ወይ መንቦቅቦቅ !!
ዘመድኩን በቀለ
• ተወደደም ተጠላም፣ አመንክም አላመንክም እኔ ዘመዴ አሸንፌአለሁ። ወንዳታ ዘመዴ ወጥር።
ወይ ዘመዴ ሳላስበው፣ ሳይታወቀኝ እንዲህ እንደቀልድ ባለከባድ ሚዛን ሆንኩ ማለት ነው? ደስስ ሲል ታድዬ። በፌስቡክ Live እገባለሁ ስል ተንቦቀበቀ አይደል?
#ማስታወሻ |~ • የሆነ የግል ጥቅም የቀረብኝ፣ እናቴ የሞተችብኝ ይመስል ስልክ እየደወላችሁ አይዞህ ዘመዴ እያላችሁ ልቤን ዝቅ አታድርጉት። ራሳችሁ አይዞኝ። ለእኔ አሁን ወሬ ሳይሆን ተግባር ነው የሚያስፈልገኝ። ዳይ እንደ እነሱ እነሰንተም ተንቀሳቀሱ። ከወሬ የለም ፍሬ።
•••
ከትናንት ወዲያ ከፌስቡክ ካምፓኒ ከሆኑ የሥራ ኃላፊ ዘንድ አንድ ኢሜይል ደረሰኝ። በፌስቡክ ዓለም ቆይታዬ ለመጀመሪያ ጊዜዬ ነበር ከፌስቡክ የሥራ ኃላፊዎች እንዲህ መልእክት ሲደርሰኝ። ያውም የሪሰርች ማዕከሉ ኃላፊ ነኝ ከሚሉ ሰው ነው ነበር መልእክቱ የመጣው። ፌስቡክን እንዴት ትገመግመዋለህ የሚል መጠይቅም አብሮ ነበረው። በደንብ አድርጌ ግምገማዬንም፣ መጠይቁንም ሞልቼ በተባለው የኢሜይል አድራሻ መልሼ ላኩላቸው። ቆይተው ፌስቡኬ ላይ መጻፍ እችል ዘንድ አረንጓዴ መብራት አበሩልኝ። እኔም ሙከራ ፩፣፪፣፫ ብዬ አየር ላይ ዋልኩኝ። 23 ሺ ሰዎችም ላይክ አደረጉት።
•••
ዛሬ ደግሞ የማዕዶታችንን ሕጋዊ ፈቃድ ማግኘት አስመልክቼ የምሥራች ለኦርቶዶክሳውያን የተዋሕዶ ልጆች በሙሉ ብዬ አበሰርኩ። በአንድ ሰዓት ውስጥም የፌስቡኩ ዓለም በባለ ማዕተቦች የደስታ ማዕበል ተጥለቀለቀ። ብዙም ሳይቆይ ደግመው ፌስቡኮች ሄጵ አሉብኝ መሰለኝ። የኮሚዩኒቲ እስታንዳርድ አላሟላህም ብለው ይኸው መልሰው ዘጉብኝ። እንደ ህጻን ልጅ እንቁልልጬ ማለት ግን ደስ አይልም። እንዴት ቢፈሩኝ ነው ግን በማርያም። ከምር አንበሳ ነኝ። ብራቮ ዘመዴ አንት የሥላሴ ባርያ የድንግል አሽከር። ወጥር ዘመዴ !!
