>
5:18 pm - Friday June 15, 6068

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የቀረበ ምክረ ሐሳብ   (አቻምየለህ ታምሩ)

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የቀረበ ምክረ ሐሳብ   

አቻምየለህ ታምሩ
(1) መግቢያ 
 
ኢትዮጵያ ባለፈው  ግማሽ ምዕት ዓመት ውስጥ  ችግር ተለይቷት ባያውቅም ባለፉት ጥቂት ዓመታት ግን ባለፉት ኀምሳ ዓመታት ውስጥ  ሲዘራ የቆየውን ፖለቲካ አዝመራ ምርት እያጨደት ትገኛለች። በተለይ ዐቢይ አሕመድ ስልጣን ከያዘ በኋላ የኦሮሞ ብሔርተኞች ግንባር ፈጥረው ኦሮሚያ በሚባለው የጥንት የአማራ፣ የጋፋት-አማራ እና የሌሎችን ነባር ኢትዮጵያውን ዐጽመ ርስት ውስጥ በሚኖረው አማራ ላይ ሕጻን፣ ነፍሰ ጡር፣ አራስ፣  አሮጊትና ሽማግሌ  ሳይሉ በመንግስታዊ መዋቅሩ ተጠቅመው ጅምላ ፍጅትና የንብረት ማውደም እያካሄዱ ይገኛሉ። በሚስጥር ተቀድቶ በቅርቡ ለሕዝብ ይፋ ከተደረገው የሽመልስ አብዲሳ  ድርጅታዊ የስራ አፈጻጸም ሪፖርት የሰኔ 23ቱ አማራ ላይ ያነጣጠረ የዘር ፍጅት በዐቢይ አሕመድ አገዛዝ  ዝግጅት፣ ቅንጅትና ድርጅቱ የተፈጸመ ስለመሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም። የአገዛዙ ቁንጮ ዐቢይ አሕመድና ግብረ በላዎቹ በሻሽመኔ፣ በአርሲ፣ በባሌ፣ በሐረርጌና በዝዋይ የተፈጸመው የዘር ማጥፋት ተድበስብሶ እንዲታለፍና ዓለም እንዳያውቀው ታትረው በመስራት ላይ የሚገኙት የዝግጅቱ፣ የቅንጅቱና የድርጅቱ አካል መሆናቸውን ስለሚያውቁ እንጂ የዘር ማጥፋቱ ግንባር ቀደም ተዋናይ የሆኑት ቄሮዎች መታወቂያ እየጠየቁና አስቀድመው ባዘጋጁት የስም ዝርዝር መሰረት ያካሄዱትን የዘር ማጥፋት መካድ የዘር ማጥፋት ወንጀሉ አካል መሆኑን ስለማያውቁ አይደለም።
ከሽመልስ አብዲሳ የስራ አፈጻጸም ሪፖርት የዐቢይ አሕመድ አገዛዝ አላማ በታሪክ የጸናውን የኢትዮጵያን ማንነት ሙሉ በሙሉ በመደምሰስ  ኢትዮጵያን የምታህል ኦሮምያቸውን መፍጠር መሆኑ በግልጽ ተነግሯል።
ብአንዴን የሚባለው ከአማራ ሕዝብ ባሕል፣ ታሪክ እና እሴት የተፋቱ፣ እንጥፍጣፊ ኢትዮጵያዊነት፣ ኅሊና እና ወገናዊነት የሌላቸው ወያኔዎች “ገ’ለን ቀብረነዋል” ያሉት አማራ መቃብሩን ፈንቅሎ እንዳይወጣ መቃብር ጠባቂ እንዲሆኑ ተደርገው የተፈጠሩት ወንጀለኞች ማኅበርም  ይህንን  የሽመልስ አብዲሳን ድርጅታዊ የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ኦነጋውያንን ሳይቀር  በሚያስደንቅ አኳኋን ከለላ ሰጥቶታል።
በመሆኑም ኢትዮጵያውያን ሁሉ ካሁን በኋላ ሁለት አማራጮች ከፊታቸው ተደቅነዋል። አንደኛው አማራጭ ሁሉም ተረባርቦ በሽመልስ አብዲሳ አንደበት የተነገረውን የዐቢይ አሕመድ አገዛዝ የዘር  ናዚያዊና ፋሽስታዊ የዘር ማጥፋት የፖለቲካ ፕሮጀክት ማክሸፍ ነው።
ሁለተኛው አማራጭ  ደግሞ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ እንደተደረገው ሁሉ ነፍሰ ጡር እና አራስ ሴቶችን ጨምሮ ንጹሐን ኢትዮጵያውያን በብአዴን ሁለንተናዊ ከለላ አክራሪና ጨካኝ የኦሮሞ ብሔርተኞች ሲፈጁ፣ የኢትዮጵያ ቅርስና ታሪክ ሲያወድሙና ኢትዮጵያን የምታህል ኦሮምያቸውን ሲገነቡ እንደሌላ አገር ዜጋ ዝም ብሎ መመልከት ነው።
የኢትዮጵያና የአማራ ስም እንኳን ሲነሣ የሚያማቸውን ሕወሓቶችን በሰውል ልጅ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ታማኝነት ሕወሓትን በማገልገል ከሁሉ በላይ ኢትዮጵያን ያዳከሟት ብአዴኖች ናቸው። ብአዴኖች አገራቸውን የሚወዱ ብቃት ያላቸው ዜጎች ምንም አይነት ሚና እንዳይኖራቸው መንገዱን በመዝጋት የሁለት ሳምንት አራስ ወልዳ ከተኛችበት አልጋ ጎትተው በመውሰድ በድንጋይ ቀጥቅጠው የሚገሉ፣ የ9 ወር ነፍሰጡር በሕጻናት ልጆቿና በባሏ ፊት አስቃይተው የሚገሉ፣ ታመው ሀኪም ቤት የተኙ አዛውንቶችን ቆራርጠው የሚገሉ ጨካኞች አገሩን እንዲረከቡ አድርገዋታል። በመሆኑም ባሁኑ ጊዜ የማይሰጠው አጣዳፊ ስራ የተቀማነውን አገራችንን ከኦሮሞ  ብሔርተኞች  እና ለሕወሓት እንዳደረጉት ሁሉ ሳይሰስቱ ማንኛውንም አይነት ከለላና ድጋፍ ከሚያደርጉላቸው ከብአዴን መንጋጋ ማውጣትና የንጹሐንን ሕይዎት መታደግም ነው።
