>

አፈወርቅ ተክሌ እና "ቪላ አልፋ"  ከበዓሉ ግርማ 1961 ዓ.ም 

 

አፈወርቅ ተክሌ እና “ቪላ አልፋ” 

ከበዓሉ ግርማ 1961 ዓ.ም
ሳሚ ዮሴፍ

አዲስ አበባ ውስጥ የተደረገውን፣ በመደረግ ላይ ያለውንና ወደፊት የሚደረገውን ሁሉ እንደ መጠጥ ብርጭቆ አንስተው የማስቀመጥ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ከተሜዎች አሉ።
ሰሞኑንም ከሰላምታ በኋላ አርዕስት ነገር አድርገው የያዙት ችግር ቢኖር ስለ አፈወርቅ ተክሌ (ወልደ ነጎድጓድ) አዲሱ የቪላ አልፋ መልክ ነው።
ትችት እንደ ተቺዎቹ የበዛ ቢሆንም አንዳንዶቹ
“ተርፎት፤ የሚሠራውን ቢያጣ ለመመጻደቅ ያደረገው ነገር ነው” ይላሉ።
ሌሎች ደግሞ (በተለይ የፍሮይድን ሳይኮሎጂ ከእጅ ጣታቸው እንደዋዛ የሚያንቆረቁሩት ተቺዎች) የዚህን ዓለም ጉዳይ ወደ ጎን ብለው….
“አፈወርቅ ከአካባቢው ውጭ ወይም በላይ ሆኖ በራሱ የፈጠራ ዓለም ውስጥ ለመኖር የሚጥር ሰው በመሆኑ ነው እንዲህ ያለውን ቪላ የሠራው” በማለት ይናገራሉ።
“ግላዊ ልዩነቱን ለመግለጽ ያደረገው ነው” የሚሉም አሉ።
ያም ሆነ ይሂ የነቀፌታዎቹ መነሾ ሠዓሊው አፈወርቅ ቪላ በመሥራቱ አይደለም። ሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎች የገነቡት በሰው አፍ አልገቡም። በግል መኖሬያቸው የሰማንያ እና የመቶ ሺህ ብር ዘመናዊ ቪላዎችን የሠሩት ዓይን አልበላቸውም።
“ታዲያ የአፈወርቅ ስም እንደ ትኩስ ድንች እያንዳንዱ አፍ ውስጥ የሚገለባበጥበት ምክንያት ምን ይሆን?” ብለን ብንጠይቅ መልሱ ሌላ ሆኖ እናገኘዋለን።
ጎንደር የሚገኘውን የአፄ ፋሲልን ግንብ የሚመስል ባለ አንድ ፎቅ መኖሪያ ቤት ባለንበት ክፍለ ዘመን በመሥራቱ ነውም
 ልዩው ነገር። ሌላ ሰው ቢያስብም ሥራ ላይ የማያውለውን ነገር አፈወርቅ ግን በመሥራቱ ነው።
የዚህ ዓይነት ቤት (ወይም ካስል) በመሥራት አፈወርቅ በዘመናችን የመጀመሪያውና የመጨረሻው ሳይሆን አይቀርም። ምክንያቱም ቤቱን የቀየሰው መሐንዲስ
G. Boscarino እንዳለው…
” እንዲህ ዓይነት ቤት ውስጥ ከአፈወርቅ በስተቀር ሌላ ሰው ቢኖርበት፣ ቤቱ አሁን ያለውን ዋጋና ጥቅም ሊሰጥ አይችልም። አዎን፤ ከአፈወርቅ በስተቀር እንዲህ ያለውን ቤት አልሞ የሚሠራ የለም። የሚሰጠውንም ጥቅምም በይበልጥ የሚያውቀው እሱ ብቻ ነው።
እንዲህ የመሰለውን መኖሪያ ቤት ለመሥራት ምን እንዳሳሰበው፣ ከተሠራ በኋላ የሚሰጠውን ጥቅም እንዲነግረኝ ጠይቄው ነበር፤ ለመናገር ፈቃዳኛ ቢሆንም ጊዜ ግን አልነበረውም። አናጢዎቹ በየደቂቃው ይጠሩታል።