•••
በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ 144 ሺ 366 ሰዎች ዘንድ መልእክቱ መድረሱን፣ 1 ሺ ሰው ኮመንት መስጠቱን፣ 2ሺ 500 ሰዎች ሼር 8ሺ 9 መቶ ሰዎች ደግሞ ላይክ ማድረግ እንደጀመሩ ፌስቡክ ውስጥ ያሉት ፀረ ተዋሕዶ ኢትዮጵያውያን አኮረፉ። በምሥራቅ አፍሪካ ኬንያ ያለችው የፌስቡክ ተወካይዋ ኢትዮጵያዊትም ቅር አላት መሰለኝ። አዲስ አበባ ያለው የብልጽግናና የኢዜማ ሠራዊትም ተንበጫበጨ። “ኔት ወርክ አጌነስት ሄት እስፒች” ተብሎ የተቋቋመው የእነ ዮሐንስ ሞላም ድርጅት ተቀየመኝ መሰለኝ የጋሽ ማርቆሱ ፌስቡክ ድርጅት ፌስቡኬን ለእኔ ብቻ እንዲታይ አድርጎ መቆለፉን ተረዳሁ።
•••
እኔ እንደሁ ወዳጄ እጄን አልሰጥ። ሞቼ መቃብር እስክወርድ እጄን አልሰጥ። ተስፋም አልቆርጥ። እኔ ዘመዴ በሚሆነው ሁሉ አልነጫነጭም፣ አላለቃቅስም። በተገኘው መድረክ፣ በተገኘው ቀዳዳ ሁሉ የመናገር ነፃነቴን በመጠቀም እንደ ዜጋ ስለ ሃገሬ፣ እንደ አማኝ ስለ ሃይማኖቴ መለማመዴን፣ መናገሬን፣ መመስከሬን እንደሁ አላቋርጥም። እኔን ከፌስቡክም፣ ከዩቲዩብም በማባረር ማስቆም አይቻልም። ከዘንዶውም ጋር ውጊያዬ ይቀጥላል። አዛኝቷ፣ አማላጂቱ የጌታዬ እናት ድንግል ወላዲተ አምላክ ከእኔ ጋር ስላለች ምንም አልሆንም። ቅዱስ ሚካኤል በቀኜ፣ ቅዱስ ገብርኤል ከፊቴ፣ አባቴ ተክልዬ፣ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ክርስቶስ ሠምራዬ፣ ሰማእቷ ቅድስት አርሴማን ይዤማ አልሸነፍም። ፈረሰኛው ቅዱስ ጊዮርጊስ የትሄዶ? እመኑኝ አሸንፋለሁ። “ለሰው ሁሉ ከሚሆነው በቀር ምንም ፈተና አልደረሰባችሁም፤ ነገር ግን ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፥ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል።” 1ኛ ቆሮ 10፥13
•••
ኦርቶዶክሳውያን የተዋሕዶ ልጆች ሆይ። እንግዲህ ልብ በሉ። መንፈሳዊ እልህን፣ እጅ ያለመስጠትን፣ በአጋጣሚ በድንገት የወደቁበት ሥፍራ ላይ፣ የወደቁበት ጭቃ ላይ ተቀምጦም ያለማለቃቀስን፣ እዬዬ ያለማለትን ከእኔ ተማሩ። ያለ ገንዘብ፣ ያለ በጀት፣ ያለ ቢሮ፣ ያለ ኮሚቴ። በአንዲት ደቃቃ አሮጌ ስልክ ብቻ ዓለሙን ሁሉ ማስጨነቅ እንደሚቻልም ከእኔ ከታናሻችሁ ተማሩ። ለልጆቻችሁም ንገሩ። ብዙዎች በኦርቶዶክሳዊነታቸው ላለመጽናት፣ ሃይማኖታቸውን ለመቀየር፣ እንደምክንያት