ሀገር የምትፀናው በጥበብና በሃይል ሚዛን ነው!
ቴዎድሮ ሀይለማርያም
የፌዴሬሽን ምክር ቤት የፊታችን ቅዳሜ 30/2012 የሚያደርገው አስቸኳይ ስብሰባ ምን ይዞ ይመጣ ይሆን? በአዲስ ዓመት ዋዜማ ሁሉም ወገን በጉጉት የሚጠብቀውና የሀገሪቱን እጣፈንታ የሚወስን ታላቅ ታሪካዊ ስብሰባ ነው፡፡ በዋነኝነት ኢትዮጵያ ወደ አንድ የተማከለ መንግሥት አገዛዝ ትሰበሰባለች ወይስ ወደ ሁለትና ከዛ በላይ ነፃ ሀገረ መንግሥታት ትበታተናለች የሚለው ጉዳይ መቋጫ ማግኘት አለበት፡፡
በአንድ ሀገር ሁለት መንግሥት አናርኪ ነው!
ጠ/ሚ አብይ እስከዛሬ የመንግሥት ያለህ! የመሪ ያለህ! ቢባል አንጀታቸው የማይጨክንባቸውና መንግሥታቸው የማይደርስባቸው ሁለቱ ስስ ብልቶቻቸው ኦሮሚያና ትግራይ ብቻ ነበሩ፡፡ በኦሮሚያ ፅንፈኛ ብሄርተኞችና የኃይማኖት አክራሪዎች የክልሉንና የፖርቲውን መዋቅር ወርሰው እንዳሻቸው አንገት ሲቀነጥሱ ፣ ደም ሲያፈሱ ፣ ሀብት ንብረት ሲዘርፉና ሲያወድሙ አብይ እንደ ሀገር መሪም እንደ ሰውም አንዲት ቃል ትንፍሽ አላሉም፡፡
በትግራይም ሰው በላው ህወሃት አንሰራርቶ ሀገር የማተራመስና የማፍረስ ስራውን በይፋ እንዲቀጥል ፈቅደዋል፡፡ የትግራይ ህዝብ የህወሃት አፈና ኢላማና የፍላጎቱ ማስፈፀሚያ እንዲሆን ትተውታል፡፡ የወልቃይትና ራያ አማሮችን ለተባባሰ የዘር ማጥፋትና ሰብአዊ ወንጀል አሳልፈው ሰጥተዋል።
መንግሥት ጥምረት የፈጠሩበትን የኦሮሞ ፅንፈኞችንና ህወሃትን በአንቀልባ አዝሎ የቆየው “በሃይል ብንሞክር ያዋርዱናል” ብሎ ሊሆን ይችላል። የሰላም አማራጭ ካለ እስከ መጨረሻዋ ደቂቃ ላሟጥ ብሎም ይሆናል። ወይም ሌላ ከለምለሙ ሳር ጀርባ ለህዝብ የተሸሸገ ትልቅ ገደል ሊኖርም ይችላል።
አሁን ግን ምንም ይሁን ምን በኦሮሚያ ከሚደረገው የዘር ማጥፋትና ታላቅ መንግሥታዊ ዝርፊያ በላይ የፅንፈኛው ሃይል ጀብደኝነት ለአብይ መንግሥት ህልውና ስጋት መደቀኑ እርምጃውን አስገዳጅ አድርጎታል፡፡ በሌላ በኩል ህወሃት የፌዴራሉ መንግሥት የመሃል ሀገር ስራውን እስኪጨርስ ጊዜ መስጠቱ የሚያስከትልበትን የመነጠል አደጋ ለማስቀረት ፍጥጫው በግድም በውድም እልባት እንዲያገኝ ቆርጧል፡፡
በኢትዮጵያ ህዝብ ኪሳራ ትግራይን መገንጠል አይቻልም!
ወያኔ—ህወሃት ሀገር ለመሸጥና ለመገንጠል አዲስ አይደለም። ከፍጥረቱ እስከ እርጅናው ሲያልም የኖረው ኢትዮጵያን አፍርሶ ፣ አማራን አጥፍቶ ፣ ትግራይን ነፃ ሀገር ማድረግ ነው። እኛ በተገኘው አጋጣሚ እየተደለልን ብንረሳውም ቅሉ ዛሬም ህወሃት በትግራይ ምርጫ ካላካሄድኩ ብሎ ለገራዥ ያስቸገረው ያደገበት ኮሮጆ ግልበጣ ናፍቆት አይደለም። ትግራይን “ከዲፋክቶ” ሀገረ መንግሥትነት ሙሉ “ህጋዊ” ነፃነት ለማጎናፀፍ ነው። ምፀቱ ግንጠላውን በኢትዮጵያ ህዝብ ኪሳራ ለማድረግ መከጀሉ ነው።
‹‹አፄ በጉልበቱ›› ህወሃት ገና ለገና መጪው የፌዴሬሽን ም/ቤት ስብሰባ የሚያስከትለውን በመፍራት ዛሬ 28 ነሃሴ 2012 ዓ.ም በትግራይ ክልል ካቢኔ አማካኝነት ዛቻና ማስፈራሪያ ቢጤ አውጥቷል፡፡ ምርጫዬን የሚያስተጓጉል አንዳች ውሳኔ ቢወሰን በቀጥታ ጠቅላይ ሚኒስትሩንና ምክር ቤቱን ተጠያቂ በማድረግ ጦርነት እንደታወጀብኝ እቆጥረዋለሁ ፣ ተገቢውን አፀፋ ምላሽ እሰጣለሁ ብሏል፡፡ እንግዲህ የፈራ ይመለስ!
