>
5:14 pm - Friday April 20, 5325

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ!!!

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ!!!

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ አሜን፡፡
 
በአገራችን ኢትዮጵያ በገጠር፣ በከተማ እና በመላው ዓለም ለምትገኙ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን በሙሉ….
ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ
 
ወቅታዊ የሰው ልጅ ስጋት በመኾን በመላው ዓለም በፍጥነት በተስፋፋው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ዓለም አቀፍ ስጋት ስለ ተከሠተ፣ መንግሥታት አገርን ከጥፋት፣ ሕዝብን ከሞት ለመጠበቅ ዐዋጆችን እያወጡ ይገኛሉ፡፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን፣ ክቡር የኾነውን የሰው ልጅ ሕይወት ለመታደግ፣ እምነትንና ቀኖናን ጠብቃ ሃይማኖታዊ መመሪያ የመስጠት ሐዋርያዊ ሓላፊነት አለባት፡፡
ስለዚህ፣ ቋሚ ሲኖዶስ፣ የጉዳዩን አሳሳቢነት ከግምት ውስጥ በማስገባት መሠረተ እምነትንና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ጠብቆ ለኹሉም ካህናት እና ለሕዝበ እግዚአብሔር ደኅንነት ሲባል የሚከተሉትን መመሪያዎች አስተላልፏል፤
1. በሰሙነ ሕማማት እንደምናደርገው፣ የእርስ በርስ መሳሳም ቀርቶ ራስን ዝቅ በማድረግ፣ እጅ በመንሳት ወይም በእማኄ ሰላምታ በማቅረብ እንዲፈጸም፤
2. ወረርሽኙ በሰዎች መሰባሰብ የሚስፋፋ ስለኾነ ማናቸውም መንፈሳዊ ጉባኤያት፣ የትምህርት ክፍለ ጊዜያት፣ ወደ ገዳማት እና አድባራት የሚደረጉ ጉዞዎች እና ምእመናን የሚሳተፉባቸው ታላላቅ መርሐ ግብሮች ለጊዜው እንዲቋረጡ፤
3. ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲገባም ኾነ አስፈላጊ በኾነበት ጊዜ ኹሉ፣ እጆቻችንን በመታጠብ እና ዘርዘር ብሎ በመቆም ሥርዓተ አምልኮ እንዲፈጸም፤
4. ዓመታዊ የንግሥ ክብረ በዓላት በቅዳሴ እና በማሕሌት ታስበው ክብረ በዓላቱ በሌላ ጊዜ እንዲከበሩ፤
5. የጉንፋን ምልክት ያለባቸው ለሌሎች እንዳያስተላልፉ፣ በቤታቸው በጥንቃቄ ተለይተው በጸሎት እና በሕክምና እንዲቆዩ፣ ከቤተ ክርስቲያን የሚያስፈልጋቸውን መንፈሳዊ አገልግሎትም በልዩ ኹኔታ እንዲያገኙ፤
6. በቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ የተቋቋመው ኀይለ ግብር የተስፋ ልዑክ በመኾን፣ እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ድረስ ተደራጅቶ ተልእኮውን በአስቸኳይ እንዲጀምር፤
7. ሥርዓተ ቅዳሴን በተመለከተ፡-
• በቤተ መቅደስ ቀዳስያን በኾኑት ልዑካን ብቻ ሥርዓተ ቅዳሴው እንዲፈጸምና ሌሎች አገልጋዮች በቅድስቱ ዘርዘር ብለው በመቆም እንዲያገለግሉ፣