አገራችንን የተቀማነው ባለፉት ግማሽ ምዕት ዓመት ውስጥ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የነበሩ የተማሪ ፖለቲከኞች አማራን እና ኢትዮጵያን የሚያስጠሉ ግራ ዘመም ትርክቶችን ከአዕምሯቸው አንቅተው በፈጠሩት የልቦለድ ታሪክ ነው። የተቀማነው አገራችን ለመንጠቅ “ታሪክ ከጥንቱ፣ ነገር ከመሰረቱ” እንዲሉ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግር ስረ መሰረቱን መመርመር ያስፈልጋል። በአሁኑ ጊዜ የምናየው ችግር ኢትዮጵያን ከ400 ዓመት በፊት ለጥፋት የዳረገውና ታላቋን መንበረ መንግሥት በራራን ያጠፋው የግራኝ አሕመድ የሽብር ወረራና ከወረራው በኋላ የተከሰተው ጠንቅ በዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ ዘመን ሙሉ በሙሉ ያልሻረ መሆኑን የሚያመልክት ነው። የኢትዮጵያ መሰረታዊ ችግር ከሌሎች አገሮች ጋር የሚመሳሰልበትም የሚለይበትም አለ። የዓለማችን ብዙ አገሮች የጸኑትና በብዙ ደም አፋሳሽ ግጭት አልፈው ነው። በብዙ አገሮች የተከሰቱ ደም አፋሳሽ ግጭቶች መነሻ የሆኑት ሐሰተኛ ታሪክ ነው። አገራት ሐሰተኛ ትርክቶች ከፈጠሩት ጥፋቶች የዳኑት በታሪክ ላይ በመግባባታቸው ነው። በሌሎች አገሮች እንደተደረገው ሁሉ  ኢትዮጵያም የሐሰት ትርክት ፈጥረው የዘር ፍጅት እያካሄዱ ከሚገኙ የኦሮሞ ብሔርተኞች ጥፋት የምትድነው በታሪካችን ላይ መግባባት ስንችል ብቻ ነው።
የኦሮሞ ብሔርተኞች  ኦሮሞ ባልሆነውና ኦሮሞ አይመስልም በሚሉት ላይ ፍጅት እያካሄዱ ያሉት በዳግማዊ ምኒልክ ተወርረናል የሚል የሐሰት ትርክት ፈጥረው ነው። ዳግማዊ ምኒልክ ግን ኦሮሞ በወረራ ከያዘው መሬት በላይ  ጨምረው በመስጠት ባለርስት አደረጉት እንጂ ከኦሮሞ የወሰዱት አንድ ኢንቺ መሬት የለም። በተፈተጉ የታሪክ ማስረጃዎች የተደገፈውን ይህንን  የታሪክ እውነት ግን በፈጠራ ታሪክ የተመሰረቱት ኦነጋውያን ሊቀበሉት  አይፈልጉም። ፖል ሄንዚ እንዳለው ኦሮሞን በምኒልክ የተጠቃና ለደረሰበትም ጥቃት ፍትህ ያላገኘ አስመስለው በማቅረብ  ላይ የተጠመዱት ኦነጋውያን ስለታሪካቸው የራሳቸው አመለካከት ሊኖራቸው ይችላል፤  መብታቸው ነው፤ ሆኖም ግን  የነሱን የተመረጡ ተረቶች ሌሎች የኢትዮጵያ ነገዶች እንደ ታሪክ እንዲቀበሉት መጠየቅ አይችሉም። ኦነጋውያን ራሳቸው የፈጠሯቸውን የተመረጡ  ተረቶች  ወደማመን ስለተሸጋገሩ በታሪክ በነባርነት አንጻር ኦሮሞ በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ነገዶች ሁሉ በጣም አዲስ መጤ (ገብ) ሕዝብ መሆኑን የሚያሳዩ በዘመኑ የተመዘገቡ የታሪክ ማስረጃዎችን የዲግሪ ማሟያ ወረቀቶቻቸውን ሲጽፉ እንጅ  የኦሮሞ ወጣቶችን ለማስተማር አይጠቀሟቸውም።  ለዲግሪ  ማሟያ በሚያቀርቡት ጽሑፍ ግን አውሮፓውያን ወደ ሰሜን አሜሪካ እና ነጮች ወደ ደቡብ አፍሪካ የገቡበት ጊዜ ኦሮሞዎች በአብዛኛው የኢትዮጵያ አውራጃዎችን ከወረሩበት ጊዜ እንደሚረዝም ይጽፋሉ።
በዚህ ጽሑፍ የፈጠራ ታሪክ ቀስው የፈጠረባቸው አገራት ችግራቸውን በምን አኳኋን መፍትሔ እንዳገኙለት፤ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ መግባባት ለመፍጠር የእርቅና የእውነት አፈላላጊ ኮሚሽን ምስረታ አስፈላጊነት መሆኑን፤ ለእውነተኛ እርቅ እና ዘላቂ ሰላም  በታሪካችን ለተበደሉ ወገኖች የካሣና የአዎንታዊ እርምጃ አስፈላጊነትና  በነባር ነገዶች፣ ሰፋሪዎችና መጤዎች መካከል የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት ነባር ነገዶች ርስታቸውን ለማስመለስ ያካሄዷቸውን እንቅስቃሴዎች በመዳሰስ ከታሪካዊ ችግሮቻችን የምንገላገልባቸውን የመፍትሔ ሀሳቦች አቀርባለሁ።
 