በተመለሰ ቁጥር “የሀገራችን አናጢዎች ለምን አንድ መስመር በትክክል መሥራት አይችሉም” በማለት ይገረም ነበር። እነሱም በበኩላቸው እሱ አሁን በቅርብ ጊዜ የሠራውን የእንስራ ተሸካሚ ሥዕል  በተለይ ወተት መስሎ በጃኖ ጥለት የታጠረውን ቀሚሷን፣ አለንጋ የመሳሰሉት ጣቶቿንና ሕልም መሳይ ውበቷን ዓይተው መገረማቸው አልቀረም።
ገና ተመልሶ ቁጭ ከማለቱም ቀለም ቀቢዎቹ ይጠሩታል።
አዎን፤ “የሰሜን ተራራ” የተባለውን ሥዕል (ኅብረ ቀለሙ ልብ መስጦ፣ ዓይን ማርኮ፣ የአእምሮ ስላም የሚፈጥረውን) የሠራ ሰው ለተራ ቀለም ቀቢዎች ችሎታ ልዩ አድናቆት ሊኖረው አይችልም። አሁንስ አፈወርቅን የሚጠራው ሰው የለም ብዬ በመተማመን ጥያቄዬን ወርውሬ፣ ብዕሬን ከወረቀት ለማገናኘት ስቃጣ  አንድ ጽጌሬዳ አበባ የት እንደሚተክሉ የቸገራቸው፣ ወይም አበባ የያዘውን ሳጥን የት እንደሚያስቀምጡ ግራ የገባቸው ለምክር ይጠሩታል።
ሳያማክሩት ያስቀመጡት፣ ወይም የተከሉት እንደሆነ ኋላ ማንሳታቸው አይቀርም።
አፈወርቅ ደጋግሞ እንደሚለው
“ማንኛውም ነገር ከተፈጥሮ ጋር በመዋሀድ በኅብረ ቀለሙና በአቀማመጥ አቅዱ ለአእምሮ ሰላምና እረፍትን ካልሰጠ አእምሯችን ወደ ከፍተኛ ደረጃ የሚመራ ነገር የመፍጠር ችሎታ ሊኖረው አይችልም። ከተፈጥሮ ሕብረት ጋር ሥራችንን እና ኑሮአችንን ለማስተባበር ካልሞከርን ውበትን ለመፍጠር አንችልም። ለኔ ከፍተኛው ምኞቴ ይህ ነው- ኅብረት ከተፈጥሮ ጋር። ይህንን ከፍተኛ ምኞት ለመግለጽ የምፈልገው በምሠራቸው ሥዕሎች ብቻ ሳይሆን በአኗኗሬም ጭምር ነው።”
ሠራተኞቹም ደከሙ ከአንድ ሰዓት ጀምሮ ያራውጣቸው ነበር። ጥሪው እያነሰ ሄደ ቁጭ ለማለት ቻልን።
“ይህን ቤት መሥራት ከጀመርኩ ወዲህ የተማርኩት ነገር ቢኖር የቤት ሥራ ምን ያህል ብስጭትና ድካም እንደሚያስከትል ለማወቅ መቻሌን ነው። ወደ ሰላማዊ የሥዕል ሥራዬ የምመለስበት ጊዜ በመቃረቡ ደስ ይለኛል”
አለና እግሩን ዘርግቶ ወለሉ ላይ ዘፍ አለ።
በሁለት ወሩ ያልቃል ተብሎ የታሰበው ቤት አሁን አራተኛ ወሩን ሊጨርስ ነው። በአራት ወር ውስጥ አፈወርቅ ሦስት ሥዕል ብቻ ነበር ለመሥራት የቻለው። የቀረውን ጊዜ ያዋለው በቤቱ ሥራ ላይ ነው።
“ቪላ አልፋ” የተሠራው በአስር ዓመት ፕላን መሠረት ሲሆን ቤቱን ለመሥራት አፈወርቅ ከሚሸጣቸው ሥዕሎች ዋጋ አንድ ሦስተኛውን ለዚህ ፕላን  ቆጥቦ ነበር። ሆኖም የቆጠበው ገንዘብ ስላልበቃው የአዲስ አበባ ባንክ ብድር ሰጥቶታል።
ይሁንና በኔ በጠያቂው በኩል ሃያ ስድስት በሃያ ስድስት ሜትር ካሬ ሜትር ላይ አዲሱ ቤት ይህን ያህል የሚያስደንቅ ወጭ የሚጠይቅ መስሎ አልታየኝም። አፈወርቅ ስንት ገንዘብ እንደጨረሰ ትክክለኛ ዋጋውን ሊገልጽልኝ አልፈቀደም። ቤቱን የአፄ ፋሲልን ግንብ አስመስሎ ለመሥራት ያነሳሳውን ነገር ሲገልጽልኝ እንዲህ አለ…
” ስለ አፄ ፋሲል ግንብ ያለኝን አድናቆት ለመግለጽና ይህ የጥንት ቅርሳችን ተሻሽሎ ለዘመናይ ኑሮ ለመዋል መቻሉን ለማሳወቅ ነው። አዎን የኮራና የተከበረ ቅርስ እያለን የቤት ፕላን ከውጭ የምንቀዳበት ምክንያት አይታየኝም።”