የሚደረድሩት፣ ለጊዜው በመራባቸው፣ በመጠማታቸው በሆዳቸው ምክንያት ፈተናን ለመቋቋም ባለመቻላቸው መታገስ ያቅታቸውና ይኮበልላሉ። ፈተና ሲበዛ እንደ ብረት እንደመጠንከር እንደ ሸክላ ይፍረከረካሉ። ተዋሕዶን ለመካድም ብዙ ምክንያትም ይደረድራሉ። እናንተ ግን እንዲህች ብላችሁ ተዋሕዶን እንዳትለቁ። እንዲች አድርጋችሁ ተስፋም እንዳትቆርጡ። ሰይጣን የሚዘጋው አንድ ሁለት በሮችን ብቻ ነው። እግዚአብሔር ግን 99999999 ያልተዘጉ በሮችን ብርግድ ወለል አድርጎ ከፍቶ ይጠብቃችኋል። እናም አሁን በእኔ ላይ የሚፈጸመውን ግፍ እያያችሁ እንዲች ብላችሁ እንዳትናደዱ፣ እንዳትበሳጩ፣ እንዳትነጫነጩም። “ይህም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን መከራ ትዕግሥትን እንዲያደርግ፥ ትዕግሥትም ፈተናን ፈተናም ተስፋን እንዲያደርግ እያወቅን፥ በመከራችን ደግሞ እንመካለን፤” ሮሜ 5፥3-4
•••
እኔ ባልጽፍ ባልናገርም እኮ ኢትዮጵያ እንደሁ ትነሣለች። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትንሣኤዋም ቅርብ ነው። ማንም አያስቀረውምም። እኔ ዘመዴ የሥላሴ ባርያ፣ የድንግል አሽከር እኮ በተጋጣሚዎቼ ሜዳና በደጋፊዎቻቸው ፊት ብቻዬን ነው ያለ በረኛ፣ ያለ ተከላካይ፣ ያለ አማካይ፣ ያለ ክንፍ ተጫወዋቾች፣ ያለበጀት 12 ቱንም ባላንጣዎቼን እየገጠምኩ ወጥ በወጥ እያደረግኩ ያለሁት። አሁን እኔ ብጎርር ጉረኛ እባላለሁ? በፍጹም እንዲህ እያልኩ ልበጥረቅባቸው እንጂ። ከምር እኔ ዘመዴ ምርጥ የተዋሕዶ ልጅ ነኝ። በሰውነት ደቃቃ ነኝ ነገር ግን ግዙፎቹን አስፈራቸዋለሁ። አስደነግጣቸዋለሁም። በእውቀት እልም ያልኩ መደዴ መሃይም ደንቆሮ ነኝ ነገር ግን ባለ ወረቀቶቹን ሁሉ አንቀጠቅጣቸዋለሁ፣ እኔ ያለኝ ሃብት ብዕርና ምላስ ብቻ ነው። ባለ ጦሮቹን ሁሉ ድንብርብራቸውን ሳወጣ እያያችሁ ነው አይደል። እነሱ ከሚሳኤልና ከአቶሚክ ቦንብ የበለጠ ብዕሬንና ምላሴን ይፈሩታል። ይሄን በዩኒቨርሲቲ የማይገኝ ሞገስ የሰጠኝ ግን እግዚአብሔር ብቻ ነው። ድንግል ሆይ አየሽልኝ አይደል እናት አለሜ! ዓለሙን ሁሉ በያለበት እየዠለጥኩ ሳስነጥሰው። እ…ን…ጥ…ሾ።
•••
