>

ጃዋር [እና] ዋኤል ...!!! (ካሳ አንበሳው)

ጃዋር [እና] ዋኤል …!!!

ካሳ አንበሳው

ጃዋር መሐመድ እንደጀመረው የዋኤልን መንገድ ተከትሎ ቢሆን ኑሮ ዛሬ ሀውልት አፍርሱ የሚለው ጃዋር ጎንደር ውስጥ ሀውል ይጠረብለት ነበር፣ ከዋኤል ያላነሰ አለም አቀፍዊ እውቅና አያጣም ነበር፣ ነበር ባይሰበር….
 
[ጁን 8, 2010] ዋኤል ጎኒም (ዕድሜ 28) እንደወትሮው ዜናዋችን ለመቃረም፣ ከዘመድና ወዳጅ ጋር ለመወያየት ዱባይ ከሚገኝው መኖሪያ ቤቱ ተቀምጦ በፌስቡክ መስኮት ወደ ትውልድ ሀገሩ ግብጽ ዘለቀ፣ በዛን እለት ያነበበው ዜና እና የተመለከተው ፎቶ ስሜቱን አወከው፣ እረፍት ነሳው፣ ዜናው አሌክሳንድሪያ ውስጥ በሙባረክ የጸጥታ ሀይሎች በግፍ ስለተገደለው ካሊድ ሰይድ (እድሜ 28) ነበር፣ ሶሻል ሚዲያ ላይ ሲዘዋወር የነበረው የካሊድ አስከሬን በዐይን ለማየት ይከብዳል፣
“በዛ አሰቃቂ የካሊድ ፎቶ ውስጥ እራሴን አየሁት፣ በካሊድ ቦታ እኔም ልሆን እችል ነበር ብዬ አሰብኩ” ይላል ዋኤል በዛች ቅጽፈት የተሰማውን ስሜት ሲገልጽ፣ ከቁጭትና ንዴት ባለፈ አንድ ነገር ማድረግ እንዳለበት አሰበ፣ ጊዜ ሳያጠፋ ማንነቱን ደብቆ “We are all Khaled Said/ሁላችንም ካሊድ ሰይድ ነን” የሚል የፌስቡክ ገጽ ከፈተ፣
ገጹ በተከፈተ ሁለት ሰዓት ውስጥ 300 ሰዋች ተቀላቀሉት፣ ከሁለት ወር በኃላ የአባላቱ ብዛት ወደ 250,000 ሲያድግ አብዮቱ ዋዜማ ላይ የአባላቱ ብዛት 3 ሚሊየን ደርሶ ነበር፣ ገጹ ከአረቡ አለም ብዙ ተከታይ ያለው ገጽ ሁኖ ተመዘገበ፣ የአባላቱ ቁጥር ከፍ እያለ ሲመጣ ዋኤል ሙሉ ሰዐቱን ሰጥቶ አብዮቱን በከፍተኛ ሀላፊነት ይከካውና ያቦካው ገባ፣ ሀሳብ ያለው ይሳተፋል፣ ቀሪው አስተያየት ይሰጣል፣ የሰማው ላልሰማው ያጋራል፣ “ፌስቡክ ላይ ለሆነው ሁሉ ስሙን ጠርተን ጀግና ነህ የምንለው ሰው የለንም፣ ሁሉም ጀግና ነውና” ይላል ዋኤል የሁሉንም አስተዋጾ ዋጋ እንደነበረው ለመግለጽ፣ “የግብጽ አብዮት የተጻፈው ልክ እንደ ዊኪፒዲያ ነው፣ ሁሉም አዋጥቷል፣ ያዋጣው ሰው ስም አይታወቅም” ነው የሚለው፣
የግብጽ አብዮት ፎስቡክ ላይ እየጋመ ባለበት ወቅት ቱኒዚያ የተነሳው ህዝባዊ ማዕበል በ28 ቀን ውስጥ የቤን አሊን መንግስት ጠራርጎ ወሰደው፣ ከተፎው ዋኤል “ቱኒዚያ ውስጥ የሆነው ግብጽ ውስጥ የማይሆንበት ምን ምክንያት አለ?” የሚል ወሳኝ ጥያቄ ይዞ ብቅ አለ፣ የህዝቡ ምላሽ አዋንታዊ ሆነ፣ “እናድርገው! የፈራ ይመለስ!” ባይ ሆነ፣ ዋኤል ጊዜ ሳያጠፍ የሰልፍ አስተባባሪዋችን በሚስጥር እየተገናኝ ሰልፋ የሚከናወንበትን መንገድ ይገልጽ ገባ፣ ጃንዋሪ 25, 2011 የጣሂር አደባባይ በወጣቶች ተጥለቀለቀ፣ የሙባረክ ምጥ “ሀ” ብሎ ጀመረ፣