(2) የሐሰት ታሪክ ችግርና መፍትሔው 
 
የሐሰት ትርክት በመፍጠር የጀርመን ናዚዎች፣ የጣሊያን ፋሽስቶች  እና የቀድሞዋ ሶቬት ኅብረት አምባገነን መሪዎች በአውሮፓና በዓለም ሕዝብ ያደረሱትን እልቂት ታሪክ መዝግቦታል። ነገር ግን እንደናዚዎች እና ፋሽስቶች ባይሆንም ታሪክን ማፋለስ በዲሞክርሲያዊ ሥርዓት በሚተዳደሩ የአውሮፓ አገሮችም የነበረና አሁንም  ድረስ ያለ ችግር መሆኑን የአውሮፓ ኅብረት የባሕል ትብብር ምክር ቤት በ1999 ዓ.ም. ያስጠናው ጥናት ያረጋግጣል። በጥናቱ መሰረት በታሪክ ላይ ከሚሰሩ ሐጢያቶች ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል፤ “የታሪክ ሐቆችን መካድ፣ የውሸት ታሪክ መፍጠር፣ ከአንድ የታሪክ ሁነት ላይ ተቸክሎ መቅረት፣ በድንቁርና እና በስንፈት የታሪክን ሐቅ መዝለል፣ ታሪክን ለፈለጉት ዓላማ ማዋል” (“abuse by denial of historical facts, by falsification, by fixation on a particular event, by omission, out of laziness or ignorance, by exploitation for extraneous purposes, to name but a few”)[1]።
በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ለተከሰተው ውድመት መነሻ የሆኑ የሐሰት ታሪኮችን ለመሻር እና የታሪክ ትምሕርትን ለማሻሻል የአውሮፓ ኅብረት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ትኩረት ሰጥተው ሰርተዋል። ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላም በምስራቅ አውሮፓ ለግጭት ምክንያት የሆኑ በየጊዜው የተፈጠሩ ሐሰተኛ ትርክቶችንም በእውነተኛ ታሪክ እንዲታረቁ ከፍተኛ ስራ ሰርተዋል። የአውሮፓ ምክር ቤት የምኒስትሮች ጉባዔ እንደአውሮፓ አቆጣጠር በጥቅምት ወር 2001 ዓ.ም. በ771ኛው ስብሰባው ላይ የታሪክን ትምሕርት በሚመለከት የሚከተለውን ወስኗል፤  “የሐሰት ታሪክ መጻፍና ታሪክን ማዛባት በሕግ በተደነገገው ከአውሮፓ ምክር ቤት ዋና መርሕ ጋር አብሮ አይሄድም” (“the falsification and manipulation of history are incompatible with the fundamental principles of the Councils of Europe as defined in its statute”)[2]።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ግጭትን ለማስቀረት የተጠቀመበት አይነተኛ መሳሪያ ትምህርትን ነበር። ይህ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መመሪያ “ትምሕርት ለሰላም” (“Education for Peace”) በመባል ይታወቃል። ይህ የትምሕርት መመሪያ ዓላማው “ለሰዎች ሙሉ የሰብእና እድገት ለማምጣትና ለሰብአዊ መብቶች እና መሰረታዊ ነፃነት መከበርን ለማጠናከር ነው” (“Education shall be directed to the full development of the human personality and to the strengthening of respect for human rights and fundamental freedoms”)[3]።  በተጨማሪም የሰላም ትምሕርት አላማ ማህበራዊ ፍትሕን፣ በነገዶች መካከል መቻቻልን እና ወዳጅነትን ማስፈን ነው።
በአውሮፓ የሚሰጠው የታሪክ ትምሕርት ዓላማም ከሰላም ትምህርት ዓላማዎች ጋር ተመሳሳይ ነበር። የታሪክ ትምሕርትን ሰላም የማስፈን ተልእኮ ለማረጋገጥ እንዲረዳ በታሪክ በጠላትነት ይተያዩ የነበሩ፣ ብዙ ጦርነት ያደርጉ የተለያዩ አገሮችን የታሪክ መማሪያ መጽሐፍትን በጋራ መጻፍ ተጀመረ (“common history textbook projects”)። የጋራ ታሪክ መጽሐፍ ዋና ተግባር እርቅ ማውረድ ሳይሆን የአንዱ አገር ዜጎች የሌላውን አገር የታሪክ ሁነቶችና ችግር እንዲያውቁ በማድረግ የጋራ መግባባት እንዲፈጠር በማስቻል ለእውነተኛ እርቅ መሰረት መጣል ነው። ለዚሕ ግጭት የማይለያቸውን የደቡብ ምስራቅ የአውሮፓ አገሮች፣ የፈረንሣይ-ጀርመንና የፖላንድ-ጀርመን የጋራ የታሪክ መማሪያ መጽሐፍት ዝግጅቶች ለአብነት መጥቀስ ይቻላል[4]።
ስለዚህ የታሪክ ትምሕርት ቀስ በቀስ “እኛ-እነሱ” (“Us-Them”) የሚለውን አሉታዊ ስሜትንና ቁርሾን የሚቀንሥ፣ የግጭትና የጦርነት ታሪክ ባላቸው ወገኖች መካከል መግባባትንና እርቅ እንዲፈጠር የሚያደርግ እንደዋና ሰላም የማረጋገጫ መሳሪያ እየታየ መጥቷል። የጋራ ታሪክ መጽሐፍ ፕሮጀክት ለግጭት የሚጋብዙና ግጭትን የሚያበረታቱ ሐሰተኛ ተለዋጭ ትርክቶችን (“Alternative Interpretations”) ለማረቅ እንዲሁም በአንዳንድ ሁኔታዎች የሚያግባቡ የጋራ ታሪካዊ ትርክቶችን ለማጎልበት ይረዳል። በተጨማሪም የታሪክ ትምሕርት በሰላም ትምሕርት ማዕቀፍ ውስጥ በተቀረጸው መሰረት ለግጭት መንሴ በሆኑ ነገሮች ላይ በማነጣጠር ለሌላው ወገን አድሎአዊነትን እና ጭፍን ጥላቻን በመቀነስ የጋራ አመለካከቶችን እና አጠቃላይ ማንነቶችን ያዳብራል[5]።
እ.ኤ.አ. ከ1990ዎቹ ጀምሮ በአውሮፓ ምክር ቤት እና በአሜሪካ የሰላም ተቋም (United States Institute of Peace, USPI) አማካኝነት ብዙ የታሪክ መማሪያ መጽሐፍት ክለሣና የአስተማሪዎች ስልጥና ስራዎች ተሰርተዋል። በተጨማሪም የአውሮፓ ፓርላማ የአውሮፓን ታሪክ መማርና ማስተማርን በሚመለከት፣ የመማሪያ መጽሐፍትን ለማረምና ለማሻሻል የተለያዩ የውሳኔ ሀሳቦችን አሳልፏል [Recommendation 1111 (1989), Recommendation 1283 (1996) ይመለከቷል]።  በተጨማሪም በአውሮፓውያኑ 19ኛው መደበኛ ጉባዔ በተካሄደው ስብሰባ ላይ በአውሮፓ ትምህርት የጋራ ጉዳዮች ላይ የውሳኔ ሀሳብ አሳልፏል። እነዚሕና ሌሎችም የውሳኔ ሐሳቦችና መርሀ ግብሮች ዋና አላማ የታሪክ ትምህርትን ለማሻሻልና አውሮፓውያን ለውጭ አገር ሰዎች ያላቸውን ጥላቻና አሉታዊ አመለካከቶች ለመቀነስ ነው[6]። እንደዚህ አይነት አላማ ያለውን የታሪክ ትምህርት ከይዘቱ በመነሳት የሰላም ትምህርት ብንለው የሚበዛበር አይሆንም።
የሰላም ትምህርት  የጋራ የታሪክ መጽሐፍት ፕሮጄክቶች በጠላትነት የሚተያዩ ወይም እንዲተያዩ የተደረጉ ወገኖችን ወደወዳጅነት እና አንድነት ለማሸጋገር  የሚያስችል የታሪክ  ትረካዎች ማዕቀፍ ነው። ይህን በመከተል ነው አገራት የራስን ነገድ ከፍ ከፍ የሚያደርግና ሌሎችን ዝቅ የሚያደርግ እና አግላይ የሆነውን አሰተሳሰብ ሌሎችን ነገዶችና አገሮችን በአዎንታዊ አመለካከትና አካታች በሆነ የአገር ፍቅር አስተሳሰቦች የሚተኩት። በነገዶች መካከል በታሪክ የነበሩ ትብብሮች፣ የወዳጅነት ምሳሌዎች፣ እንዲሁም በሰላም አብሮ የመኖር ታሪክ በሥርዓተ ትምሕርት ሲቀርብ፣ የጋራ ታሪክንና የአብሮነትን ግንዛቤ እንዲፈጠር መሰረታዊ ስራዎችን ለማጎልበት ያግዛሉ። የሰላም ትምሕርት ማዕቀፉ የጋራ ታሪክ ፕሮጀክቶች በድሕረ ግጭት ማኅበረሰብ ውስጥ የሁሉንም አካላት ስሕተትን ነቅሶ በማውጣት የማስታረቅን ውስብስብ ስራን በአግባቡ ለመስራት ያስችላቸዋል[7]።
ነገር ግን የጋራ ታሪክ መጻሕፍት ዓላማ ማኅበረሰቦችን ለማስታረቅ ሲባል ብቻ በተለያዩ ኃይሎች የተፈጸሙ ጭካኔ የተሞላባቸውን ድርጊቶች መካድ ወይም ችላ ማለት አይደለም። ያለፉ የግጭት ታሪኮችን መንስኤዎችንና ያስከተሉትን ጉዳት በትክክለኛ መረጃ ተመስርቶ ማሳወቅና ማስረዳት በራሱ ጎጅ የሆነውን ጠባብ የነገድ ስሜትንና የዘውግ ፖለቲካን ይደፍቀዋል፣ ያረግበዋል፣ ይሸረሽረዋል። የጋራ ታሪክ ፕሮጀክት ልዩነት ላይ ብቻ ሳያተኩር፣ የታሪክ ሁነቶችንም ሳያዛባ በማቅረብ በግጭት ያለፉ ማኅበረሰቦችን እንዱ ሌላውን እንዲረዳና ወደአንድነት እንዲመጡ መንገድ ይጠርጋል ማለት ነው። ለአንድነት ሲባል በታሪክ የተፈጸሙ አሉታዊ ሁነቶችን መካድ ፍትህን አያሰፍንም፣ አንድነትም አያመጣም። ታሪክን መካድ አደገኛ “የግብረ ገብነት ክፍተት ይፈጥራል፣ የሚዛናዊነትን እሴት ያጠፋል” (“Ddenying them would result in dangerous moral relativism”)[8]።
 