እርግጠኛ መሆን ባይቻልም ፈረንጆቹ ብቻ እኔን እየተከታተሉ ይሁነኝ ብለው ይሄን ግፍ አይፈጽሙብኝም። ፈረንጆቹ ኧረ በጌታ፣ ኧረ በኢየሱስ ይሄንን ሰው አስቁሙልን የሚሉ የእኛ ሰዎች ካልወተወቷቸው በቀር ይሄን ግፍ አይፈጽሙብኝም። ይሄን የሚያደርጉትና ሊያስደርጉብኝ የሚችሉት የእኛው ጉዶች ናቸው። እንዴት ሰው ግሩፕ አቋቁሞ እንዲህ ዓይነት ወራዳ ተግባር ይፈጽማል? ዛሬ የምሥራች ነው የለጠፍኩት። ቅዱስ ፓትርያሪኬን ነው የለጠፍኩት። ዕንቁዋን አትሌት ደራርቱ ቱሉን፣ ባለማዕተቧን አርቲስት መሰረት መብራቴን ነው የለጠፍኩት። የቅዱስ ሲኖዶሱንና እና የመንግሥትን ፈቃድ ነው የለጠፍኩት። ይሄንን ጦማር የኮሚዩኒቲ ስታንዳርድ አያሟላም ብሎ እንዳይታይ ማድረግን ምን ይሉታል? እነሱ የፈለጉት ዛሬ ኦቦ ዳውድ ኢብሳ ታሰረ። ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ተፈታ። የሚል አጀንዳ ሰጥተውን ከዳር ቆመው ለመዝናናት ነበር። እኔ እቴ ነቄ እኮ ነኝ በቀደዱልኝ ቦይ የማልፈስ፣ የራሴን አጀንዳ ቀርጬ በራሴ አጀንዳ የምወጠር፣ እሱ ነው ያናደዳቸው። ፌስቡክ የተዋሕዶ ልጆች እልልታ ሲበዛባቸው ደንግጠው ቆለፉብኝ።
•••
በሌላም በኩል የማዕዶት መመስረት ነስር በነስር ያደረጋቸው ማኅበራት እንዳሉም እረዳለሁ። መጣልን ሳይሆን መጣብን የሚሉ። ስግብግቦች፣ ከቤተ ክርስቲያን ይልቅ በራስ ግንባታ የተወጠሩ። በየቦታው የተንኮል የክፋት ባለሙያዎች ያሏቸው። ምቀኞች። የቤት ውስጥ ቀጋ የውጭ አልጋዎች፣ የጭቃ ውስጥ እሾሆች፣ ራስ ወዳድ ዘረኞች፣ ጎጠኞች፣ መንደሬዎች። ካለ እነሱ ሌሎች በመድረኩ ላይ እንዳይታይ የሚፈልጉ ከንቱዎች እነሱም ትንፋሽ አጥሯቸዋል። ዩቲዩቤን ላዘጋብኝ ለእነ ዮሐንስ ሞላ ለመከራከር ያላፈሩ፣ ጋለሞታ ነጠላ ለበባሽ አሰልፈው እኔን የሚያሰድቡ ክፉዎች። ሰው መሳይ በሸንጎዎች። እነሱም ይሄንን ያደርጋሉ። ከቤተ መንግሥት እስከ አማሪካ፣ ከሱሉልታ እስከ ሚኒሶታ በመንገዳችን ላይ የተገጠገጡ እንቅፋቶችም ሞልተዋል። እኔ፣ እኛ ብቻ ባዮች። አሳፋሪዎች። ለራበው ድንጋይ እየሰጡ መካሪዎች ግን ትገለበጣላችሁ። እመኑኝ ማኔ ቴቄል ፋሬስ።
•••
በሰለጠነ ዓለም ተቀምጦ የመናገር፣ የመጻፍ መብትን ማገድ ይሄ ነውር ነው። ሕገወጥም ነው። በተቃዋሚዎቼ የሚቀና ነገር አላቸው ከተባለ ለክፋት የሚያደርጉት ኅብረታቸው ብቻ ነው። ክፉዎች በጣም ይተባበራሉ። የእኔንና የሌሎችን ኦርቶዶክሳውያን የተዋሕዶ ልጆችን ፔጆች ለማዘጋት ከቤተ መንግሥት በጀት ተመድቦላቸው አማሪካ ዋሽንግተን ቤዙን ያደረገ ቡድን እንዳቋቋሙ ነው የሚነገረው። እነ ዮሐንስ ሞላ ያቋቋሙት ኔትወርክ አጌነስት ሄት እስፒች በኢዜማና በማኅበረ ቅዱሳን ልጆች የተሞላ ስብስብ ነው። ለዚህ ነው የአደባባይ ሚዲያዎች ለእኔ ሳይሆን ለዮሐንስ ሞላ ጥብቅና ለመቆም ቅሽሽ ያላላቸው። ለዚህ ነው እነ ቀሲስ ኤፍሬም እሸቴ ሁለት ጋለሞቶችን በስልክ ጥሪ በሚል ሰበብ አዘጋጅተው ሲያሰድቡኝ የነበረው። ምድረ ምቀኛ ሁላ። ትግሉ ግን ይቀጥላል። ወደ ጎንም ወደ ላይም ትግሉ ይቀጥላል።