ፌስቡክ ላይ የተጸነሰው አብዮት ሽሉ እየገፍ ሲመጣ ለግል ጉዳይ ወደ ሀገሩ መመለስ እንዳለበት አለቆቹን አሳምኖ አብዮቱን ሊያዋልድ ዋኤል ካይሮ ገባ፣ 
ጃንዋሪ 27 ዋኤል የተሳተፈበት ሀገር አቀፍ ሰልፍ ተደረገ፣ ውጥረት የበዛበት የሙባረክ መንግስት አራት የሚሆኑ የኢንተርኔት ማስተላለፉያ መስመሮችን ዘጋ፣ በዛኑ ቀን የጸጥታ ሀይሎች ዋኤልን አፍነው ወደ አልታወቀ ቦታ ወሰዱት፣ የልጁ መታፈን ወጣቶቹን አስቆጣ፣ መሰወሩን የአለም አቀፍ ሚዲያዋች ተቀባበሉት፣ ጎግል መግለጫ አወጣ፣ የሰባዊ መብት ድርጅቶች ተንጫጩ፣ አላየሁም ዐይኔን ግንባር ያርገው ሲል የነበረው የሙባረክ መንግስት ጫና ሲበዛበት (ከ11 ቀን በኃላ) ይሄውላችሁ ብሎ ለቤተሰቡ አስረከበው፣
የዋኤል ከእስር የወጣው አሞቱን እምርሮ ነበር፣ ከእስር በወጣበት ቀን Dream TV ጋር ባደረገው ቆይታ የሙባረክን መንግስት “ቆሻሻ ነው፣ ቆሻሻ ደግሞ ትጠርጎ መጣል አለበት” ሲል ቆምጨጭ ያለ አስተያቱን ሰጠ፣ አስከትሎም በዚህ ትግል ውስጥ መሞት ለሱ ክብር እንደሆነ በመግለጽ ከትግሉ ወደ ኃላ እንደማይል አስረግጦ ተናገረ፣
የሙባረክ መንግስት ስንብት እርግጥ እየሆነ ሲመጣ (ፌብሩዋሪ 9) እስከ ዛሬ የምትጠቀስለት አንድ ወሳኝ መልዕክት ጣሂር አደባባይ ለተሰበሰቡት አብዮተኞች አስተላለፈ፣
“This is not the time for individuals, or parties, or movements. It’s a time for all of us to say just one thing: Egypt above all”
” ይህ የግለሰቦች ወይም የፖለቲካ ድርጅቶች ወይም የንቅናቄዋች ጊዜ አይደለም፣ ይህ ሁላችንም በአንድ ልብ “ግብፅ ትቅደም” የምንልበት ወቅት ነው”
ይህን ንግግር ባደረገ ሁለተኛው ቀን የሙባረክ መንግስት ስልጣን ለቆ ወታደራዊው ምክር ቤት ሀገሪቱን ማስተዳደር ጀመረ፣ አንድ ላይ የሚያጨበጭበው፣ በአንድ ላይ የሚጮህው፣ አንባገነኑን ስርዕት ያራደው ማህበራዊው ሚዲያው በለውጡ ማግስት መሰንጠቅ ጀመረ፣ ቆየት ብሎ ተተረተረ፣
ይህ ዋኤል የጠበቀውና የተዘጋጀበት ጉዳይ አልነበረም፣ “ህዝብን ከጭቆና ቀንበር ለማላቀቅ የሚያስፈልግህ ኢንተርኔት ነው የምል ሰው ነበርኩ፣ ተሳስቼ ነበር/ I once said If you want to liberat a society all you need is the internet, I was wrong” ይላል ወቅቱን ሲያስታውስ፣