(3) የእርቅና የእውነት አፈላላጊ ኮሚሽን ምስረታ አስፈላጊነት  
 
እርቀ ሰላምና አብሮነት ውስብስብ፣ ረጅም ጊዜ የሚፈጅ ሰላምን ለማስፈን የሚደረግ የእውነት ፍለጋ አድካሚ ስራ ነው። የእርቅ ሂደት ማኅበረሰቦች፣ ቡድኖች እና አገሮች በሰላም አብሮ ለመኖር ያላቸውን ፍላጎት፣ ግጭቶችን በዘላቂው ለመፍታትና ግጭቶች ከፈጠሩት የበቀል ስሜት ለመውጣት፣ አንዱ ሌላውን ለመረዳትና ለመተማመን ያላቸውን ፍላጎት ያሳያል[9]። የጠፉ ሰዎችን ጉዳይና በታሪክ የተፈጸሙ ወንጀሎችን መርማሪ ጉባዔዎች ወይም ኮሚሽኖች በክፍለ አሕጉራዊ ፍርድ ቤቶች፣ በአገር ውስጥ ፍርድ ቤቶች ወይንም በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤቶች ሊቋቋሙና ሊሰየሙ ይችላሉ። የእርቅና የእውነት አፈላላጊ ጉባዔዎች የሰብአዊ መብት ጥሰቶችንና የታሪክ ወንጀሎችን መጥንና ስፋት፣ ያስከተሉትን ጉዳት እና ምክንያታቸውን ለመረዳት መረጃ ይሰበስባሉ[10]።
የእርቅና የእውነት አፈላላጊው ኮሚሽን ስራ ታላቅ ግብ የተደበቁ፣ የተካዱና አከራካሪ ወይም አጨቃጫቂ  እንዲሆኑ የተደረጉን የታሪክ ሁነቶች በሕዝቡ ዘንድ በማሳወቅ እና ግንዛቤ በማስጨበጥ ድምጽ አልባ የሆኑትን የታሪክ ተጎጅዎች ታሪካቸው እንዲታወቅ ማስቻል ነው። የእርቅና የእውነት አፈላላጊ ኮሚሽን ወደፊት የሚከሰቱ ግጭቶችን ለማስቀረት የመርኅና የተቋም ማሻሻያ እንዲደረግ በጥናት የተደገፍ ምክርና አስተያየት ይሰጣል። ነገር ግን የተደበቁና የተካዱ የታሪክ ሁነቶችን በማሳወቅና ግንዛቤ በመፍጠር ብቻ ዘላቂ ሰላምና እርቅ አይመጣም። የታሪክ ተሞክሮ እንደሚያሳየው አንዳንድ ወገኖች ይቅር ለማለት የተደበቀውን እውነት እንዲታወቅ ከማድረግ የዘለለ፣ ተጨባጭ ነገር ይፈልጋሉ። እውነተኛ እርቅ ብዙ ጊዜ የሚፈልግ ዘገምተኛ ሂደት ነው። ስለዚህ የእርቅና የእውነት አፈላላጊ ደርግ ስራ እውነተኛ እርቅና ሰላም ለማምጣት ከሚያስፈልጉ ነገሮች አንዱ ተደርጎ መታየት አለበት። የእርቅና የእውነት አፈላላጊ ደርግ ስራ ብቻውን ዘላቂ ሰላም እና እርቅ አያመጣም።  ስለእርቅና የእውነት አፈላላጊ ኮሚሽኖች አሰራር፣ ስልጣን እና ተዛማጅ ጉዳዮች የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ያወጣውን መመሪያና ምክረ ሐሰብ እንደኢትዮጵያ ላሉ አገሮች በጣም ጠቃሚ ስለሆነ መከተል ይቻላል[11]።
 
