>

ብልጽግናዎች እነ እስክንድርን  ያሰሯቸው በሶስት ምክንያቶች ነው...!!! (ግርማ ካሳ)

ብልጽግናዎች እነ እስክንድርን  ያሰሯቸው በሶስት ምክንያቶች ነው…!!!

ግርማ ካሳ

ሕግን ማስከበር በሕግ ስም ሰላማዊ ዜጎች ላይ ዱላ ማሳረፍ አይደለም 
አንድ ያልተዋጠልኝ ነገር ቢኖር ግርግሩን ተጠቅሞ በአጫሉ ግድያ ዙሪያ ምንም ግንኙነት የሌላቸውን ዜጎች በጅምላ የማሰሩ ጉዳይ ነው።
እስክንድር ነጋ ፣ ስንታየሁ ቸኮል ፣ ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት ሌሎችም ይኖራሉ፣  ከሃጫሉ መገደል ጋር በተገናኘ ታሰሩ መባሉ ታላቅ ፌዝ ነው!!!
ባልደራሶች በሰላም፣ የአገሪቷ ሕግ በሚፈቅደው መሰረት የሚንቀሳቀሱና የሚሰሩ ናቸው። 
–   በአዲስ አበባ በኢንጂነር ታከለ ኡማ መስተዳደር በግፍ ተፍናቅለው ሜዳ ላይ ለሚበቱ ወገኖች ፣ ለድሆች የሚሟጋቱና ለአዲስ አበባ ሕዝብ ጥቅም የሚሰሩ ናቸው።
– የባልደራስ ደጋፊዎች ቆንጨራና ገጀራ ይዘው የሚዞሩ አይደለም። ድሆችን ለመርዳት እርዳታና ድጋፍ ይዘው የሚዞሩ ናቸው። ሰው ለመገደል፣ ለማፈናቀል፣ ለመዘረፍ የሚሰማሩ ሳይሆን የተገፊ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ለማንሳት እጅ የሚዘረጉ ናቸው። ለነርሱ የሚጮኹ ናቸው።
–  አንድም ጊዜ ባልደራስ የመንግስት አካላት እውቅና ሳይሰጡ ሰልፎችንም ሆነ  ሕዝባዊ ስብሰባዎችን አድርጎ አያውቅም። ባልደራስ አቋሞቹን፣ ፖለቲካውን በግልጽ ነው ያስቀመጠው።
ባልደራሶችን አውቃቸዋለሁ። እስክንድር ነጋን ስንታየሁ ቸኮል በአካል አውቃቸዋለሁ። አደርባዮች አይደሉም። ስልጣን ፍለጋ ለመሪዎች አጨብጫቢ አይደሉም። የጥቅም ሰዎች አይደሉም። ለሕዝብና ለአገር የታሰሩ፣ ትልቅ ዋጋ የከፈሉ ናቸው። ዘረኝነትን የሚጸየፉ፣  ዜጎች በኃይማኖታቸውና በጎሳቸው ልዩነት ሳይደርግባቸው እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚሰሩ ናቸው።
እነ እስክንድር ነጋን አመጽ ቀሰቀሳችሁ ብሎ ማሰር በጭራሽ ተቀባይነት የለውም። አራት ኪሎ ያሉት ሕግ ማስከበር የሚሉትን ነገር መሳቂያ ባያደርጉት ጥሩ ነው። ለነርሱም ለፖለቲካቸው አይጠቅማቸውም። በአንድ በኩል ከግብጾች፣  ከወያኔዎች፣  ከኦነጋዊያንን ጃዋራዉያን ጋር እየታገሉ ፣ በሌላ በኩል ሌላው ማህበረሰብ በተቃውሞ እንዲነሳባቸው ማድረግ የለባቸውም። ወዳጅ እንጂ ጠላት ማብዛት አለማስተዋል ነው።
ዜጎችን ከአሸባሪዎች ይጠበቁና  ሕግ ያስከበሩ ዘንድ ተጠየቁ እንጂ ሕግን በማስከበር ስም ሕግን በመጣስ በዜጎች ላይ በደል እንዲፈጸሙ አይደለም የተጠየቁት።
አንዳንዶች፣ እነ እስክንድር ነጋን ዛሬ ያወቋዋቸው ይመስል፣  “መረጃ በነ እስክንድር ላይ ቢኖራቸው ነው” ሲሉ ያስቁኛል። ይኸው መስተዳደር አይደለም እንዴ፣ ከአንድ አመት በፊት፣ የሰኔ 15ቱን የባህር ዳር ግርግር እንደ ሰበብ ቆጥሮ፣ የባልደራሶቹ ስንታየሁ ቸኮልንና ኤሊያስ ገብሩ ለ4 ወራት ክስ ሳይመሰርቱባቸው አስረዋቸው በኋላ ምንም መረጃ አላገኝንም ብለው የፈቷቸው ?
