>

የዶክተር  ካሳ ከበደ ነገር. . . (አቻምየለህ ታምሩ)

የዶክተር  ካሳ ከበደ ነገር. . .

አቻምየለህ ታምሩ

ዶክተር  ካሳ ከበደ  ግንቦት ፳ን አስታክከው በኢሳት ቴሌቭዥን ቀርበው ባካሄዱት ቃለ ምልልስ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት መጨረሻ ላይ ተፈጥሮ የነበረውን የሥልጣን ክፍተት ለመሙላት በእሳቸው አገላለጽ «የተዘረገፈውን ነገር መልሶ ጆንያ ውስጥ ከትቶ ሰብስቦ ለማሰር መልስ ሆኖ የተገኘው ወታደሩ ነው» ሲሉ ደርጎችን አወድሰዋል።
 ይህ የዶክተር  ካሳ አገላለጽ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም እ.ኤ.አ. በ1999 ዓ.ም. በሮይተርስ ቴሌቭዥን ቀርቦ «the only viable institution or social group to rescue the country was the army» ሲል ከተናገረው ጋር አንድ አይነት ነው። ዶክተር  ካሳ ንግግራቸውን ይቀጥሉና «በወታደሩ ላይ [ደርጎችን ማለታቸው ነው] የሚሰነዘረው አመለካከት ሚዛናዊ ቢሆን እመኛለሁ» ሲሉ አስተያየታቸውን ያጠቃልላሉ።
በእውነቱ ይህ የዶክተር  ካሳ አስተያየት እጅግ የሚያሳዝን ከመሆኑ ባሻገር ደርግን ለማግዘፍ የተሰጠ በጣም የሚያስተዛዝብ አስተያየት ጭምር ነው። የዝነኞቹ የሳንድረስትና የሳንሲየር ምሩቃን በነበሩባታ አገር ደመወዝ ለማስጨመር ከየ ክፍለ ጦሩ ተጠራርተው አዲስ አበባ የተሰባሰቡ አስር አለቆችንና የበታች መኮንኖችን «የተዘረገፈውን ነገር መልሶ ጆንያ ውስጥ ከትቶ ሰብስቦ ለማሰር መልስ ሆኖ የተገኘው ወታደሩ ነው» ማለታቸው ታሪካችንን ለሚያውቅ ሰው በእጅጉ የሚያም ነው።
ምናልባት ይህ ዶክተር  ካሳ ከበደ «የተዘረገፈውን ነገር መልሶ ጆንያ ውስጥ ከትቶ ሰብስቦ ለማሰር መልስ ሆኖ የተገኘው ወታደሩ ነው» ሲሉ የሰጡት አስተያየት እነ ጀኔራል ኃይሌ ባይከዳኝን፣ እነ ጀኔራል ዐቢይ አበበን፣ እነ ጀኔራል ከበደ ገብሬን፣ እነ ጀኔራል ይልማ ሽበሺን፣ እነ ጀኔራል አሰፋ አየነን፣ እነ ጀኔራል ደበበ ኃይለ ማርያምን፣ እነ ጀኔራል እያሱ መንገሻን፣ እነ ጀኔራል ስዩም ገድለ ጊዮርጊስን፣ እነ ጀኔራል ነጋ ተገኝን፣ እነ ጀኔራል ጃገማ ኬሎን፣ ወዘተን  የሚመለከት ቢሆን ኖሮ አስተያየታቸው ውኃ ሊቋጥር በቻለ ነበር። ዋናውን ስራቸውን [የአገር ዳር ድንበር መጠበቅን] ትተው ደመወዝ ለማስጨመር አዲስ አበባ የከተቱ ደም የተጠሙ ነፍሰ ገዳዮችን የተዘረገፈውን ነገር መልሶ ጆንያ ውስጥ ከትቶ ሰብስቦ ለማሰር መልስ ሆኖ የተገኘው ወታደሩ ነው» ብሎ ማቅረብ is beyond me to comprehend! ደመወዝ ለማስጨመር ከያሉበት የተሰባሰቡት የበታች መኮንኖች [ደርጎች] ምን አውቀው ነው የተዘረገፈውን ነገር መልሰው ሊያስሩ የሚችሉት? ኢትዮጵያ የተማረና አዋቂ ሰው አልኖራት ብሎ ነው መደዴዎቹ እነ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ክፍተቷን የሚሞሉላት? እንዴውም አብዛኛዎቹ እንደ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም አይነት ሌጣዎች በቅጡ እንኳ ትምህርታቸውን ያልጨረሱና የተማሩትን እንደ ኮሎኔል ስምረት መድኃኔና ሜጀር ጥበበ መንክር አይነት ልሒቃንን አጥብቀው የሚጠሉ ዋልጌዎች ነበሩ።