ከሙባረክ ፈርጣማ ክንድ ያላቀቃት ማህበራዊ ሚዲያ ግብጽን ሊያጠፍት እንደሆነ ግልጽ እየሆነ መጣ፣ ስድስት ነገሮች ናቸው የሆኑት ይላል የአብዮቱ ወላጅ አባት ዋኤል ጎኒም፣
 [1] በወታደራዊው ኃይል ደጋፊዋችና ኢስላሚስት መካከል ጽንፈኝነት (polarization) ስር ሰደደ
[2] ሀሜትና የውሸት/የተሳሳተ መረጃ (rumours and misinformation) ነገሰ
[3] ፌስቡከኛው የራሱን ድምጽ የሚያስተጋባለት ጎጆ (echo chamber) ፈጠረ፣ የተለየ ሀሳብ ያለው ሰው በብሎክ ያሰናብተው፣ ባለመከተል (unfollow) ይርቀው ጀመር
[4] ውይይትና ክርክር ወደ ስድብና ዘለፍ ተለወጡ [5] አዲስ ማስረጃ በቀረበለት ጉዳይ ላይ ጭምር ሀሳብ መቀየር፣ አቋምን መከለስ ከባድ ሆነ፣ ግትርነት ጌጥ ሆነ
 [6] ሁሉም ተንታኝ፣ ሁሉም ጸሐፊ፣ ሁሉም ተናጋሪ ሆነ፣ የሚሰማ እና የሚያነብ ጠፍ፣
ከላይ በተጠቀሰው መንገድ ስርዐት አልበኛ የሆነው ማህበራዊ ሚዲያ በዲሞክራሲያዊ ምርጫ ስልጣን የተረከበውን መሐመድ ሙርሲን ጁላይ 3, 2013 ከወንበሩ ከነበለው፣ “የዛን እለት ተስፋ ቆርጪ ከማህበራዊ ሚዲያው ራሴን አገለልኩ” ይላል ዋኤል፣ ፖለቲካውን ለፖለቲከኞች ትቶ፣ ጨርቁን ከጣለው ማህበራዊ ሚዲያ ራሱን አግሎ ከስር የምገልጻቸውን ከወነ፣
[የግብጽ ማህበራዊ ሚዲያ አደብ እንዲገዛ የሆነበትን ሂደት ወደ ፊት አቀርበዋለው] 
 
ነገረ ዋኤል______
ዋኤል ከእድሜው በላይ ያነበበ፣ ከሁለት ትልልቅ ዮኒቨርስቲዋች ሁለት ዲግሪዋች በከፍተኛ ማዕረግ የወሰደ ባለ ብሩህ አዕምሮ ወጣት ነው፣ የመጀመሪያው ዲግሪ በኮንፒዮተር ሳይንስ መሆኑና ጎግል ውስጥ መስራቱ ማህበራዊ ሚዲያውን በስፍትና በተገቢው መንገድ እንዲጠቀምበት ሳይረዳው አልቀረም፣
ዋኤል በግብጽ አብዮት ከነበረው ትጽህኖ አንጻር የፕሬዝዳንትነት ወንበር ቢያጣ ጠቅላይነቱን የሚከለክለው አልነበረውም፣ ልጁ ቀልቡን የገዛ፣ በጭብጨባ ያልሰከረ፣ ሰክኖ የተወለደ ሆኖ ኑሮ ይህን ጥያቄ ሲቀርብለት እኔ ለፖለቲካ አልተፈጠርኩም፣ ስልጣንም አልፈልግም፣ ቀጥተኛ የፖለቲካ ተሳትፎ ሳላደርግ ሀገሬን በምችለው ሁሉ እረዳለው እያለ መልስ ይሰጥ ነበር፣ አብዮቱን በከፍተኛ ሀላፊነት ከመምራቱ በበለጠ ከአብዮቱ በኃላ ባሳየው ስክነት እና አርቆ አሳቢነት አለም አደነቀው፣
