>
6:11 am - Friday March 31, 2023

ህያው ምስክርነት....!!! (ወርቅነህ አሰፋ)

ህያው ምስክርነት….!!!

ወርቅነህ አሰፋ

በምድር ስትኖር መልካም እያደረግኽ በተራመድክ ቁጥር ዉበቱን ያፈስስብሀል።   እስኪ ዛሬ በሙያዉ የህዝብ፣ በግል ህይወቱ የብዙሀን አሌኝታ ስለሆነ ምርጥ ከያኒ ላጫዉታችሁ። አያሌዉ መስፍን። አርሱን በደንብ ከሚያዉቁት ቅርብ ሰዎች አንዱ ስለሆንኩ ሳልመሰክርለት ባልፍ ቁጭት እንዳይጎዳኝ  ለራሴ ስል ይሄዉ።
   ብዙዎች ጋሽ አያሌዉ ይሉታል። እኛ የቅርቦቹ አዩዬ እንለዋለን። ገና ጎረምሳ እያለሁ ጎበዝ በነበርኩባቸዉ የሙዚቃ ጉዞዎቼ ጊዜዎች ነበር ያገኘሁት። አዱ ገነት ፒያሳ እምብርቷ ላይ እዉቁ እና የብዙ ጓደኛሞች፣ ፍቅረኞች፣ ነጋዴዎች፣ ደላሎች፣ ገበያተኞች ወዘተ መቀጣጠሪያ አያሌዉ ሙዚቃ ቤት።
    ገና በጠዋቱ ነበር የገባሁት። ከካሸሩ ወስጥ ከተቀመጠበት ብድግ ብሎ ትልቅ ሰዉ የገባ ያህል ጎንበስ ብሎ ጤና ይስጥልኝ እንደምን አደርክ ሲለኝ የምናገረዉ ጠፋኝ። እኔ የማዉቀዉ ብዙ ትላልቅ የምንላቸዉ ሰዎች, ጎረምሳዉ እዴነሽ ሲሉኝ ነዉ። ትንሽ ትልቁን በእኩል የማክበር ስብዕናን ያየሁትም የተማርኩትም ከአያሌዉ መስፍን ነዉ።           ተዲያ ከዚያች እለት ጀምሮ የሙያ ቅብብሎሽ ሁለት ዜማና ግጥሞቼን የወሎ ልጅ እና ሞንዳላዬን ፣ የራሱን ስምንት ዜማና ግጥሞች ጨምሮ በካሴት አሳትሞ ካቀነቀነልኝ በኋላ መለያየት የማንችል ስጋዎች ሀነን ቀረን።
      አሁን የእኔና የሱን ጉዳይ እዚህ ላይ ልግታና
ዉስጤን ሲሞግተኝ ስለኖረዉ ምስክርነት ልቀጥል።
    አዩዬ በተለይ ፒያሳ ጀምበር ብቅ ስትል ሱቁን ይከፍት እና እዚያዉ ፈትለፊት ጫማ በመጥረግ የሚተዳደሩ ልጆች ጠርቶ በሉ እስኪ ይቺን እዚያ ጋር፣ ያቺን ወደ እዚህ እያለ የሆነ ያልሆነ እቃዎች እንዲያጸዱ ወይም እዲደረድሩ ያደርግ እና በሉ አሁን ቁርስ አስመጡ ይልእና ከጎኑ ያሉት ምግብ ቤቶች አንዱ ጋር ይልካቸዋል። ያዘዛቸዉ ስራዎች በቀላሉ በአንድ ሰዉ የሚከወኑ እና ቀላል ሆነዉ ሳለ የእርሱ እሳቤ ግን ሰርቶ መብላት ምንያህል ጣፋጭ እንደሆነ ማስተማር ነዉ።
    ምግቦች ይመጣሉ፣ ይደረደራሉ። በሉ እጃችሁን ታጠቡ እና ቅረቡ ይልና እየተጎራረሰ ከማንም እንደማያንሱ አሳይቷቸዉ፣ ሞራላቸዉን ገምብቶ ይሸኛቸዋል። በየሳምንቱ የእርሱን ጨምሮ የቤተሰቡ ጫማዎች ተሰብስበዉ ወደሱቁ ይመጣሉ፣ ሊስትሮዎቹ ይወለዉሏቸዉ እና በየወሩ ጠርቀም ያለ ገንዘብ እየከፈለ ለቤተሰቦቻቸዉ እንዲሰጡም ያደርጋል።
    እርሱ የሚደጉማቸዉ በእርጅና ወይም በተለያዩ ምክንያት ስራ ያጡ ከያኒያን ቤታቸዉ ይቁጠራቸዉ። ስማቸዉን መጥቀስ ጨዋነት ስላልሆነ ትቼዋለሁ። አንዳንዶቹ የቤት ክራያቸዉን ሳይቀር እንደሚከፍል አስታዉሳለሁ። ያለፉት እንዳለፉ ሆኖ በህይወት ያሉት አንድቀን ይመሰክራሉ ብዬ እጠብቃለሁ።
