚደረጉ ጥንቃቄዎች ተነስተን ይህቺን ምክረ ሐሳብ ፅፈናል። እናንተ ደሞ የታያችሁን ጨምሩበት።
Filed in: Amharic