ሌላው ዶክተር  ካሳ ከበደ ያነሱት ጉዳይ «የተዘረገፈውን ነገር» ሲሉ የገለጹትና በሳቸው አቀራረብ «ደርጎች የሞሉት የስልጣን ክፍተት» ተፈጥሮ እንደነበር አድርገው ለማሳየር የሞከሩትም በእጅጉ ከእውነት የራቀና የሚያስተዛዝብ አስተያየት ነው። ጤና ይስጥልኝ ዶክተር ካሳ ከበደ?! የትና መቼ ነው የስልጣን ክፍተት የተፈጠረው? የአገር አስተዳደር ልምድና እውቀት የነበራቸው ኢትዮጵያውያን [Ethiopian Statesmen] የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ፓርላማው በሰጣቸው ኃላፊነት መሰረት አዕምሯቸውን ጨምቀው የወደፊቱን የኢትዮጵያ ሁኔታ የሚበይን ሕገ መንግሥት አሰናድተውና  ኢትዮጵያ ወደሚቀጥለው የለውጥና የዲሞክራሲ ጎዳና የምትጓዝበትን የለውጥ ፍኖት  አዘጋጅተው ጨርሰው ወደሚቀጥለው እድገት እየተሸጋገረች በነበረችበት ደረጃ ላይ አይደለም እንዴ እርስዎ «የሚሰነዘርባቸው አስተያየት ሚዛናዊ ሊሆን ይገባል» ያሏቸው ደመወዝ ለማስጨመር የተሰባሰቡት ደርጎች ከአንዳንድ የውስጥ አዋቂዎች ጋር ተመሳጥረው መፈንቅለ መንግሥት [creeping coup] ያካሄዱት?
ሌላው ቢቀር ደርግ ራሱ መስከረም ሁለት 1967 ዓ.ም. ባስነገረው አዋጅ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አስተዳደር በልጅ እንዳልካቸው መንግሥት የተቋቋመው ኮምቴ ባዘጋጀው ሕገ መንግሥት መሰረት ባስቸኳይ ምርጫ እንደሚካሄድ፣  አልጋ ወራሹ ንጉሠ ነገሥቱን ተክተው እንደሚነግሱና  ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ እንዲመረጥ የሚደነግገው ረቂቅ ሕገ መንግሥት ስራ ላይ እንደሚውልኮ  አውጇል። ይህ የደርግ አዋጅ የተዘረገፈ ነገር እንዳለና መልሶ ወደ ጆንያ ውስጥ በደርጎች እንደሚከተተ አያሳይም። እርስዎም እንደሚያውቁት በአባትዎ በደጃዝማች ከበደ ተሰማ አማካኝነት መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ፊት ቀርቦ የንጉሠ ነገሥቱን እጅ ነስቶ የተቀበለው 40 ሺህ ብርኮ የስልጣን ክፍተት ለመሙላት አዲስ አባባ መጥቶ የተሰጠው ሳይሆን የተረቀቀው ሕገ መንግሥት ሥራ ላይ እንዲውል ለማገዝ መጣን ባለው መሰረት እሱና ባለንጀሮቹ የሆኑት የበታች መኮንኖች ከተማ ውስጥ ሁከት የሚያስነሱ ተማሪዎች ጥፋት እንዳያስከትሉ የሚያደርጉትን የሰላም ማስፈን ስራ ባግባቡ ለማስኬድ እንዲችሉ የየእለት ወጪያቸውን ለመሸፈን ነበርኮ።