ሁለት ሀገር ስለሌለን በኢትዮጵያ አንቀልድም!
የዶ/ር አብይ መንግሥት ከእንግዲህ ‹‹በሰባራ ወንበር›› ተንጠልጥሎ የመቆየት እድሉ እያከተመ ነው፡፡ ሉዓላዊ ሥልጣኑን የሚገዳደሩ ሃይሎችን ተሸክሞ ፣ ጉልበተኞች ሀገር ሲያተራምሱ የዝሆን ጆሮ ሰጥቶ ማለፍ አይችልም፡፡ መንግሥት ከሁለት ዓመታት በላይ ሲገፋው የከረመው የብሄራዊ ደህንነትና ሉዓላዊነት ማስጠበቅ ጉዳይ አግጥጦ መጥቷል።
አሁን የራሱንም የሀገሩንም ህልውና የሚያስጠብቅ ቁርጠኛ የፖለቲካ አመራር ያስፈልጋል፡፡ በወያኔ ግብረ አበርነት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የፈፀመውን ግፍ እንዲክስ ታሪክ ሁለተኛ እድል የሰጠችው የአሁኑ ብልፅግና አመራር በቅዳሜው ውሳኔው ማንነቱን ለአንዴና ለመጨረሻ ገሃድ ያድርጋል፡፡ ወይ ከታሪክ ጎን አለያም ከታሪክ በተቃራኒ ይሰለፋል፡፡
አብይ ከልብ የህዝብ መሪ ቢሆኑ ኖሮ ገና እንደመጡ ከሁሉም ክልል በላይ የደገፋቸው የትግራይ ህዝብ ነበር፡፡ እንዳለመታደል ከህወሃት መንጋጋ ሊታደጉት አልቻሉም፡፡ አማራውንም ፣ አዲስ አበቤውንም ፣ ደቡቡንም ፣ ሶማሌውንም ፣ ጋምቤላውንም በሙሉ አክባሪያቸውን ህዝብ ከዘር አጥፊዎችና ከጉልበተኞች መከላከል አልቻሉም፡፡
ሀገር የምትጠበቀው በጥበብና በሃይል ሚዛን ነው። ሃይልም ከምንም በላይ ህዝብ ነው፡፡ መንግሥት ሰላም ፣ ህግ ፣ ድርድር አሻፈረኝ ያለውን ሽፍታ ቡድን በሚገባው የእሳትና ብረት ቋንቋ ማናገር ስራው ነው፡፡ ስለዚህ የፌዴሬሽን ም/ቤት ህወሃት በአስቸኳይ ህገወጥ ምርጫውን አቁሞ ወደ ሰላማዊ መንገድ ካልተመለሰ ማናቸውንም አስገዳጅ እርምጃ መንግሥት እንዲወስድ ውሳኔ ማሳለፍ አለበት፡፡
የሀገር መከላከያ ሠራዊትም የሀገር ሉዓላዊነትና ህገ መንግሥታዊ ስርዓቱን በሃይል ጭምር ማስጠበቅ ግዴታ አለበት፡፡ መለዮ የለበሰው ከሀገር ሉዓላዊነት በላይ ለምን ሊቆም ነው? መንግሥት በፊናው ምድር የጠላችውን ህወሃት የሚባል ወንጀለኛ አደብ ማስገዛት ካቃተው ይሄን አምኖ ሥልጣኑን ለህዝብ ማስረከብ ግዴታው ነው።
ጠ/ሚ አብይ በእንዲህ ያለ ወቅት ከተደበቁበት ጓዳ ወጥተው ከኢትዮጵያ ህዝብ ጎን በመቆም ቁርጠኛ አመራር መስጠት አለባቸው። እስካሁን ሲያፈቅራቸው የገፉትን ህዝብ በይቅርታ ጥሪ ከጎናቸው ካሰለፉ የኢትዮጵያን ህልውና በማዳን ታሪክ የሚሰሩበት እድል ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ካልሆነ በታሪክ መዝገብ ቀርቶ በግራፊቲም አይታወሱም፡፡
ሁለት ሀገር የሌለን ዜጎች ፣ ተቋማት ፣ ቡድኖች ፣ ድርጅቶች ኢትዮጵያ ስትፈርስ ፣ ህዝባችን ለዳግም ግፍና መከራ ሲዳረግ በዝምታ አንመለከትም፡፡ ከእንግዲህ የህወሃትና ጋሻ ጃግሬዎቹን የጥፋት ተግባር ‹‹የወንድማማቾች ፀብ›› ብለን ልንዳለል አንችልም፡፡ በደቡብም ይምጣ በሰሜን ሀገር አፍራሾችንና የህዝብ ጠላቶችን ለመመከት አስፈላጊውን መስዋእትነት ለመክፈል መዘጋጀት አለብን።
አዲሱን ዓመት የሰው ልጅ ጠላቶችን ለመፋለም ቃል የምንገባበት ያድርግልን!