>
5:18 pm - Monday June 15, 7903

የቢሾፍቱ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ በአስቸኳይ አቶ ልደቱን እንዲፈታ ወሰነ...!!! (ይታገሱ አምባዬ)

የቢሾፍቱ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ በአስቸኳይ አቶ ልደቱን እንዲፈታ ወሰነ…!!!

ይታገሱ አምባዬ

* “ትእዛዙ ካልተከበረ  ችሎቱ እርምጃ እንደሚወስድ  የምሥራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አዘዘ”
ጠበቃ መሐመድ ጅማ ገለጹ
*   “እኛ ያላከበርነው እና ያልታዘዝነው ፍርድ ቤት ነጻና ገለልተኛ ሆነ ማለት ከንቱ ነው” 
ጠቅላዩ ለፓርላማ
እንደ አቶ መሐመድ ገለጻ ከሆነ፤ ትናንት ጥቅምት 9 ቀን 2013 ዓ. ም የምሥራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወንጀል ችሎት በመቅረብ ምላሽ የሰጡት የቢሾፍቱ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ፤ ለቦታው አዲስ መሆናቸውን ያስረዱ ሲሆን፤ የአቶ ልደቱ ክስም ሕገ ወጥ መሣሪያ በመያዝ እንደሆነ እንደማያውቁ አስረድተዋል።
ኃላፊው አክለውም፤ ከኦሮሚያ ፖሊስ ጋር ስለዚህ ጉዳይ ተነጋግሬ እንድመጣ ሌላ ቀጠሮ ይሰጠኝ በሚል ችሎቱን ጠይቀዋል።
አቶ ልደቱ የዋስትና መብታቸው ተጠብቆ የማይለቀቁ ከሆነ፤ ፍርድ ቤቱ እርምጃ እንደሚወስድ ማስጠንቀቁንም ጠበቃ መሐመድ  ተናግረዋል።
ለወራት በእስር ላይ የሚገኙት አቶ ልደቱ፤ የምሥራቅ ሸዋ ዞን ፍርድ ቤት በ100 ሺህ ብር በዋስትና ወጥተው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ወስኖ ነበረ ቢሆንም የቢሾፍቱ መምሪያ ፖሊስ ግን ሳይለቃቸው ቆይቷል።
በወቅቱም የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አቶ ልደቱን በሚመለከት ባወጣው መግለጫ፤ አላስፈላጊ እስር ማስቀረትና የዋስትና መብት ማክብር ያስፈልጋል ሲል ጠይቋል።
አቶ ልደቱ በአንድ መቶ ሺህ ብር ዋስ ከእስር እንዲወጡ መስከረም 12/2013 ዓ. ም ትዕዛዝ ቢሰጥም እስካሁን አልተፈቱም።
አቶ ልደቱ ዛሬ ፍርድ ቤት በቀጠሮ የቀረቡት በሦስት ጉዳዮች እንደነበር ጠበቃው አስረድተዋል።
ከዚህ ቀደም ፍቃድ የሌለው መሣሪያ በመያዝ በሚለው ክስ ላይ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች ተሰምተው የነበረ መሆኑን አስታውሰው፤ ዛሬ መዝገቡን መርምሮ ለብይን ቀጠሮ ይዞ እንደነበረ ተናግረዋል።
ዛሬ በነበረው ችሎት ላይ የችሎቱ ፀሐፊ በድምጽ መቅጃ ያለውን ተይቦ አለመጨረሱን ማስረዳቱን ይናገራሉ።
ሁለተኛው ጉዳይ፤ አቶ ልደቱ የዋስትና መብታቸው ተጠብቆ ይፈቱ ቢባልም የቢሾፍቱ ከተማ ፖሊስ ትዕዛዙን ባለመፈፀሙ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሸን የቢሾፍቱ ፖሊስ መምሪያን አስገድዶ አቶ ልደቱን እንዲለቅቃቸው ታዝዞ ስለነበር የኦሮሚያ ፖሊስ ትዕዛዙን መፈፀም አለመጸፀሙን ለማረጋገጥ ነበር።
