>

ብልፅግና ፓርቲ ራሱን “ከመሀል ሰፋሪዎች” የማፅዳት ዘመቻ ሊጀምር ነው (ዋዜማ ራዲዮ) 

ብልፅግና ፓርቲ ራሱን “ከመሀል ሰፋሪዎች” የማፅዳት ዘመቻ ሊጀምር ነው

ዋዜማ ራዲዮ- 

  * በጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ እና በመከላከያ ሚንስትሩ ለማ መገርሳ መካከል ያለውን አለመግባባት ለመፍታት የተደረጉ ጥረቶች የታሰበውን ውጤት አላስገኙም። ምንም እንኳን ለማ መገርሳ በመደበኛ ስራቸው ላይ ቢሆኑም ቁርሾውን ወደጎን ትተው በተመደቡበት ዘርፍ ሀላፊነታቸውን መወጣት አልቻሉም…
 
በኦሮምያ ክልል የድምፃዊ ሀጫሉ ሁንዴሳን መገደል ተከትሎ ከፍተኛ ተቃውሞና የፀጥታ መደፍረስ መከሰቱ ይታወቃል። ክስተቱን ተከትሎ የኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ ራሱን “ከመሀል ሰፋሪዎች” ለማፅዳት አስቸኳይ ስብሰባ እያዘጋጀ መሆኑንና በግምገማ የሚለዩትን አባላት እንደሚያሰናብት የፓርቲው ከፍተኛ ካድሬዎች ለዋዜማ ተናግረዋል።
የኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ አመራር እንደነገሩን በፓርቲው ውስጥ ሆነው ድርጅታዊ ስነምግባር ከሚፈቅደው ውጪ ከተለያዩ ጀብደኛና የሽብር ቡድኖች ጋር የዓላማ ትስስር ያላቸውን የመለየትና የማሰናበት ስራ ይጀመራል። የድርጅቱ አብዛኛው አባልና አመራር ቀን ተሌት ለውጡን ከግብ ለማድረስ በሚለፋበት በዚህ ወቅት ድርጅታዊ ስነምግባርና የዓላማ ግልፅነት የጎደላቸውን በግምገማ በመለየት የመገሰፅና ችግሩ የባሰባቸውን ደግሞ የማሰናበት ዕቅድ አለ።
ከኦሮምያ ውጪ ያሉ የብልፅግና አባል ድርጅቶች የዚህ ግምገማ አካል አይደሉም።
ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ምንጮች እንደነገሩን በጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ እና በመከላከያ ሚንስትሩ ለማ መገርሳ መካከል ያለውን አለመግባባት ለመፍታት የተደረጉ ጥረቶች የታሰበውን ውጤት አላስገኙም። ምንም እንኳን ለማ መገርሳ በመደበኛ ስራቸው ላይ ቢሆኑም ቁርሾውን ወደጎን ትተው በተመደቡበት ዘርፍ ሀላፊነታቸውን መወጣት አልቻሉም። አቶ ለማ አቤቱታቸውን በድርጅት ግምገማ የማቅረብ ፍላጎት እንዳላቸው ለቅርብ ወዳጆቻቸው ሲናገሩ ተሰምተዋል።
የሁለቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት መቃቃር በድርጅቱ ውስጥ ጥርጣሬና አለመረጋጋት እንዲሰፍን አድርጎ መቆየቱንና ተቀናቃኝ የፖለቲካ ሀይሎች ይህን ክፍተት በመጠቀም ድርጅቱን ለማዳከም ሲሞክሩ መቆየታቸውን የኦሮምያ ብልፅግና አባላት ይናገራሉ።
ከዚህ ሳምንት ጀምሮ የኦሮምያ ክልል ባለስልጣናት ግጭትና ሁከት ወደ በረታባቸው አካባቢዎች ተጉዘው ከህብረተሰቡ ጋር ለመወያየት ዕቅድ እንዳላቸውም ስምተናል።
Filed in: Amharic