ባጭሩ ደርግ የፈጠረው የአገርና የትውልድ ክፍተት እንጂ የሞላ አንዳች የሥልጣን ክፍተት አልነበረም። አንድ ነገር ሊታወቅ ይገባል። ደርግ ሥልጣን የወሰደውም ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እጅ ሳይሆን እሳቸውን ከተኳቸው ሰዎችና ኢትዮጵያ በሕዝብ የተመረጠ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲኖራት የሚደነግገውን ረቂቅ ሕገ መንግሥት መስከረም ሁለት ባወጣው አዋጅ በማገድ ነው። እንዴውም እንነጋገር ከተባለ ከወያኔ በፊት  ኢትዮጵያን አደጋ ላይ የጣለው ደርግ ነው። ኢትዮጵያ  ያስተማረቻቸውን ጀኔራሎችን ገድሎ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ያስደፈረው ደርግ ነው። ኢትዮጵያኮ ከሶማሊያ ጋር ጦርነት ስታደርግ ጦሩን የሚመራ አንድም  ጀኔራል አልነበራትም።  ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር ባደረገችው ጦርነት ጦሩን የሚመራ ጀኔራል ያልነበራት ጀኔራሎችን ስላላፈራች ሳይሆን ያፈራቻቸውን ጀኔራሎች ደርግ ፈጅቷቸውና የቀረሩትንም አስሯቸው ነው። ከዚህ በላይ የአገርን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ መጣልና ክፍተው መፍጠር ምን ሊኖር ይችላል?  ግና  የወያኔና የደርግ ጠላት ኢትዮጵያ ስለነበረች ደርግ ወድቆ ወያኔ ሲተካ ደርግ በኢትዮጵያ ላይ የፈጸመው ግፍ እስከዛሬ ድረስ ሳይነገር ተሽፍኖር እንዲሁ ይኖራል!  ሌላው ቢቀር ወያኔ በሀብት ባሕር የዋኘው ደርግ  ከኢትዮጵያውያን ወርሶ ትቶላቸው በሄደው የኢትዮጵያውያን  አንጡራ ሀብት መሆኑን እንኳ ልትነግሩን አትፈልጉም።
ስለእውነት ስለእውነት. . . ኢትዮጵያን አደጋ ላይ የጣሉና የደም ባሕር ያደረጓትን ደርጎችን፤ እነ ክዋሜ ኑክሩማህ «Ethiopia, a land of the wise; the bold cradle of Africa’s ancient rule and fertile school; the beacon of freedom for the black peoples in the world and the repository of Africa’s culture» ያሉላትን ጥንታዊቷን ኢትዮጵያ ታሪክ አልባ አድርገው ታሪኳንና ብሔራዊ ትርክቶቿን [national narratives] ወደ ተጨቋኝና ጨቋኝ ግንኙነት ያወረዱ ነውረኞችን፤ ኢትዮጵያ ወደፊት እንዲረከቧት ያስተማረቻቸውንና እጅጉን የበቁ ልጆቿን በዱልዱም አርደው የበሉ አውሬዎችን፤ ኢትዮጵያ እያደረገችው የነበረውን ተፈጥሯዊ ግስጋሴ ገትተው ከነበረችበት የጥቁር ሕዝቦች የለውጥ ኃዋርያነትና የተስፋ ጮራነት አዋርደውና በስተመጨረሻም ኢትዮጵያውያን በላባቸው ያፈሩትን ሀብት ሁሉ ወርሰው ለወያኔዎች አስከርበው አገር አልባ ያደረጉንን ደርጎችን አገር እንዳረጋጉና የሥልጣን ክፈተት እንደሞሉ አድርጎ ማቅረብ በእጅጉ ያማል!
Filed in: Amharic