አቶ መሐመድ፤ በዛሬ የፍርድ ቤት ቀጠሮ የኦሮሚያ ፖሊስ ፍርድ ቤት አለመገኘቱን፣ ትዕዛዙ መፈፀም አለመፈፀሙን ችሎት ላይ ቀርቦ አለማረጋገጡን ተናግረዋል።
ሦስተኛው ጉዳይ የቢሾፍቱ ከተማ ፖሊስ የፍርድ ቤትን ትዕዛዝ አክብሮ ለምን አቶ ልደቱን እንዳልለቀቃቸው ለማጣራት ቀጠሮ ተሰጥቶ እንደነበር አቶ መሐመድ ያስታውሳሉ።
የቢሾፍቱ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ችሎት የቀረቡ ሲሆን፤ ከመስከረም 13 በኋላ ተቀይረው ወደ ቢሾፍቱ ከተማ መምጣታቸውን አስረድተዋል።
ተቀይረው ከመጡ በኋላም ሥራ ይበዛባቸው እንደነበር በማስረዳት፤ የአቶ ልደቱ ክስ የሕገ ወጥ መሣሪያ መያዝ መሆኑን እንደማያውቁ እና ሐገ መንግሥቱን በኃይል ለመናድ በመሞከር በሚል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ክስ ስላላቸው አለመለቀቃቸው መረጃ እንዳላቸው ለችሎቱ አስረድተዋል።
ትዕዛዙም ቢሆን ሁለቴ እንዳልደረሳቸው ገልጸው፤ ባለማወቃቸው ብቻ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ መፈፀም አለመቻላቸውን አስረድተዋል።
አቶ ልደቱ በቢሾፍቱ ፖሊስ መምሪያ ስር ቢሆኑም የተያዙት ግን በኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በመሆኑ ከኮሚሹኑ ጋር ተመካክረው ውሳኔ እስከሚሰጡ ድረስ ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጣቸው አቤቱታ አቅርበዋል።
ፍርድ ቤቱ ይህንን ከሰማ በኋላ ለችሎቱ ያቀረቡት መልስ አጥጋቢ እንዳልሆነ ገልጾ፤ አቶ ልደቱ በአስቸኳይ እንዲለቅቁ ካልሆነ ግን እርምጃ እንደሚወስድ ትዕዛዝ አስተላልፏል።
የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽንም የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ለምን አክብሮ እንዳልቀቀቃቸው ወይንም ለምን እንደማይለቃቸው ቀርቦ ስላላስረዳ በቀጣይ ቀጠሮ ቀርቦ እንዲያስረዳ ትዕዛዝ ተሰጥቷል።
የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በሚቀጥለው ቀጠሮ ትዕዛዙን ፈጽሞ ካልሆነም ያልፈፀመበትን ምክንያት ይዞ እንዲቀርብ አዝዟል።
የችሎት ፀሐፊውም በድምጽ መቅረጫ ላይ የሚገኘውን የምስክሮች ቃል ተይቦ እንዲጨርስና ከችሎቱ ቀጠሮ በፊት እንዲያቀርብ ታዝዟል።
አቶ ልደቱ አያሌው ጥቅምት 11 ቀን 2013 ዓ. ም ችሎት ፊት እንዲቀርቡ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ 5ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ ልዩ ስብሰባ ላይ፤ ፍርድ ቤቶች የሚሰጡትን ማንኛውም ውሳኔ አስፈጻሚው አካል ማክበር እንዳለበት መግለጻቸው ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም “እኛ ያላከበርነው እና ያልታዘዝነው ፍርድ ቤት ነጻና ገለልተኛ ሆነ ማለት ከንቱ ነው” ብለዋል፡፡
Filed in: Amharic