>

ኦነግ ሸኔ እና ባንዲራዉ - የባከኑ እሴቶች! (ታዬ ደንደኣ)

ኦነግ ሸኔ እና ባንዲራዉ – የባከኑ እሴቶች!

ታዬ ደንደኣ

የዛሬን አያድርገዉና ግራዝማች ግሪሳም “ኦነግ ዳግም ላይጠገን ተሰብሯል” ብሎ ነበር!
 
* ኦነግነት እና ባንዲራዉ ወያኔ በኦሮሞ ላይ የዘረጋዉ አዕምሯዊ እና አካላዊ እስር ቤት ነበር!
 
አንድ ወቅት ላይ ኦነግና ባንዲራዉ በኦሮሞ ዘንድ ክብር ነበራቸዉ። እኔም ድርጅቱ የኦሮሞን ህዝብ ጥቅም የሚያስከብር መስሎኝ በዚያ መስመር ዋጋ ከፍዬ ነበር።  በኋላ የተደራጀ አሻጋሪ ሀሳብ የሌለበት የአቧራ ስብስብ መሆኑን ተረዳሁ። ከስሙ እና ከባንዲራዉ በስተቀር ምንም ተጨባጭ ነገር አልነበረም። ባንዲራዉን እና ስሙን የሚጠቀመዉ ደግሞ የጌታቸዉ አሰፋ መዋቅር ነበር።
አምቦ ላይ ሀጫሉን ወንጅሎ ለማሰር የጌታቸዉ መዋቅር ባንዲራዉን ሲያሰራጭ በጄነራል ደቻሳ ቢትማ መያዙን በOBN ሰምተናል።
ጌታቸዉ አሰፋ የኦሮሞ ባለሀብቶችን በኦነግነት ፈርጆ ባንዲራዉን በማልበስ ይዘርፋል። ያኔ ህወሀት በኦነግ አመለካከት የኦህዴድ ታጋዮችን ያሸማቅቅ ነበር። ተማሪ እና አስተማሪ በዚያ ስም ታስሮ ይሰቃያል። በተጨባጭ ግን ኦነግነት እና ባንዲራዉ ወያኔ በኦሮሞ ላይ የዘረጋዉ አዕምሯዊ እና አካላዊ እስር ቤት ነበር ማለት ይቻላል። የዛሬን አያድርገዉና ግራዝማች ግሪሳም “ኦነግ ዳግም ላይጠገን ተሰብሯል” ብሎ ነበር። የወያኔ አሻንጉሊት እንደሆነ ያዉቅ ነበር!
ኦነግ ሸኔ ያንሰራራዉ ከህወሀት ዉድቀት በኋላ መሆኑ ይታወቃል። ህወሀት ኦነግነትን ተጠቅሞ ስልጣን ላይ እንደቆየ ሁሉ ያንኑ ተጠቅሞ ከወደቀበት ለመነሳት ይሞክራል። ባንዲራዉንም በለመደዉ መንገድ ለመጠቀም ሲጣጣር ይታያል። በቅርቡ ለንደን ላይ የሆነዉ እዉነታዉን ያሳያል። በኢትዮጵያ ኤምበሲ ላይ ባንዲራዉን ገልብጦ ሰቅሏል። ግን ምን ያደርጋል?  ህወሀት በከንቱ ይለፋል! ዉሃ የወሰደዉ አረፋ ይጨብጣል። ሀሳብ አልባ ስብስብ ራሱን በራሱ ጠልፎ ይጥላል። የኦሮሞና የኢትዮጵያ ህዝብ በልጆቹ ውድ መስዋእትነት ያመጠዉን ነፃነት ነቅቶና ተባብሮ ለማሻገር ወስኗል! በኦሮሞ ዘንድ ገናና የነበረዉ ስም እና የሚወደደዉ ባንዲራ በወያኔና በሸኔ ሲበላሽ ግን ያሳዝናል! በድርጅቱ ዉስጥ በቅንነት ሲታገሉ የነበሩትን እዉነተኛ ታጋዮች ማፅናናት ይገባል!
Filed in: Amharic