•••
ደስታችንን ማጣጣማችንንም እንቀጥላለን። እንኳን ደስ ያለን። እንኳን ደስ ያላችሁ። ነገር ግን በውጭ ሃገራት የምትገኙ፣ በተለይ በሃገረ አሜሪካ የምትገኙ፣ እንዴት ፌስቡክንና ዩቲዩብን የሚያነጋግር አንድ ኢትዮጵያዊ ይጠፋል? ይሄን የግለሰቦች ተንኮል ገልጾ ለነጮቹ አሳስቦ መፍትሄ ማምጣት ያቅተዋል? በእንግሊዝና በአየርላንድ የምትገኙ ኢትዮጵያውያን እንዴት እዚያው ፌስቡክ ቢሮ ሄዳችሁ ማውራት ያቅታችኋል? እነሱ ለጥፋት የገንዘብ በጀት በጅተው እንዲህ እንቅልፍ ሲያጡ እንዴት ሌሎቻችሁ ከዳር ቆማችሁ ከንፈር ትመጣላችሁ። ለእኔ ስልክ እየደወላችሁ አጽናኑኝ ያልኳችሁ ይመስል “ አይዞኝ ዘመዴ” እያላችሁ ልቤን ውልቅ ከምታደርጉኝ እንደ እነሱ ተሰባስባችሁ አንድ ነገር አታደርጉም። የዩቲዩብ የፌስቡክ የሥራ ኃላፊዎችን ስልክና ኢሜይል ፈልጋችሁ ካምፔን አትፈጥሩም? ምንድነው ከዳር ቆሞ መብሰክሰክ። እንዴት አንድ ቆራጥ ይጠፋል? እኔ በዚህ አፍራለሁ። ለነገሩ ለጣና ሐይቅ አንቦጭ ማጥፊያ አንዲት የምርምር ውጤት ጠብ ያላደረገ ባለ ወረቀት ለእኔ ለደካማው ባለ ብርቱ ፌሮው ዘመዴ ጥብቅና ይቆምልኛል ብዬም አላስብም። ግን ሰው ቢኖረኝ እኔ አሸንፍ ነበር። የእኔ ሰዎች በዚህ በኩል ፈሪዎች ናቸው። ቦቅቧቃ፣ ከንፈር መምጠት፣ መወራጨት፣ እልህ፣ በጓዳ መብከንከን ብቻ። እስቲ ወጣ በሉ። ብዙ ሴናተሮችን ታውቃላችሁ። ዩቲዩብም፣ የፌስቡክ ካምፓኒ ሰዎችንም የምታውቁ አላችሁ። የሕግ ባለሙያ የምታውቁም አላችሁ። እንዴት ሰብሰብ ብላችሁ ስለ እኔ ማናገር ያቅታችኋል? በዚህ አፍራለሁ። በእነሱ የጥፋት ኅበረት ደግሞ ባያስቀናም እቀናለሁ።
•••
እንግዲህ የዛሬውን የምሥራች ፖስቴን የኮሚኒቲ እስታንዳርድን ጥሰሃል ብሎኝ ነው ያጠፋብኝ። ለእኔ ጦማሬ ይታየኛል። የጠሉት የላይኩንና የሼሩን፣ የገጼን ተመልካቾች ብዛት ነው። እንጂ ምንም የኮሚኒቲ እስታንዳርድ ጥሰት አልፈጸምኩም። በጭራሽ። ሴቶቹ የለበሱት ነጭ የሃገር ልብስ ነው። ራቁቱን የቆመም የለም። ሄት ስፒች የሚያሰኝም ነገር የለም። ምንአልባት በፌስ ቡክ የቀጥታ ስርጭት (Live) እመጣለሁ ማለቴ ይመስለኛል ያስደነገጣቸው። የሆነው ሆኖ እኔ አሸናፊ ነኝ። ለአንዳንዶች የእኔ ጦማር እንዳይታያቸው ነው ያደረገው ፌስቡክ። ማፈሪያ ነው። እደግመዋለሁ እኔ ግን አሸናፊ ነኝ።