(4) የካሣና የአወንታዊ እርምጃ አስፈላጊነት ለእውነተኛ እርቅ እና ዘላቂ ሰላም 
በታሪክ ጉዳት የደረሰባቸውን ማኅበረሰቦች እና ቡድኖች በሚገባ ከተረዱ በኋላ የእርቅና የእውነት አፈላላጊ ኮሚሽኖች ብዙ ጊዜ ስራቸውን የሚያጠናቅቁት ስለካሳ አስፈላጊነት እና የካሳው አይነት ጠንካራ አስተያየትና የምክረ ሐሳብ ዘገባ በመጻፍ ነው። ካሳን በሚመለክት አይነቱና መጠኑ እንደየአገሮቹ የታሪክ አውድ የተለያየ ነው። ከዚህ በፊት በነበሩት የእርቅና የእውነት አፈላላጊ ኮሚሽኖች  ብዙ ጊዜ የሚካተቱት የካሳ አይነቶች ለተጎጅዎች የተለየ የትምሕርት ዕድል፣ የገንዘብ ካሳ እና ሌሎች እርምጃዎች እና ጥቅማ ጥቅሞች ናቸው። የካሳ መርሀ ግብሮች ብዙ ጊዜ ተፈጻሚነቱ ውስብስብ ሊሆን ስለሚችል የእርቅና የእውነት አፈላላጊ ኮሚሽኖች በቂ ጊዜ ወስደውና የባለሙያ እውቀትን ተጠቅመው የካሳን አፈጻጸም፣ ጊዜና አይነት መወሰን ይጠበቅባቸዋል። በተጨማሪም የካሳው አይነትና መጠን የእርቅና የእውነት አፈላላጊ ኮሚሽኖች በሚያቀርቡት መረጃ መሰረት በሌላ ወገን ሊወሰን ይችላል[12]።
 
(5) ነባር ነገዶች፣ ሰፋሪዎችና መጤዎችን በተመለከተ  
 
በታሪክ ርስታቸውን በመጤዎች እና በሰፋሪዎች እርስታቸውን የተነቀሉ ነባር ነገዶች መብት በተባበሩት መንግሥታተ ድርጅት ትኩረት እያገኘ መጥቷል። እ.ኤ.አ. ከ1995 ጀምሮ እስከ 2004 ዓ.ም. ያሉት አስርት ዓመታት የባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም የነባር ሕዝቦችን ዓመታት ተብለው ተሰይመዋል (“United Nations International Decade of the World’s Indigenous Peoples”)። በተባበሩት መንግሥታት ስር የነባር ነገዶች ቋሚ መድረክ የተቋቋመው እና ጠቅላላ ጉባኤው ስለነባር ነገዶች መብት የሚመለከት ውሳኔ የተላለፈ በዚኽው ጊዜ ነበር[13]። በታሪክ ርስታቸው የተነቀሉት ነበር ነገዶች ከደረሰባቸው ጉዳት እንዲያገግሙ ርስታቸው ወሳኝ እንደሆነ ግልጽ እየሆነ መጥቷል። በአሜሪካ፣ በደቡብ አፍሪካ እና በአውስትራሊያ የሚገኙ የነባር ነገዶች ቁጥራቸው የሣሣ፣ ባሕላቸው እና ቋንቋቸው የተዳከመበት በአውሮፓውያን ሰፋሪ ቅኝ ገዢዎች በሐይል ከርስታቸው ስለተነቀሉ ነው። በነዚኽ አገሮች የሚገኙ ነባር ነገዶች ከ1960ዎቹ ጀምሮ በተለይም ደግሞ በቅርብ ጊዜ ርስታቸውን ማስመለስ አደጋ ላይ ያለውን ሕልዎናቸውን ለማረጋገጥና የደከመውን ባሕላቸውን ለማደስ ወሳኝ መሆኑን ስለተረዱት ከፍተኛ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ነበሩ፤ አሁንም እያደረጉ ነው[14]።
 
(6) የነባር ነገዶች ርስት የማስመለስ እንቅስቃሴ 
 
ነባር ነገዶች ርስታቸውን ለማስመለስ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ካደረጉባቸውና አሁንም እያደርጉ ካሉበት አገሮች ውስጥ አንዱ አውስትራሊያ ነው። እ.ኤ.አ. በ1992 ዓ.ም. የአውስትራሊያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንግዝሊዞች አገሩን በያዙበት ጊዜ የማንም አልነበረም የሚለውን የቆየ የሐሰት ትርክትና የባለቤትነት ሕጋዊ መብት ሊሽረው ችሏል። ይህ የነባር ነገዶች የትግል ውጤት ሲሆን መሬታቸውንና መብታቸውን ለማስመለስ በሚያደርጉት ትግል አንድ እርምጃ ወደፊት እንዲጓዙ ያደረገ ውሳኔ ነው። ምንም እንኳ በመሬቱ ላይ ያለውን የመንግሥት ሉአላዊ ስልጣን ባይሽረውም በክፍት መሬቶች ላይ ነባር ነገዶች የባለቤትነት መብት መጠየቅ እንደሚችሉ ሕጉ ይፈቅዳል[15]። እ.ኤ.አ.  በ1991 ዓ.ም. አውስትራሊያ በነባር ነገዶች እና ነባር ባልሆኑት መካከል እርቀ ሰላም እንዲወርድ የእርቅ ሂደቱን የሚመራ የነባር ነገዶች የእርቅ ምክር ቤት (“Council for Aboriginal Reconciliation”) በአዋጅ አቋቁመዋል። ምክር ቤቱን ለማቋቋም ያስፈለገበትን መነሻ ምክንያት በአዋጁ መግቢያ ላይ ተዘርዝሯል፤
a) Australia was occupied by Aboriginal and Torres Strait Islanders who had settled for thousands of years, before British settlement at Sydney Cove on 26 January 1788; and
b) Many Aboriginal and Torres Strait Islanders suffered dispossession and dispersal from their traditional lands by the British Crown;
c) To date, there has been no formal process of reconciliation between Aboriginal and Torres Strait Islanders and other Australians; and
d) By the year 2001, the centenary of Federation, it is most desirable that there be such a reconciliation; and
e) As part of the reconciliation process, the Commonwealth will seek an ongoing national commitment from governments at all levels to cooperate and to coordinate with the Aboriginal and Torres Strait Islander Commission as appropriate to address progressively Aboriginal disadvantage and aspirations in relation to land, housing, law and justice, cultural heritage, education, employment, health, infrastructure, economic development and any other relevant matters in the decade leading to the centenary of Federation, 2001. [16]
 
