>

አብይን መደገፍ ኢትዮጵያዊነት ነው  (ዶ/ር ዘላለም እሸቴ)

አብይን መደገፍ ኢትዮጵያዊነት ነው 

ዶ/ር ዘላለም እሸቴ


ሲጀመር ሁላችንም የአብይን ንግግር ወደን አብይን ደገፍን።  አሁን ደግሞ ሁላችንም ኢትዮጵያን ወደን አብይን የምንደግፍበት ጊዜ ነው።  ኢትዮጵያ መጨረሻዋ ምን ይሆን ብለን ስንሰጋ መንታው መንገድ ላይ ደረስን።  አንደኛው ኢትዮጵያ የምትቀጥልበት አቀበት ሲሆን፥ ሌላኛው ሞቷ የታወጅበት ቁልቁለት ነው።  መሀል ሰፋሪ መሆን ከእንግዲህ አይቻልም። ፖለቲካ አያገባኝም ማለት ዘበት ነው። የምንደግፈውን ፓርቲ ወደ ስልጣን እንዲመጣ የምንሮጥበት ጊዜ አሁን አይደለም። የዛሬው ምርጫ ኢትዮጵያን ማስቀጠል ላይ የሚወስን ነው። ዛሬ ኢትዮጵያን ሊያጠፋ ከመጣ እኩይ ተንኮል፥ ወጥመዱ ተሰብሮ ኢትዮጵያ የምታመልጥበት ወሳኝ ሰዐት ነው።  ስለዚህም ዶ/ር አብይን መደገፍ ኢትዮጵያን ማሻገር ነው። ሳይበላ እያበላን ያስተማረንን ድሀ ባለ አገሩን እናስብና ለኢትዮጵያ ዘብ እንቁም። ሀገር ከሌለ፥ እንዳለን አይቆጠርም። ስለዚህ በቃል በፀሎትና በሥራ ከጎኑ እንቁም።

 

ኢያሪኮን ያፈረሰው ድምፅ ነው። ምክንያቱም ከድምፁ ጀርባ ፈጣሪ ነበርና። ለዶ/ር አብይ አጋርነታችንን ስናሳውቅ፥ ፍቅርን አብሮነትንና ቤተሰብነትን መምረጣችን ነው። ይህም ድምፅ ብርሀን የሆነ ነው።  ጨለማ የሆነው የአጥፊውን ሴራ ስፍራውን የሚያስለቅቀው የብርሃን ድምፅ ነው። እኛ ተነስተን ድርሻችንን እንወጣ፥ ማዳን ከፈጣሪ ይሆንልናል። የሚንጫጫው የጥቂት ፅንፈኞች ድምፅ ፀጥ ይላል ብለን አንጠብቅ።  ይልቁንስ አድፍጦ የተኛው ብዙሃኑ ዝምተኛ ድምፁ ይሰማ። አንበሳው ሕዝብ ያግሳ። ያ ጥቂት አጥፊ ድምፅ የኢትዮጵያን ሕዝብ ስብዕና እንደማይወክል ይታወቅ። በቃ! ይሁን አሜን።

Filed in: Amharic