ምንም መደባበቅ አያስፈልግም። እነ እስክንድርን ብልጽግናዎች ያሰሯቸው በሚከተሉት ሶስት ወይንም ከሶስቱ አንዱ ወይ ሁለቱ  ምክንያቶች ነው።
አንደኛው–  እነ እስክንድር እያደረጉት ያለውን ፣ ታከለ ኡማን ጨምሮ አንዳንድ የኦህዴድ/ብልጽግና ሃላፊዎች የሚሰሩት ሙስናና ህገ ወጥ ተግባራት ፣ በመረጃና በበቂ ሁኔታ፣ ሰላማዊ  በሆነ መንገድ  በማጋለጣቸው፣ ከማንም ድርጅት በላቀ የሕዝብን መሰረታዊ ጥያቄዎች በማንገባቸውና  በሕዝብ ያላቸው ድጋፍ በመጨመሩ ደስተኛ ስላልሆኑ ነው፡፡ ይሄን አጋጣሚም ተጠቀመው  የባልደራስን ግስጋሴ ለመግታት ካላቸው የተሳሳተ አመለካከት የተነሳ ነው።
ሁለተኛ ፣ የሕዝብ ደም በእጃቸው ያለባቸው ከአጫሉና ሌሎች በኦሮሞ ክልል ከተፈጸሙ ግድያዎች ጋር ንክኪ ሊኖራቸው የሚችለውን  እነጃዋርን በማሰራቸው ፣ ጸረ-ኦሮሞ እንዳይባሉ፣ ሌሎችንም  አስረናል ለማለት ነው ያሰሯቸው። ማባያ እንዲሆኗቸው። የሚገርመው ግን እነዚሁ ባለስልጣናት ከአንድ አመት በፊት ከባህር ዳር በጅምላ ሲያስሩ፣ በተመሳሳይ ሎጂክ የኦሮሞ ፖለቲከኞችንና አክቲቪስቶችን አላሰሩም ነበር።
ሶስተኛ ፣ ለጊዜው ጠመንጃ በእጃቸው ስላለ ነው። ፣ ጡንቻ ስላላቸው።  “የፈለግነው ብናደርግ ማን ይናገረናል ?”  ከሚል፣ ስልጣናቸውን ተማነው፣  ልባቸው በመታወሩና ውስጣቸው በጥጋብ በመሞላቱ።
አንዳንዶች እነ እስክንድር የታሰሩት ፣ እንዳይገደሉ ሊጠብቋቸው ነው ይላሉ። እኔም የነ እስክንደርን መታሰር ስሰማ ያ ነበር የመሰለኝ። ግን የመንግስት ሃላፊዎች በሜዲያ ወጥተው እነ እስክንድር  ፣ አይናቸውን በጨው አጥበው፣ አመጽ ቀስቅሰዋል በሚል ስማቸውን ሲያጠፉና ሲበጣረቁ  ስሰማ፣ ወደ ወህኒ ሲወስዷቸውም እያመናጨቋቸውና እያዋከቧቸው መሆኑ ሳውቅ ያሰብኩት እንዳልሆነ ገባኝ።
ብዙዎቻን ዶር አብይ የሕዝብ ደም በእጃቸው ያለባቸውን ሰዎች ከብዙ ግፊትና ልመና በኋላ በቁጥጥር ስር መዋሉ በእጅጉ አስደስቶናል። ሆኖም ግን በብርሃን ፍጥነት እነ እስክንድርን በማሰር ደስታችን ላይ ግን ቀዝቃዛ ዉሃ ከልብሶበታል።ጥሩ ሰርቶ ሊያገኝ የነበረውን ድጋፍ መሎስ መሬት ላይ በትኖታል።
አሁን ዶር አብይ ልብ ይገዛ ዘንድ፣ ጥሩ አማክሪዎችን ከጎኑ ያደርግ ዘንድ እመክረዋለሁ። ለርሱምቅርበት ያላችሁ ወገኖች ምከሩት። የአዲስ አበቤዎች ተቆርቋሪ የሆኑትን ባልደራሶች በአስቸኳይ መፍታት አለበት። ከአዲስ አበቤው ጋር በታከለ ኡማ ምክንያት እየተካረረ ነው። ነገሮችን የበለተ ባይባባስና  አዲስ አበቤው የበለጠ ባያስክፋ ጥሩ ነው።
ሕግ ወንጀለኛ ለመቅጣት የሚረዳ ነው። ሕግን ማስከበር ማለት ወንጀለኛን መቅጣት ማለት ነው። በሕግ ስም፣ ህግን እንደ ዱላ በመጠቀም፣ ወንጀል የሌለባቸውን ሰዎች ላይ ዱላን ማሳረፍ ኢሰባአዊነት ብቻ ሳይሆን ትንሽነት ነው።መሸነፍ ነው።
Filed in: Amharic