>
5:18 pm - Sunday June 14, 4950

ለራሱ ሃሳብና እምነት የታመነ ብእረኛ!!! (ይትባረክ ዋለልኝ)

ለራሱ ሃሳብና እምነት የታመነ ብእረኛ!!!

 

ይትባረክ ዋለልኝ
መቼም ከጥንት ጀምሮ በሃገራችን በሁሉም ሙያ ውስጥየሚገኙ ታላላቅ ባለሙያዎች በአብዛኛው ለታላቅነታቸው ያበቃቸውን ስራ የሰሩት በተመቻቸ ህይወት ውስጥ ሆነው  ሳይሆን የሰው ልጅ እኩይ ተግባር ያሳረፈባቸውን በርካታ መከራዎች ድል እየነሱ ነው::አንደንዶች ለእውነት :ለሰው ልጅ ህይወትና እድገት:ሰላምናፍቅር….ሲሉ ህይወትን የሚያህል ውድ ዋጋ ከፍለዋል::ሌሎች ለስደት ተዳርገዋል::ሌሎች ደግሞ የአካልና የስነ ልቡና ጉዳት ሰለባ ሆነዋል::ዛሬ በክብር ላነሳው የምፈልገው የኪነጥበብ ባለሙያ የጥበብ ስራዎች የሰራው ሐገሪቱ በሰጠችው ምቹ ሁኔታ ሳይሆን ለሐገሪቱ ባበረከተው መልካም ፍሬ ነው::
 ሰሞኑን ረጅም አመት በሃላ ብሔራዊ ቲአትር ላይ የአደዋን በዓል በማስመልከት በተሰራ ቲአትር ላይ ከነ ሚካኤል እና መአዛ ታከለ ጋር መድረክ ላይ ተመለከትኩት:: ደስ አለኝ:: ይህችንም ሃሳብ ለመጫር ምክንያትም ሆነኝ:: ይህ ሰው ሐገሩን የሚወድ ነው:: ለእውነት :ለፍቅር :ለፍትህና ለሰላም የላቀ ቦታ አለው::ልበስሱ ነው::ህይወቱን ሙሉ ለሚወደውና ለሚያከብረው ሙያ እየሰጠ ያለ ሰው ነው::
ሰለሞን አለሙ ይባላል:: ደራሲ : አዘጋጅና ተዋናይ ነው:: ብዙዎች በተለምዶ “አብዬ ዘርጋው ” እያሉ በሚጠሩት “ሸምጋይ” በተሰኝው ተከታታይ የሬዲዮ ድራማው ያውቁታል::የራሱ የአፃፃፍ ይትበሃል ( style)ያለው ፀሃፊ ነው::  በሰው ልጅ ማህበራዊ ህይወት ላይ አተኩሮ የሚፅፍ ታላቅና ጠንካራ ፀሐፊ ነው:: ሰለሞን ለ Virtue Ethics ለሰናይ ምግባርና ለስነምግባር የቆመ ነው::
ለራሱ ሃሳብና እምነት የታመነ ብእረኛ ነው:: የእኩይ ድርጊቶች ጠላት ነው::እውነት ብቻናት የብዕሩ ማዕከል:: ህይወቱ እውነት ናት:: ብእሩም ከህይወቱ የሚቀዱ ናቸው::
ሰለሞን በስራዎቹ ማህበራዊ ሃያሲ ደራሲ ነው ማለት እችላለሁ::በርካታ በህዝብ ክብርና ፍቅርን ያጎናጸፉ የጥበብ ስራዎች  አሉት:: ዛሬም በርካታ የቴሌቪዥንና የመድረክ ስራዎች አሉት::በሐምሌ 1983 ዓም በቤተሰብ መምሪያ የተገናኙት ሰለሞን እለሙ :ሰራዊት ፍቅሬ: አዜብ ወርቁ: ድርብወርቅ ሰይፋ:ፍሬህይወት መለሰ ሆነው በጋራ በከፈቱት “አፍለኛው”በተሰኘው የቲአትር ቡድን ውስጥ ሰለሞን በጻፉቸው በርካታ ድርሰቶች አማካኝነት ብዙ ሰርተዋል::
ሰለሞን አለሙ 500 የሬዲዮ ድራማዎችን ፅፎአል::እንደዛሬው ተከታታይ የቴሌቭዥን ድራማዎች በሌሉበት ዘመን 13 ተከታታይ የቴሌቭዥን ድራማዎችን ፅፎ አዘጋጅቷል::እንዲሁም 6 ቲእትሮችን ጽፏ አዘጋጅቷል ተውኗል ::በሌሎች ፀሃፊያን በተሰሩ የቴሌቪዥ ድራማዎችና ቲአትሮች ላይም ተውኗል:: ሰለሞን በርካታ መነባንቦችንም ለመድረክ አብቅቷል::በተለይ በእሁድ ረፋድ ላይ በኢትዬጵያ ሬዲዮ ለ70 ሳምንት ሲተላለፍ የቆየውና በመላው ኢትዮጵያን ዘንድ ተውዳጅ የነበረው ” ሽምጋይ” ወይም (አብዬ ዘርጋው) የተሰኘው የሬዲዬ ድራማው ዛሬ ድረስ በብዙ ኢትዬጵያዊያን የሚታወስ ድራማ ነው:: ሰራዊት ፍቅሬ: አዜብ ወርቁ: ድርብወርቅ ሰይፋ:ፍሬህይወት መለሰ የዚህ ድራማ ፈርጥ ጌጦች ነበሩ:: ሰለሞን ትላንትም ዛሬም ይፅፋል:: በርካታ የሬዲዮና የቴሌቪዥን እስክሪፕቶችና መነባንቦች አሉት:
  በመጨርሻም
    በሃገራችን በየጊዜው ለሚመጡ ለተለያዪ የፖለቲካ ስርዓቶች እንደጊዜው ሆነው ሙያቸውን ችሎታቸውን እውቀታቸውን የገበሩ እንዳሉ ሁሉ በአንፃሩ በርካታ ፀሃፊያን  ግን ባብዛኛው ከፖለቲከኞች ጋር መስራት የማይፈልጉ ብቻ ሳይሆን አምርረው ይቃወሟቸዋል:: ሰለሞን ዓለሙም ወደ ስርዓቱ መጠጋት ለእሱ የተሻለ ህይወት ሊያስገኝለት እንደሚችል ይህን መረዳት አልተሳነውም::ይህ ሰው ከፖለቲከኞች ጋር መጠጋት እንደ ሃገር ክህደት ስለሚያየው ይጠየፈዋል::ምክንያቱም ከስርዓቱ ጋር መስራት የሐግርንና የህዝብን መከራ በይበልጥ የሚያገዝፍ መሆኑን ስለሚረዳ ብቻ ሳይሆን ለስርዓቱ ክንድ መፈርጠም ተጨማሪ ሃይል መሆን ስለማይፈቅድ ነው:: በዚህ ሳቢያ ብዙ ተገፍቷል::ዛሬ ግን ስራዎቹን ወደአደባባይ ለማውጣት እየሰራ ነው:: ብዙዎችም ከእሱ ጋር ለመስራት በሩን እያንኳኩ ነው:: ብዙ ጊዜውን በስቱዲዮው ውስጥ በስራ ነው የምያሳልፈው::  ሶል ዛሬም ከበርካታ ወጣት ጸሐፍትና ተዋንያን ጋር ሆነህ ብዙ ስራዎች እንደምታሳየን እርግጠኛ ነኝ:: እግዚአብሔር ረጅም እድሜ ከጤና ጋር እንዲሰጥህ እመኝልሃለው::!!
Filed in: Amharic