ትርጉም፤ 
 
(ሀ) እ.ኤ.አ. በጥር 26 ቀን 1788  እንግሊዞች በሲድኒ ኮቪ ሰፈራ ከመጀመራቸው በፊት አውስትራሊያ አቦርጂናልና የቶሬስ ስትሬት  ደሴት ነዋሪዎች  በመባል የሚታወቁ ነባር ነገዶች ለብዙ ሽህ ዓመታት ይኖሩበት ነበር፤  እናም
(ለ) ብዙ ነባር አቦርጂናልና የቶሬስ ስትሬት  ደሴት ነዋሪዎች በእንግሊዝ መንግሥት ከርስታቸው እንዲነቀሉና እንዲበታተኑ ተደርገዋል፤
(ሐ) እስከአሁንም ድረስ አቦርጂናልና የቶሬስ ስትሬት  ደሴት ነዋሪዎች እና በሌሎች አውስትራሊያዊያን መካከል እርቀ ሰላም አልወረደም፤ እናም
(መ) በፌደሬሽኑ መቶኛ ዓመት በሚከበርበት በ2001 ዓመት እንዲህ አይነት እርቅ መኖሩ በጣም አስፈላጊ ነው፤
(ሠ) እንደ እርቅ ሂደቱ አንድ አካል የ[አውስትራሊያ] የጋራ ብልጽና በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አካላት እንደአስፈላጊነቱ ደረጃ በደረጃ የነባሮችን ችግር ለመቅረፍ እና የነባሮችን የመሬት፣ የቤት፣ የሕግና ፍትህ፣ የባሕል ቅርስ፣ የትምሕርት፣ የሥራ እድል፣ የመሰረተ ልማት፣ የኢኮኖሚያዊ እድገት ፍላጎቶችና እና ሌሎች አስፈላጊ ጉዳዮችን ፊደረሽኑ የተመሰረተበት መቶኛ ዓመት እስከሚከበርበት እስከ2001 ዓ.ም. ድረስ ባሉት አሥር ዓመታት ውስጥ ለማሟላት ከአቦርጂናልና የቶሬስ ስትሬት  ደሴት ነዋሪዎች ኮሚሽን ጋር ለመተባበርና በቅንጅት ለመስራት ቁርጠኛ እንዲሆኑ ይጠይቃል።
በተመሣሣይ በካናዳም በ1973 ዓ.ም. የነባር ሕዝቦችን የርስት ጥያቄ የሚመለከት ሕግ ወጥቷል። የካናዳ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ነባር ነገዶች በክፍት መሬቶች ያላቸውን መብት ተቀብሎታል[17]። ምንም እንኳ በአሁኑ ጊዜ በወረራ፣ በኃይል እና በግጭት የተፈጠሩ ድንበሮች ሕጋዊነት ተቀባይነት ቢኖራቸውም ከርስታቸው የተነቀሉት ነባር ነገዶች እስከአሁንም ድረስ የባለርስትነት መብታቸውን ይጠይቃሉ። የታሪካዊ የርስት ባለቤትነት ጥያቄ ለነባር ነገዶች አስፈላጊና ፍትሐዊ ጥያቄ ነው፤ ምክንያቱም ከርስታቸው የተነቀሉ ሳይፈቅዱ በኃይል እና በሕግ ወጥ መንገድ ስለሆነ ነው[18]።
እንደካናዳና እንደአውስትራሊያ ሁሉ በአሜሪካም የነባር ነገዶች መብት ተሟጋቾች በሕግ ወጥ መንገድ ከ18ኛ ምዕት ዓመት መጨረሻ ጀምሮ እስከ 1900 ዓ. ም. ድረስ የርስቱ ባለቤቶች ሳይፈቅዱ የተወሰደው 809 371 284. 48 ሄክታር የሚገመት መሬት ለባለቤቶቹ እንዲመለስ እንቅስቃሴ ሲያደርግጉ ቆይተዋል። የነባር ነገዶች መብት ተሟጋቾች አሜሪካ መሬቱን ያለምንም ካሳ በኃይል ስለያዘችው ለባለቤቶቹ እንድትመልስ የሞራል ግዴታ አለባት ብለው ይከራከራሉ። በአጠቃላይ የአሜሪካ አንድ ሶስተኛው ግዛት በሕግ ወጥ መንገድ ነባር ሕዝቦችን በመንቀል የተያዘ ነው[19]። ሰለዚህ ጉዳይ ሰፊ ጥናት ያደረገው በርክ ሄንድሪክ የነባር ነገዶች የርስት መብት ተሟጋቾችን መከራከሪያ እንደሚቀጥለው ያሰቀምተዋል፣
In short, some people believe rights to ownership are natural rights and ought not to be reshaped with some idealized social contractors in mind. These rights must instead be protected; and where properties were stolen, they must be returned if possible, and if not possible, some suitable form of reparation must be offered. [20]
 
ትርጉም፤  
በአጭሩ አንዳንድ ሰዎች የርስት ባለቤትነት መብት የተፈጥሮ መብት ነው ብለው ያምናሉ እናም አንዳንድ ከማሕበራዊ ርዕዮት አስተሳሰቦች ጋር ለማስታረቅ ሲባል መቀየር የለባቸውም። እነዚህ መብቶች ይልቁንም መከበር አለባቸው፣ የተሰረቁም ካሉ የሚቻል ከሆነ [ለባለቤቶቹ] መመለስ አለባቸው፣ የማይቻል ከሆነ ደግሞ ተመጣታኝ ካሳ መሰጠት አለበት። የተፈጥሮ የርስት ባለቤትነት መብት ዋና መከራከሪያ ነጥብ ወራሪዎች እና መጤዎች የነባር ሕዝቦችን መሬት የያዙበትን መንገድ ሕግወጥ ስለሆነ የባለቤትነት መብታቸው እንደተጠበቀ ነው የሚል ነው። በርክ ሄንድሪክ ይህን ጉዳይ እንደሚከተለው ይገልጸዋል፣
Instead, what matters is the means by which particular holdings were acquired—if properties were originally acquired from nature without injustice and have been transferred freely by their owners up until the present time, then those who now hold them have natural rights to do so. If holdings were expropriated at any point, on the other hand, then justice requires that these properties be returned to their original owners or (where this is not possible) to their heirs. [21]
 