•••
በጀመርነው መንገድ እንቀጥላለን። የቴሌግራም ቻናሌን አጥብቃችሁ ያዙ። ቴሌግራም የራሺያዋ ኦርቶዶክስ ስለሆነ እስከአሁን ችግር አልገጠመኝም። ሰብስክራይብ አድርጉት፣ አስደርጉትም። 1 ሚልየን ፎሎወር እስኪሞላ በዚያው እንቀጥላለን። በሳታላይት የመምጣቱን ጉዳይም 99% ከመቶ ተሳክቷል። ዝርዝሩን ለብቻው እመለስበታለሁ።
•••
ይሄ በእኔ በዘመዴ ላይ ብቻ የተቃጣ ጥቃት መስሎህ ከሆነ ተሳስተሃል። ይሄ በኢትዮጵያዊነትና በኦርቶዶክሳዊነት ላይ የተቃጣ ዓለም አቀፋዊ ጥቃት ነው። የተዋሕዶ ክብሯ በየትም፣ በማንም እንዳይገለጥ አውሬው፣ ዘንዶው ተቆጥቶ መነሣቱን የሚያመላክት ነው። እናም ጥቃቱ የእኔ ብቻ ከመሰለህ ተሳስተሃል። ብንተባበር ግን እናሸንፈዋለን።
•••
“እኔ ግን እላለሁ! እምዬ ኦርቶዶክስ አንቺ እናትዓለም፤ የእነ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ፣ የእነ ቅዱስ አትናቴዎስ እና ቅዱስ ቄርሎስ የእነ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ የእነ ቅድስት አርሴማ፣ የእነ አቡነ ተክለሃይማኖት፣ የእነ አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ፣ የአባ ሳሙኤል ዘዋልድባ፣ የቅድስት ክርስቶስ ሠምራና የአቡነ አረጋዊ ሃይማኖታቸው የሆንሽ ንጽህት፣ ቅድስት፣ ርትዕት ተዋሕዶ ሃይማኖቴ ሆይ! ብረሳሽና ብከዳሽ ቀኜ ትርሳኝ። ትክዳኝም። ባላስብሽና ባልሟገትልሽ ባልሞትልሽም ምላሴ ከጉሮሮዬ ይጣበቅ። ሳለጎበድድና ሳለከዳሽ እንድኖርም አምላክሽ ይርዳኝ። ይህን ባላደርግና ሳልጮህልሽ ዝም ብዬ ብሞት ስሜ ከህይወት መጽሐፍ ይደምሰስ።
“ጌታ ሆይ! ከዚህ በፊት በሆነው፤ አሁንም እየሆነ ባለው እና ወደፊትም በሚሆነው ነገር ፤ ክብሩን ሁሉ አንተ ውሰድ።” አሜን።
“ድንግል ሆይ እናቴ ! አዛኝቱ ዛሬም እንደትናንቱ ቅደሚ ከፊት ከኋላዬ”
¶ ድልና ትንሣኤ ለኢትዮጵያ ሀገሬና ለተዋሕዶ ሃይማኖታችን ! ውድቀትና ጥፋት፤ ለሁለቱም ጠላቶች። አራት ነጥብ።
• ይህንንም ራሴው በእጄ ጻፍኩት። +49 1521 5070996 ደግሞ የቴሌግራም፣ የቫይበር፣ የኢሞና የኋትስአፕ መልእክቶችን የምቀበልበት የእጅ ስልኬ ነው።
•••
ሻሎም ! ሰላም !
ዘመድኩን በቀለ ነኝ።
ጥቅምት 5/2012 ዓም
ከራየን ወንዝ ማዶ።