አፈወርቅ ለሚሠራው ነገር ሁሉ ምክንያት አለው። በቤቱ ውስጥ ያለምክንያት የሚደረግ ነገር የለም። የአበባ ማስቀመጫው እሱ በፈለገበት ቦታ እንዲኖር የተደረገው ያለምክንያት አይደለም። የቤቱ ቆርቆርቆሮ ቀይ ቀለም የተቀባበት ምክንያት አለው። ቤቱ ነጭ ቀለም የተቀባበት ምክንያት አለው። አንድ ሥዕል አንድ ግድግዳ ላይ በአንድ በኩል እንዲሰቀል የተደረገበት ያለምክንያት አይደለም።
ቤቱ የተሠራው ለመኖሪያ ቤት ብቻ ሳይሆን ሌላ ምክንያት አለው። ቤቱም፣ ቀለሙም፣ አቀማመጡም- ሁሉም በአንድነት ተዋሕደው ኅብረት መፍጠር አለባቸው።
“ይህን የመሰለ ቤት የሠራሁበት ምክንያት አለኝ፤ የሠራኋቸው ሥዕሎች በተሠሩበት አካባቢ እንዲታዩ ለማድረግ ሲሆን፣ እንዲሁም እንግሊዝ ሀገር ተማሪ ሳለሁና በታላላቅ አውሮፓ ከተማዎች እየተዘዋወርኩ ሥዕል በምሠራበት ወቅት፣ ብዙ ሠዓሊዎች ቤታቸው ይጋብዙኝ ነበር። አሁንም በተራዬ እዚህ በመጋበዝ አንድ ኢትዮጵያዊ ሠዓሊ እንዴት እንደሚኖር ለማሰይትና ከዚህም አልፎ ከሀገራችን የታሪክ ቅርስ ጋር ለማስተዋወቅ ነው።
እንግዶቼ በውብ ነገር ተከበው ጊዜያቸውን እንዲያሳልፉ ከማድረግ ሌላ የዕለት ኑሮዬን እንዴት እንደማሳልፍ እንዲያውቁም ጭምር ነው።
ከዚህ ቀደም ቤቴ በግንብ አጥር ተከቦ ታፍኜ ስኖር ነበር። አሁን ግን የቤቱ ሰገነት ወደ ውጭና ወደ እሩቅ ለመመልከት ያስችለኛል። ሰገነቱ ላይ ወጥቼ የአዲስ አበባ ተራራዎችን ለማየት እችላለሁ። ለአንድ ሠዓሊ እንዲህ ያለው የመዝናናት ትእይንት ጠቃሚ ነው።”
አዎን ያለምክንያት የተደረገ ነገር የለም። ቤቱ አንድ ሺህ ካሬ ሜትር ላይ መሠራቱ ምክንያት አለው። የመሬት ቁጠባን ለማስተማር ነው። ሦስቱ መስኮቶች ሦስት ዓይነት ቀለማት የተቀቡት ምክንያት አለው። የፀሐይዋን ዕለታዊ ጉዞ ተከትለው እንዲያንፀባርቁ ለማድረግ ነው። የቤቱ ክፍሎች አቀያየስ ምክንያት አላቸው። ሃምሳ አራት ሥዕሎች በአንድ ጊዜ ለማሳየት እንዲቻል ታስቦ የተደረገ ነገር ነው።
እንዲሁም እያንዳንዱ ክፍሎች ከየጠቅላይ ግዛቶች የሚገኙትን ጌጣ ጌጦች ማሳያ ሊሆን ይችላል።
የጸሎት ወይም የሀሳብ ማጠንጠኛ ክፍሉ የአክሰም ጽዮንን መልክ የያዘ ነው። የሚስጥር በሩ ያለምክንያት አልተሠራም።
አፈወርቅ ካንዱ ክፍል ወደ ሌላ ሳይታይ ለመዘዋወር እንዲችል ነው።
የጋራጁም ስፋትና ቀለም ያለምክንያት አልተደረገም። ሁለት መኪናዎች እንዲይዝ ከመሆኑም በላይ የጋራጁ ቀለም ከመኪናዎቹ ቀለም ጋር ተዋሕዶ ኅብረትን ለመፍጠር እንዲችል ታስቦ ነው።
አዎን በአፈወርቅ ቤት ያለምክንያት የተደረገ ነገር የለም።
በዓሉ ግርማ 
መነን መጽሔት ሚያዚያ 29 1961 ዓ.ም 
እንድምታ የጥበብ መጽሔት
Filed in: Amharic