ትርጉም፤ 
 
ዋናው ነገር መሬቱ የተያዘበት መንገድ ነው—መሬት መጀመሪያ የተያዘው ድንግሉን መሬት በማቅናት ያለግፍ ከሆነና ባለቤቶች በነጻ እስከአሁን ድረስ ለሌላው ወገን ያስተላለፉት ከሆነ የአሁኑ ባለቤቶች በባለቤትነት ለመያዝ የተፈጥሮ መብት አላቸው። በሌላ በኩል የመሬት ይዞታ በአንድ ወቅት በኃይል የተቀማ ከሆነ ለፍትህ ሲባል ንብረቱ ለመጀመሪያው ባለቤቶች ወይም (ይህ የማይቻል ከሆነ) ለወራሾቻቸው እንዲመለሱ ያስፈልጋል። ስለዚህ ምንም እንኳ ብዙ ትውልዶች ቢያልፉም ባለቤቶች ጨርሰው እስካልጠፉ ድረስ በተነቀሉት ርስታቸው ላይ ያላቸው የተፈጥሮ የባለቤትነት መብት እንደጸና ይኖራል።
 
(7) ኢትዮጵያ ከታሪካዊ  ችግሮቿ  እንድተገላገል  ምን ማድረግ ይኖርብናል?
 
ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ በምትገኝበት አደጋ ላይ የወደቀችው  የኢትዮጵያ ችግር ታሪክ ነው ያሉ ብሔርተኞች ባካሄዱት ትግል ነው። ዛሬ በአገራችን በአማራ፣ በኦርቶዶክስ ክርስቲያንና ኦሮሞ አትመስሉም በተባሉ የኢትዮጵያ ነገዶች ላይ ኦሮምያ በሚባለው ክልል ውስጥ እየተፈጸመ ያለው የዘር ፍጅት ውልደቱ የኢትዮጵያ ችግር ታሪክ  በሚል ትርክት የተካሄደው  የኦነግ ፖለቲካ ነው። በፈጠራ ታሪክ ላይ የተመሰረተው የኦነግ ፖለቲካ መሰረቱ  ሰፋሪ፣ መጤ፣ ሰፋሪ ቅኝ ገዢ፣ ወዘተ የሚላቸውን  ኦሮምያ በሚባለው ክልል ውስጥ የሚኖሩ  ኦሮሞ ያልሆኑ  የኅብረተሰብ ክፍሎችን በመፍጀት ኦሮሞ ካልሆኑ ነገዶች የጸዳች ኦሮምያ የምትባል አገር መመስረት ነው። ኦነጋውያን ከአቅም ማነስ በስተቀር ይህን እውን ለማድረግ ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር ብቻ  ከሰይጣንም ጋር ቢሆን ይወዳጃሉ። ኦሮሞ ካልሆኑ ኢትዮጵያውያን  እንድትጸዳ የምትፈለገው የኦነግ ኦሮምያ ግን የኦሮሞ አጥመ ርስት አይደለችም።  ርስት  ደግሞ የፈለገው ሰው ቢሰፍርበት ባላቤቶቹ ጨርሰው እስካልጠፉ ድረስ ያለ ብርቱ ነገር አይለቀቅም። ለዚህም ነው ያገራችን ሰው “ርስት በሺሕ ዓመቱ ለባለቤቱ” የሚለው።
በመሆኑም ርስት ያለ ብርቱ ነገር ስለማይለቀቅና ተወረርን የሚሉን ኦነጋውያን በሌላው ርስት ላይ መስፈራቸውን ረስተውት ሌላውን መጤና ሰፋሪ እያሉ ኦሮሞ ባልሆኑ ነባር ኢትዮጵያውያን ላይ የዘር ማጥፋት  ማካሄደን ፖለቲካቸው አድርገውት አብሮ መኖር ስለማይቻል ቀደም ሲል  ባየነው ኦሮሞ ኢትዮጵያን ከመውረሩ በፊት  የነባር ነገዶችን ርስት በወረሩ የሌሎች አገሮች አለማቀፍ ተሞክሮ እንዳየነው  የራሱ ያልነበረን የሰው ርስት የወረረ ማነው?  በሌላው ላይ በደል ያደረሰው ማነው? በታሪክ ሂደት በደል ያደረሰ ማነው? መጤና ሰፋሪ  ማነው?  የሚሉ ጉዳዮች ውስጥ መግባት  ደም መፋሰስ ለማስቆም በእጅጉ ወሳኝ ነው።
ለዚህም ላለፉት 400 ዓመታት፣ ማለትም የኦሮሞ የገዢ መደብ ኢትዮጵያን ከወረረ በኋላ፣ የተፈጸመውን ግፍ ፣ የዘር ማጥፋት፣ ርስት መንቀልና እና ጥፋት የሚመረምር፤ ውሳኔውና ግኝቱ አስገዳጅ የሆነ አለማቀፋዊ የእርቅና እውነት አፈላላጊ ኮሚሽን ሊቋቋም ይገባል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተቋቋመው እንዲህ አይነት አለማቅርፋዊ የእርቅና የእውነት አፈላላጊ ኮሚሽኖችን በመደገፍ የዓለም ሰላምን ማስጠበቅ ስለሆነ  ይህን የሚቋቋመው ኮሚሽንም ዓለም አቀፍ ድጋፎች ስላሉት እንዴትና በምን መልኩ ይቋቋም የሚለው ራስ ምታት ሊሆን አይችልም። ይህ አለማቀፍ ኮሚሽን በኢትዮጵያ ታሪክ የነበሩ የነባር ነገዶችን፣ የሰፋሪዎችና የመጤዎች ታሪክ በተመለከተ አለማቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ምርመራ ያካሂዳል፤ ሰፋሪዎችና መጤዎች በነባር የኢትዮጵያ ነገዶች ላይ ላደረሱት ጥፋት ማካካሻ የሚሆን ተመጣጣኝ የካሣና የአወንታዊ እርምጃ ድንጋጌዎችን ያወጣል።
ዳግማዊ ምኒልክ ወሮኛል፣ ማንነቴን አጥፍቷል፣ ርስቴን ወስዷል፣ ጨፍጭፎኛል፣ የፊንፊኔ መሬት ይገባኛል፣ ወዘተ ሲል የሚል ኦነጋዊ ሁሉ አለኝ የሚለውን የታሪክ ማስረጃ  ሁሉ ለዚህ ኮሚሽን ማቅረብና ከታሪክ እንዲቀዳ የሚፈልገውን መብት  ማግኘት የግድ ይለዋል። እኛም አለን የምንለውን የታሪክ እውነት ለአለማቀፋዊው የእርቅና እውነት አጣሪ ኮሚሽኑ ማቅረብና ፍርዳችንን መቀበል የግድ ይለናል። ባለፉት አስርት ዓመታት በመሰረቱት የፈጠራ ታሪክ ሰክረው የተመረጡ ተረቶችን አረፋ እየደፈቁ  ላንቃቸው እስኪሰነጠቅ ድረስ እየጮሁና በየዕለቱ አዳዲስ ተረት ተረቶችን እያመረቱ የኦሮሞ ወጣቶችን ኦሮሞ ያልሆኑት ነገዶችን  እንዲያጠቁ ሲያሰለጥኑ የሚውሉ ኦነጋውያን ሁሉ  በእውነት ላይ ለሚመሰረት አለማቀፋዊ ፍትሕ በመቆም እውነተኛነታቸውን በአለም ፊት ማስመስከር አባቶቻችን ከሚሏቸው ከአባገዳዎችና  እኛ አባቶቻችን ከምንላቸው አርበኞቻችን ወንጀል የፈጸመው ቢኖር እንዲክስ፣ የሌላውን ቅድመ አያት አጽመ ርስት የያዘውን ማንኛውንም መሬት ቢኖር ወደ ትክክለኛው ባለቤቶች እንዲመለስ ለሚበይነው  አለማቀፋዊው የኮሚሽኑ ውሳኔ መገዛት የግድ ይላል። ይህ በኔ አምነት የ 400 ዓመት ደም መፋሰስ እና ጥፋት እንዲያበቃ ያደርጋል ብየ አምናለሁ።
 