   አንድ እርሱ ባቋቋመዉ ጥቁር አንበሳ ባንድ ዉስጥ ይጫወት የነበረ ኪቦርድ ተጫዋች ሙዚቀኛ የአዕምሮ መታወክ ይደርስበትና ከቁጥጥር ዉጭ ይሆናል። ጎዳና ወጣ፣ በጣም ቆሸሸ፣ አልፎ አልፎ በአስጸያፊ ሁኔታ እየቆሸሸ ሰዎች መቅረብ እስከሚቸገሩ ድረስ ይሆን ነበር። ታዲያ የመስፍን ጩፋ ልጅ ደጉ አያሌዉ መስፍን ብቻ ነበር የማይጠየፈዉ። ቱታዉን ይለብስና፣ ወደሱቁ ያስገባና ከስቱዲዮዉ በስተጀርባ ከሚገኘዉ ሻወር ቤት ዉስጥ ሙልጭ አድርጎ ጸጉሩን ላጭቶ ገላዉን አጥቦ የራሱን ልብስ ሰጥቶ፣ ምግቡን አብልቶ ይሸኘዋል። ይህን የሚያደርገዉ ሰዉየዉ በህይወት አስካለፈ ጊዜ ሁሉ ነበር።
    ታዲያ ምን ያደርጋል እሱ ግን ተመልሶ እዚያዉ አሮንቃ ዉስጥ ይገኝ ነበር። አዩዬ ግን አንድም ቀን ሰልችቶት አያዉቅም ነበር።
    በሌላ ጊዜ አንድ በድለላ ስራ የሚተዳደር አልፎ አልፎ እንዲሁ እርሱ የሚረዳዉ ወጣት ይሰርቀዉና ለሦስት ወራት ያህል ጠፍቶ አመድ መስሎ ብቅ አለ። ያኔ እኔ እና አዩዬ ሱቅ ከፍተን ቁርስ ይዘናል። አጅሬዉ ጸጉሮቹን እያከከ አዩዬ ደህና ነህ? ይላል። አዩ ቀበል አርጎ እኔ ምን እሆናለሁ ጨዉ መስለህ የመጣኸዉ አንተ ይልቅ የራበህ ትመስላለህ እጅህን ታጠብ እና የደረስክበት ላይ ቅረብ ብሎት እጁን ሊታጠብ ሲገባ እኔ ከንክኖኝ አዩዬ ዝም አልከዉ? ማለት! አይ ወንድም አለም ሞቶ መጣ እኮ ምኑን ልቆጣዉ አልቋል እኮ እያለ ጭራሽ ያዝንለት ጀመር። አሱም ረሀቡን ጋብ አድርጎ ወጣ።
      የአያሌዉ መስፍን ስብዕና ጥግ ስለሌለዉ በብዙ ሰዎች ተክዷል፣ ተጭበርብሯል፣ እያወቀ እንዳላወቀ ሲያልፋቸዉ ብዙዎች ብልጠት እየመሰላቸዉ ደጋግመዉ ጎድተዉታል። እርሱ ግን ለቂምም፣ ለበቀልም ቦታ የለዉም። ጭራሽ ያዝንላቸዋል። ሌላዉ የሚገርመኝ የጸሎቱ ማሳረጊያ ኢትዮጵያን አደራ ነዉ። ነገርግን ከማሳረጊያዉ በፊት የወዳጆቹን ሁሉ ስም እየጠራ እግዚዓብሄር እንዲጠብቀን ይማጸናል።
    ታዲያ ከላይ እንደጠቀስኩት መልካም ስብዕና ያለዉ ሰዉ እድሜዉ በጨመረ ቁጥር የበለጠ እያማረበት፣ ሞገሱ እየጎላ ክብሩ እንደሚበዛ ፎቶዉን አይታችሁ ፍረዱ።
    ይልቅ ብዙዎች የማያዉቁትን ሌላ ሙያዉን ላሳብቅ። ጥሩ ኮፒ አድራጊ የእጅ ባለሙያ ነዉ።
 ምናልባት ልብ ካላችሁ አያሌዉ ሙዚቃ ቤት ስትገቡ በቀኝ በኩል ካለዉ የሙዚቃ መሳሪያዎች መሰተሪያ መድረክ ላይ ቆሞ የነበረዉ ዘመናዊ ድራም የአያሌዉ መስፍን የእጅ ስራ ዉጤት ነዉ ብላችሁ ስንቶቻችሁ ታምኑ ይሆን? ይሄ ድራም ሲሰራ እንጨቶቹ ሲዘጋጁ ያዝ! ወጥር ስባል ላቤ ጠፍ ብሏልና እመኑኝ።
   የእኔ የግሌ የሆነዉን የመጀመሪያ ቤዝ ክራር በእጁ ሰርቶ ሰጥቶኝ ብዙ አመታት ተጠቅሜበታለሁ። አዩ የሚጠላዉ ስራ መፍታት ብቻ ነዉ።
  ብዙ ልል እችላለሁ ግን የአያሌዉ መስፍንን ታሪክ በቀላሉ ስለማልጨርሰዉ ስጓጓለት በኖርኩት እሱን ማመስገን ልቋጨዉ።
    አዩዬ ዉለታህን ልክፈል ብል ሚዛኑ ከባድ ነዉ። የማያልቅበት አምላክ እግዚዓብሄር በጤና እና በእድሜ ይክፈልልኝ። የማያልቅ ፍቅራቸዉን ለቸሩኝ ቤተሰቦቼ ዉዷ ባለቤትህ ሄለን አስፋዉ፣ ልጆችህ ህይወት አያሌዉ፣ በአካል ብናጣዉም በተለይ አያሌዉ፣ ዳግማዊ አያሌዉ እና ነብዩ አያሌዉ ፣ ዶሚኒክ /ማሙሽ/ ለእናንተ ያለኝ ፍቅር ገደብ የለዉም።
Filed in: Amharic