• በዕለቱ ለሚቆርቡ ምእመናን ለአረጋውያን፣ ለወጣቶች እና ለሕፃናት የፈረቃ ተራ በማዘጋጀት ቆራቢዎች ብቻ ወደ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ገብተው ዘርዘር ብለው በመቆም እንዲያስቀድሱ፣
• ሌሎች ምእመናን በዐጸደ ቤተ ክርስቲያን ቢያንስ ኹለት የትልቅ ሰው ርምጃ ያህል በመራራቅ ቆመው እንዲያስቀድሱ፣
• የቅዳሴ ጠበል በየግል መጠቀሚያ ምእመናን በየቆሙበት ቦታ በጥንቃቄ እንዲሰጥ፣
• ሌሎች ከቅዳሴ ጋራ የተያያዙ ዝርዝር የአፈጻጸም ጉዳዮችን ኀይለ ግብሩ አዘጋጅቶ በቅዱስ ሲኖዶስ በማጸደቅ ለአህጉረ ስብከት በሚልከው መመሪያ መሠረት ተግባራዊ እንዲደረግ፤
8. ከሥርዓተ ቅዳሴ በተጨማሪ እንደ ስብሐተ ነግሕ፣ ሰዓታት፣ ቁመተ ማሕሌት፣ ጥምቀተ ክርስትና፣ ጸሎተ ፍትሐት፣ የመሳሰሉ አገልግሎቶች ለሥርዓቱ በሚያስፈልገው ቁጥር ብቻ እና በውሱን ሊቃውንት በተራ እንዲፈጸም፤
9. ወረርሽኙ ከዓለም እንዲጠፋ፣ ካህናት ብቻ በቤተ መቅደስ፣ በዐውደ ምሕረት እና በዐጸደ ቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ጸሎተ ዕጣን በማድረስ ማዕጠንት እንዲፈጽሙ፤
10. በማኅበራዊ ግንኙነት በደስታ፣ በሐዘን፣ በዕድር፣ በሥርዓተ ቀብር አፈጻጸም እና በመሳሰሉት መሰባሰቦች በሽታው እንዳይሠራጭ አገልግሎቱ በውስን የሰው ቁጥር በጥንቃቄ እንዲፈጸም፤
11. ምእመናን ራሳቸውን እየጠበቁ በቫይረሱ የተጠቁ እና አገግመው የወጡ ወገኖችን፣ እንዲሁም በውጭ አገር ዜጎች ላይ ከሃይማኖት እና ከምግባር የወጣ መገለል እና ጥቃት እንዳይደርስባቸው በክርስቲያናዊ ፍቅር እና በኢትጵያዊ ጨዋነት ክብካቤ እንዲደረግላቸው፤
12. ለነዳያን እና ለተቸገሩ ወገኖች አስፈላጊው ማኅበራዊ እና ቁሳዊ እገዛ በኹሉም አጥቢያዎች እንዲደረግ፤
13. ቤተ ክርስቲያንን ከማይወክሉ እና ቀኖናዊ ካልኾኑ አሳሳች መረጃዎች በመቆጠብ ሊቃውንት፣ ካህናት፣ መምህራን፣ ሰባክያን፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ከቅዱስ ሲኖዶስ የሚሰጡ መመሪያዎችን በየአጥቢያችኹ እና አስፈላጊ በኾኑ ቦታዎች ኹሉ እንድትፈጽሙ እና እንድታስፈጽሙ ተወስኗል፡፡
በአጠቃላይ፣ በበሽታው እስከ አሁን ለተያዙት፣ በጊዜያዊ ማቆያ ለሚገኙት በሙሉ እግዚአብሔር አምላካችን ምሕረቱን እንዲሰጥልን እንጸልያለን፤
በመላው ዓለም፣ ዜጎቻቸውን በበሽታው ለተነጠቁ ኹሉ፣ መጽናናቱን እንዲሰጥልን፣ ያረፉትንም እንዲምርልን እግዚአብሔርን በጸሎት እንጠይቃለን፤
በመላው ዓለም የምትገኙ ወገኖቻችን፣ የራሳችኹ እና የሌሎች ሕይወት ከወረርሽኙ እንዲጠበቅ፣ እንዲሁም የበሽታው ሥርጭት እንዲቆም፣ መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ ሓላፊነታችኹን እንድትወጡ እያሳሰብን የተሰጡት መመሪያዎች ወረርሽኙ እስኪጠፋ ድረስ የጸኑ እንዲኾኑ በጥብቅ እናስታውቃለን፡፡
ልዑል እግዚአብሔር በቸርነቱ እና በይቅርታው ብዛት፣ ዓለማችንን ከጥፋት፣ የሰውን ልጅ ኹሉ ከመከራ ሞት ይጠብቅልን፤ አሜን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
መጋቢት 14 ቀን 2012 ዓ.ም.
አዲስ አበባ
Filed in: Amharic