ዶክተር አንማው አንተነህ
እዮብ ሰለሞን
* “በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ፖለቲከኛ አለመሆን የሚቻል አይደለም፡፡ አሁን አያገባኝም የምንልበት ወቅት አይደለም፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ህልውና የሚያሳስበን ዜጎች ሀገር አፍራሾች እንዳሻቸው ሲያደርጉ ቁጭ ብለን ማየት የለብንም”
የ1997 ምርጫ ከመካሄዱ አንድ አመት ቀደም ብሎ አቶ መለስ ዜናዊ ከዩንቨርሲቲ መምህራን ጋር ለመወያየት በተሰየሙበት መድረክ ላይ አንድ መምህር ትንቢታዊ የሚመስል አስተያየት ሰንዝሮ ነበር፡፡
ይህ ሰው ዶክተር አንማው አንተነህ ነው፡፡ በዚያ ውይይት ላይ የዘር ፖለቲካ መዘዝ ሀገር እንደሚያፈርስ እና ህዝብ እንደሚያጫርስ የተናገረው ዶክተር አንማው አንተነህ፤ አቶ መለስ ዜናዊን “እርሶ በህይወት እያሉ በኢትዮጵያ ምድር ዴሞክራሲ አይመጣም፡፡ ይህ እንዳይሆን ያደረጉት ደግሞ ሆነ ብለው ነው፡” በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
ዶክተር አንማው አንተነህ ይህን ንግግር ካደረገ ከረዥም አመታት በኋላ ትናንት ጥቅምት 8 ቀን 2013 ዓ.ም በኢዜማ ምርጫ ወረዳ 20 ፅህፈት ቤት ለፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም መታሰቢያ በተዘጋጀ የጧፍ ማብራት ስነ-ስርዓት ላይ ተገኝቶ የሚከተለውን ንግግር አድርጓል፡፡
“በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ፖለቲከኛ አለመሆን የሚቻል አይደለም፡፡ አሁን አያገባኝም የምንልበት ወቅት አይደለም፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ህልውና የሚያሳስበን ዜጎች ሀገር አፍራሾች እንዳሻቸው ሲያደርጉ ቁጭ ብለን ማየት የለብንም፡፡
አሁን አሰላለፋችንን ማስተካከል አለብን፡፡ በኢትዮጵያ በአሁኑ ሰአት ሁለት አሰላለፍ ነው ያለው፡፡ ኢትዮጵያን የማፍረስ የዘረኝነት አካሄድ እና ኢትዮጵያን የማቆየት የኢትዮጵያዊነት አሰላለፍ ነው ያለው፡፡ ሁለቱም አሰላለፍ ላይ አልገባም፤ አያገባኝም ብሎ መቀመጥ ሀገር ሲፈርስ እንደመተባበር ነው፡፡
በዘረኝነት ቅዠት ውስጥ ያሉ ሰዎች ኢትዮጵያን ለማፍረስ እና ዘጠኝ ትንንሽ ሀገር ለመስራት በትጋት እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያ ህልውናዋ እንዲጠበቅ የምንፈልግ ሰዎችም አሰላለፋችንን ከኢትዮጵያዊነት ጎን በማድረግ የምንችለውን ሁሉ ማድረግ አለብን፡፡
ኢትዮጵያዊነትን ደግፎ መንቀሳቀስ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የሞት የሽረት ጉዳይ ነው፡፡ ጥያቄው ኢትዮጵያን ስትፈርስ ቆመን እናያለን ወይስ እንዳትፈር እንከላከላለን የሚለው ነው፡፡ ፖለቲካ አያገባኝም ብሎ ቁጭ ማለት ኢትዮጵያ ስትፈርስ እንደመተባበር ነው፡፡
እኔ በግሌ ፖለቲካን ሙያው ያላቸው ሠዎች ቢገቡበት እመርጣለሁ፡፡ እኔም ፖለቲከኛ ለመሆን ፍላጎቱም ሆነ ችሎታው እንደሌለኝ አምናለሁ፡፡ የኔ ሙያ እንግሊዝኛ ቋንቋ ማስተማር ነው፡፡ አሁን ግን የኢትዮጵያ ሁኔታ ሳልወድ በግድ ኢዜማን ተቀላቅዬ ለኢትዮጵያዊነት ዘብ እንድቆም አድርጎኛል፡፡ እኔ አሰላለፌን በኢትዮጵያዊነት ጎራ አድርጌያለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ጉዳይ የሚያሳስባችሁ ወገኖች ሁሉ አያገባኝም ብላችሁ ከመቀመጥ ከኢትዮጵያዊነት ጎን መሰለፍ አለባችሁ፡፡”