>

'ይቅር .... ታ.... ታታ ..... ሿሿሿ'  (ያሬድ ሀይለማርያም)

ይቅር …. ታ…. ታታ ….. ሿሿሿ’ 

ያሬድ ሀይለማርያም

ትላንት የይቅርታ ቀን ተብሎ መሰየሙን እና አንዳንድ የመንግስት ባላሥልጣናት፤ እንዲሁም የኃይማኖት አባቶች ይቅርታ ሲጠይቁ እየሰማው ነው። በሃሳብ ደረጃ ነገርየው ጥሩ ነው። ይቺን ነገር አምናና፣ ካቻምናም አድርገናት ነበር። ከአምናው ይቅርታ መጠያየቅ ወዲህ በአገራችን የተፈጸሙትን ነገሮች ብቻ ማሰብ ይህ ነገር ከልብ ነው? ያስብላል። የኃይማኖት አባቶችን እና የሕዝብን ለጊዜው ልተውና በባለሥልጣናት በየአመቱ ስለሚጠየቀው ይቅታ ይችን ልል ወደድኩ።
ይቅርታ ጥፋትን እና ጸጸትን ተከትሎ የሚመጣ ነገር ነው። በፖለቲካው አውድ ጥፋት ሳይኖር ይቅርታ አይጠየቅም። ጥፋት፤ ከዛ መጸጸት፤ ከዛ ተጠያቂነት፣ ከዛ ይቅርታ ይከተላል። ፖለቲከኞች እና ባለሥልጣናት የሚፈጽሙት ጥፋት በአገር እና በሕዝብ ጥቅምና መብት ላይ ያነጣጠሩና ጉዳታቸውም ከፍ ያለ ስለሆነ ይቅርታ የሚጠይቁትም አገርን እና ሕዝብን ነው። በመሆኑም ፖለቲከኞች፤ በተለይም ባለሥልጣናት የሚጠይቁት ይቅርታ ሌላው ተራው ሰው እንደሚጠይቀው ይቅርታ ሾላ በድፍኑ አይነት ነገር አይደለም። ቢያንስ ከዚህ የሚከተሉትን የይቅርታ ቋንቋዎች እና ሃሳቦች የያዘ መሆን አለበት።
፩ኛ/ ተገልጾ ለታወቀው ጥፋት መጸጸትን መግለጽ (Expressing regret)
፪ኛ/ ለተፈጸመው ጥፋት ኃላፊነትን መውሰድ (Accepting responsibility)
፫ኛ/ የተጎዳን መካስ ወይም ያበላሹትን ማስተካከል (Making restitution)
፬ኛ/ ዳግም ተመሳሳይ ጥፋት እንዳይፈጸም የሚያስችል ከእውነተኛ ፍላጎት የመነጨ የእርምት እርምጃ (Genuinely repenting) እና
፭ኛ/ ተበዳይ ወገን ይቅርታ እንዲያረግ መጠየቅ (Requesting forgiveness)
እኔ ይሄን ካልኩኝ ዘንዳ ዛሬ አቶ ታከለ ኡማ እና ሌሎች ባለሥልጣናት በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለው “ሳናውቅ ለበደልናችሁ ይቅርታ” ያሉበትን መንገድ መፈተሽ ደግሞ የእናንተ ሥራ ይሁን። ይህ አይነቱ ይቅርታ አምና እና ካቻምና ከተደረጉት የይቅርታ ጥያቄዎች በምን ይለያሉ? ከዛስ በይቅርታው ማግስት ምን ሆነ?
እንግዲህ እኔ ፖለቲከኞች ስለሚጠይቁት የይቅርታ አይነት ከላይ ያሉትን አምስት ነጥቦች አስቀምጫለሁ። እናንተ የሹሞቹን ይቅርታ በእነዚህ መስፈርቶች እየመዘናችሁ ‘ይቅር ብለናል’ ማለቱን ለእናንተው ልተው።
እንደ እኔ የፖለቲከኞቻችን ይቅርታ ከላይ ያለውን መስፈርት እሲኪያሟላ እና ከልብ እስኪሆ ድረስ፤ ‘ይቅር …. ታ…. ታታ ….. ሿሿሿ’ ብያለሁ።
Filed in: Amharic