በ2011 ለሰላም ኖቤል ሽልማት እጩ ሁኖ ቀረበ፣ ኒው ዮርክ ታይምስ የአለማችን 100 ተጽኖ ፈጣሪ ሰዋች መዝገብ ላይ ስሙን ከተበለት፣ “Arabian Business” የሚሰኝ ደረጃ አውጪ “የ2013 ተጽኖ ፈጣሪ አረብ” ብዬ ሰይሜሀለው ብሎታል፣ የአለም ኢኮኖሚክ ፎረም የ2012 “Young Global leader” አለው፣ በጆን ኤፍ ኬኔዲ መታሰቢያ የሚሰጠው “Profile in Courage Award” ይገባሀል ተባለ፣ ሽልማቱን የወሰደው የJFK ሴት ልጅ እጅ ነው፣ ሀርቫርድ ዮኒቨርስቲ ደረቱን በሜዳሊያ ካሸበረቀለት በኋላ የዮኒቨርስቲው ማህበረሰብ (senior fellow) አድርጌ ሹሜሀለው አለው፣ TEDTalks ተናጋሪ ነው፣ በትልልቅ ዮኒቨርስቲዋች እየተጋበዘ “ቃል አውጣ” የሚባል ሰው ሆነ፣
ዋኤል በበኩሉ “Revolution 2.0: The power of people is greater than the people in power ” በሚል ርዕስ አብዮቱን የሚያትት መጸሐፍ አሳተመ፣ ከመጸሐፍ ሽያጭ የተገኝውን 2.5 ሚሊየን ዶላር ለበጎ አድራጎት ድርጅት ለገሰ፣ “Tahrir Academy” የሚሰኝ ማሰልጠኛ ከፍቶ ጥልቅ አሳቢዋችን የወደፊት መሪዋችን እያሰለጠነ ነው፣
ነገረ ጃዋር____
ጃዋር መሐመድ የዋኤልን መንገድ ይከተል እንደነበር ብዙ ማሳያዋች አሉ፣ ህልሙና ግቡ ዋኤልን መሆን ነበር፣ ነበር ባይሰበር፣
በእርግጥ የጸረ ወያኔ ትግል በተፈለገው መንገድ ቢጻፍ ጃዋር መሐመድን ሳይጠቅስ አያልፍም፣ የልጁን አስተዋጾ ማኮስመን ትዝብ ላይ ይጥላል እንጂ ሀቁን አይቀይረውም፣ ኦሮሞ የኢትዮጵያ ግንድ ነው ብዮ ስለማስብ ጃዋር ለኢትዮጵያ አልታገለም ለማለት እቸገራለሁ፣
ጃዋር የገዛ ራሱን ቁርጭምጭሚት በጥይት የነደለው ከድህረ ወያኔ በኃላ ነው፣ ራሱን መግዛት አቃተው፣ ጭብጨባ አሰከረው፣ በዋኤል ልሳን “ፖለቲካ የኔ አይደለም፣ ሀገሪቷ እንድትረጋጋ የበኩሌን ካበረከትኩ በኃላ ማስተማር ነው የምፈልገው፣ የኔ ስራ የወደፊት መሪዋችን ማብቃት ነው” ሲል ቆየ፣ ብዙም ሳይቆይ “ኦፌኮ” ነኝ ብሎ መጣ፣ የዛን ቀን ጃዋር መሐመድ የግብጹን ዋኤል ጎኒምን እንደማይሆን ተረጋገጠ፣
ጃዋር መሐመድ የዋኤልን መንገድ ተከትሎ ቢሆን ኑሮ ዛሬ ሀውልት አፍርሱ የሚለው ጃዋር ጎንደር ውስጥ ሀውል ይጠረብለት ነበር፣ ከዋኤል ያላነሰ አለም አቀፍዊ እውቅና አያጣም ነበር፣ ነበር ባይሰበር፣
መውጫ_____
ጃዋር መሐመድ የፖለቲካ ድርጅት አባል መሆኑ ትልቅ ስህተት እንደሆነ የገባው ይመስለኛል፣ እንደ እግር እሳት እንደሚያቃጥለው አልጠራጠርም፣ የድርጅት አባል መሆኑ በኦሮሞ ማህበረሰብ ውስጥ ያለውን ተጽኖውን ቀነሰበት እንጂ አልጨመረለትም፣ ፖለቲካውም የተሳካለት አይመስልም፣ ጃዋት ከሁለት ያጣ ቁማርተኛ ነው፣ የቆሰለ አውሬ ነው፣ ተስፍ የቆረጠ ፍጡር ነው፣ የቆሰለ አውሬ፣ ተስፋ የቆረጠ ፍጡር ደግሞ ሰማይ ቢከነበል፣ ምድር ብትጠቀለል ደንታው አይደለም፣ እንጠንቀቀው!
Filed in: Amharic