>
5:13 pm - Wednesday April 19, 3854

በሀገራችን ላፈጠጠው አደገኛ ነገ፤ ዋዜማ (አንዱ ዓለም ተፈራ)

በሀገራችን ላፈጠጠው አደገኛ ነገ፤ ዋዜማ

አንዱ ዓለም ተፈራ


ውድ ኢትዮጵያዊያን

ክፍለ ዘመናትን ባስቆጠረው የአገራችን ታሪክ፤ ብዙ አጣብቂኝ ፈተናዎች ተከስተዋል። ከውጭ በመጡ ጠላቶች እስከ አገር በበቀሉ ተንኳሾች፤ ኢትዮጵያዊያን ብዙ ችግሮችን አሳልፈዋል። በሂደቱ ብዙ መስዋዕት ተከፍሏል። አገራችን ከዚህ ሁሉ ወጥታ፤ ሰፍታም ሆነ ጠባ፤ ለኛ ደርሳናለች። በዚህ በአገራችን ታሪክ፤ የተገፋ ክፍል ወይንም ያልጎፋ ክፍል፤ የተቀየመ ወይንም ያላስቀየመ፣ ከሁሉ ንጹህ ሆኖ እጁን አጥፎ የተቀመጠ አንድ አካባቢ አለ ብሎ መናገር ይከብዳል። ይሄን ያልኩበት፤ በሥልጣን ላይ የነበሩት የተለያዩ ገዥ ክፍሎች፤ በጊዜው በሚያውቁትና በነበረው አግቦት፤ ልኔ የቀረበ ላሉት ሳያዳሉና፤ ራቅ ያለ ላሉት ደግሞ ሳይበድሉ አላለፉምና ነው! የዚያ መመዘኛ፤ የራሱ የታሪክ ወቅትና የቦታው ሀቅ ነው። ዛሬ ያለንበት የአገራችን ፈተና፤ ከመቼውም በላይ ነው። ይህ አባባል በተደጋጋሚ ስለተነገረ፤ “ምን የተለዬ መጣና!” ብሎ ማለፉ፤ ፍጹም የአፈጠጠውን አደጋ አለመረዳት ነው። ይህ ከግል እምነታችንና ከግል ጥቅማችን ውጪ የሆነ ከፍተኛ ፈተና ነው። ይሄን እንዴት ማለፍ እንደምንችል አብረን ካልመከርንና የምንችለውን ካላደረግን፤ “ያኔ ይሄንን ባደርግ ኖሮ!” የሚያስብል ጊዜ አናገኝም። ውጪሰው ኢትዮጵያዊያን ሌላ አማራጭ አለን። ይሄውም፤ በያለንበት አገር ዜግነት ወስደን፤ የግል የተደላደለ ኑሮ መኖር ነው። ይቻላል! ማንም አታድርግ! ብሎ በግል የሚይዘን የለም። ወገን አፍቃሪና አገር ወዳድ ለሆን ግን፤ ይሄ አይዋጥልንም። ከፋንም ደላንም፣ በውጭ ኖርንም ወደ አገራችን ተመለስን፤ የአገራችን ሕልውና፤ በጥያቄ ውስጥ መግባት የለበትም! ይህ ነው አሁን ከፊታችን ፈጦ የተገተረው። “ለዚህማ እንዴት ዝም እላለሁ!” የምትሉ ከሆነ፤ ንባባችሁን ቀጥሉ።

ኮቬድ አይደለም። የአንድና የብዙ ሰዋች በየቦታው መገደልም አይደለም። ጉዳዩ “የኢትዮጵያ ሕልውና በክር መንጠልጠል!” ነው። አብዛኛውን ጊዜ የሚቀናን፤ “ኢትዮጵያን አምላካችን ይጠብቃታል!” “ማንም ሊያፈርሳት አይችልም!” በማለት፤ እጆቻችን ተጣጥበን፣ ኃላፊነቱን ለሌላ አስረክበን፣ የራሳችን ኑሮ መግፋት ነው። እስከዛሬ ይሄኑ በነጋ በጠባ ብለነው ብለነው አጠንዝተነዋል! አሁን ይብቃ! እያንዳንዳችን የአገር፣ የታሪክ፣ የትውልድ ኃላፊነት አለብን። በርግጥ ይሄንን አስገድዶ በተግባር ማዋያ ሕግ የለም። የሕሊና ሕግ ተገዥ መሆንን ብቻ ነው የሚጠይቀው! አሁን የአመለካከት፣ የድርጅት፣ የርዕዩተ ዓለም፣ የቁመትና የወርድ ልዩነት ቦታ የለውም! ጥያቄው አንድና አንድ ብቻ ነው። ዝርዝሩን እዚህ ማስፈሩ፤ ለቀባሪው ማስረዳት ይሆናል። እናም አልፈውና፤ ምን ይደረግ ወደሚለው እገባለሁ። አሁን በአገራችን ያሉት ሁለት ክፍሎች፤ ማለትም በሥልጣን ላይ ባለው ብልጽግና ፓርቲና በትነግ በኩል እየተደረገ ያለው ሽርጉድ፤ አስጊ ነው። እነሱ ፊታቸው ባለው ጉዳያቸው ላይ ዓይኖቻቸውን ተክለው፤ የዘመናት ታሪክ ያላትን አገራችንን የመበታተን አፋፍ ላይ አስቀምጠዋታል። ጥፋተኛው ይሄኛው ነው! ብሎ ሰፈር ለይቶ፤ እንዲህ መሆን አለበት! ማለት ቀላል ነው። ሽምግልና ይግቡ ብሎ ለሌሎች ኃላፊነትም ማሸከሙም ቀላል ነው። ያ ግን አሁን ባለንበት ሁኔታ፤ አደጋውን አያስቀረውም።

እና ምን ይደረግ! ውጪሰው ኢትዮጵያዊያን፤ ወገን አፍቃሪና አገር ወዳድ የሆን ሁሉ፤ ይህ የኔ ጉዳይ ነው! ብለን ምክክር ማድረግ አለብን። ከሩቅ ሆኖ ውጤት መጠበቅ፤ ሊከተል የሚፈልገውን ለማያውቅ ሰው የሚተው ዘዴ ነው። እኔ ግን፤ ማንም ገዛ ማን፣ ምንም ዓይነት ርዕዩተ ዓለም ተከተለም አልተከተለም፣ መጀመሪያ ኢትዮጵያ መኖር አለባት! የሚል እምነት አለኝ። ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተን እኛኑ ነው። እናም ያገባናል። ያ ብቻ ሳይሆን፤ ኃላፊነት አለብን። ስለዚህ፤ ቀርበን ተገናኝተን እንድንነጋገር ሃሳብ አቀርባለሁ። በርግጥ በዚህ ጉዳይ እያሰባችሁበት ስላልሆነ አይደለም እኔ ይሄንን ያቀረብኩት። አንዳችን የግድ መጀመር ስላለብን እው። እናደርገዋለን ለምትሉ ቅድሚያውን ልሥጣችሁ! ካልሆነ ደግሞ እኔ ኮንፈረንስ ለማዘጋጀት ዝግጁ ነኝ። ሌሎች አዘጋጅታችሁ ጥሪ ብታስተላልፉ፤ ቀድሜ እገኛለሁ። ይሄን ፈጦ የመጣ አደጋ አላውቅም የሚል ካለ፤ ራሷን በአሸዋው ውስጥ ሽጉጣ፤ ማንም አያየኝም፣ ምንም አልሰማም እንዳለችው ሰንጎ መሆን ነው።

የኢሜል አድራሻዬ፤ eske.meche@yahoo.com

Filed in: Amharic