ምንጮች፡
 
[1]. Council of Europe, The Misuses of History (Strasbourg: Council of Europe, 2000), 5.]
[2].  Karina V. Korostelina, “Introduction Part 2: Peace Education and Joint History Textbook Projects,” in History Education and Post-Conflict Reconciliation: Reconsidering Joint History Textbook Projects, ed. Karina V. Korostelina and Simone Lässig (New York, Routledge, 2013), 20]
[3]. UN, Article 26, the Universal Declaration of Human Rights, 1948, online at: www. Ohchr.org/EN/UDHR/Pages/Introduction.aspx (accessed June 2020)]
[4]. Simone Lässig, “Introduction Part 1: Post-Conflict Reconciliation and Joint History Textbooks Projects,” in History Education and Post-Conflict Reconciliation: Reconsidering Joint History Textbook Projects, ed. Karina V. Korostelina and Simone Lässig (New York, Routledge, 2013), 7, 8 and 11]
[5]. Karina Korostelina, “Peace Education and Joint History textbook projects,” 19 ]
[6]. Korostelina, “Peace Education and Joint History textbook projects,” 21-22; E. A. Cole and J. Barsalou, Unite or Divide? The Challenges of Teaching History in Societies Emerging from Violent Conflict, USIP Special Report, Washington, DC.: USIP Press, 2006 (https://www.usip.org/sites/default/files/resources/sr163.pdf); Council of Europe, Lessons in History: The Council of Europe and the Teaching of History, Strasburg, Council of Europe Publishing, 1999; Council of Europe, The Misuses of History, Strasburg: Council of Europe Publishing, 2000 (https://www.coe.int/en/web/history-teaching/the-misuse-of-history); L. M. de Puig (rapporteur), Recommendation 1283 (1996) on History and the Learning of History in Europe, Report of the Committee on Culture and Education, Strasburg, Council of Europe, 1996 (https://assembly.coe.int/nw/xml/XRef/Xref-XML2HTML-en.asp?fileid=15317&lang=en); C. Gallagher, History Teaching and the Promotion of Democratic Values and Tolerance—A Handbook for Teachers, Strasburg: Council of Europe, 1996.
[7]. Korostelina, “Peace Education and Joint History textbook projects,” 21-22.
[8]. Korostelina, “Peace Education and Joint History textbook projects,” 23.
[9]. Lässig, “Post-Conflict Reconciliation and Joint History Textbooks Projects,” 7.
[10]. Office of the United Nations High Commissioners for Human Rights, Rule-of-Law Tools for Post-Conflict States: Truth Commissions (New York/Geneva, 2006), 1-2.
[11]. Office of the United Nations High Commissioners for Human Rights, Rule-of-Law Tools for Post-Conflict States: Truth Commissions (New York/Geneva, 2006), 1-2.
[12]. Office of the United Nations High Commissioners for Human Rights, Rule-of-Law Tools for Post-Conflict States: Truth Commissions (New York/Geneva, 2006), 28.
[13]. Paul Keal, European Conquest and the Rights of Indigenous Peoples: The Moral Backwardness of the International Society (Cambridge: Cambridge University Press, 2003), 114.
[14]. Keal, European Conquest and the Rights of Indigenous Peoples, 122-123.
[15]. Keal, European Conquest and the Rights of Indigenous Peoples, 124.
[16]. Damien Short, Reconciliation and Colonial Power: Indigenous Rights in Australia (Ashgate, 2008), 1-2; Council for Aboriginal Reconciliation Act 1991, https://www.legislation.gov.au/Details/C2004C03090, accessed 11 August 2020.
[17]. Keal, European Conquest and the Rights of Indigenous Peoples, 125.
[18]. Burke A. Hendrix, Ownership, Authority, and Self-Determination (University Park: Pennsylvania State University Press, 2008), 30.
[19]. Hendrix, Ownership, Authority, and Self-Determination, 35-36.
[20]. Hendrix, Ownership, Authority, and Self-Determination, 42.
[21]. Hendrix, Ownership, Authority, and Self-Determination, 44-45.
Filed in: Amharic