>

.....በቤንሻንጉል በግፍ የተገደሉ ዜጐች  አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ 

በሀገራችን ኢትዮጵያ በምዕራብ ወለጋ እና በጉራፈርዳ እንዲሁም በቤንሻንጉል በግፍ የተገደሉ ዜጐች  አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን  ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ 

 
 ስለ ዓለማት አፈጣጠር ስለሰው ዘር አመጣጥ ስለ ኃጢአትና የስቃይ ኑሮ አጀማመር እግዚአብሔር ከሰው ዘር ጋር ስለአለው ግንኙነት በሚናገረው በኦሪት ዘፍጥረት መጽሐፍ ምዕራፍ አንድ ቁጥር አንድ ላይ በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይና ምድርን ፈጠረ በዚያን ጊዜ ምድር ባዶ ነበረች ይላል፡፡
 ከዚህም ጋር ለሰው ልጆች በእጅጉ አስፈላጊ የሆነውን ብርሃን “ብርሃን ይሁን” በማለት ብርሃንን ከጨለማ ለየ፡፡ በዚህም መሠረት በብርሃን በሞላው አለም ይኖር ዘንድ እግዚአብሔር ሰውን በራሱ መልክና በራሱ አምሳያ ፈጠረው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ሰውን ከፈጠረው በኋላ ብዙ ተባዙ ዘራችሁ ምድርን ይሙላ ምድርም በቁጥጥራችሁ ሥር ትሁን በሚል የሰው ልጆች ምንም ዓይነት መልክ ይኑረን የትኛውንም ቋንቋ እንናገር እግዚአብሔር በፈጠረልን ምድር በየትኛውም አቅጣጫ ተከብረንና ተከባብረን እንድንኖር ምድርንም እንድናለማ እግዚአብሔር ፈጥሮናል፡፡
ማለትም የሰው ልጆች በዚህ ዓለም ላይ ስንኖር እንግዶች እንጂ ከመካከላችን አንድም ባለአገር እንደሌለ ሊኖርም እንደማይችል ከላይ የተገለፀው የእግዚአብሔር ቃል ይነግረናል፡፡
እውነታው ይህ ሁኖ ሳለ የሰው ልጅ በእጅጉ በተሳሳተ አመለካከት ውስጥ በመግባት ይሄ የኛ ያኛው የእናንተ አካባቢ እየተባባልን የመለያየት ሁሉ መሠረት የሆነውን የጠላትን መንፈስና አሠራር በመከተል እርስ በርሳችን በመጠላላት ወንድም ወንድሙን ሲያሳድድ እርስ በርሳችን እየተጠፋፋን እንገናለን፡፡
በቅርቡ ጥቅምት 22 ቀን 2013ዓ.ም. በኦሮምያ ክልል በምዕራብ ወለጋ እና ጉራፈርዳ እንዲሁም በቤንሻንጉል ምንም ዓይነት የፖለቲካ አመለካከት የሌላቸው ማልደው በመነሳት አምሽተው በመግባት ምድርን ቆፍረውና አርሰው፣ ዘርተውና አጭደው፣ በድካም ኑሮአቸውን የሚገፉ ንፁሐን ዜጐች ሽማግሌዎች፣ ሴቶችና ሕጻናት ጭምር ሳይቀሩ ጅምላ ጥፍጨፋ በማካሄድ ሕይወታቸው እንዲያልፍ መደረጉ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤው በዓመታዊ ስብሰባ ላይ እያለ የሰማው ሲሆን ቅዱስ ሲኖዶሱንና ቤተ ክርስቲያናችንን በእጅጉ ያሳዘነ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት በመሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ እንዲህ ዓይነቱን ድርጊት አውግዟል፡፡
መላው ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንና የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ከላይ በመግቢያው እንደገለጽነው እግዚአብሔር ሰማይና ምድርን ፈጠረ ሰውንም በራሱ መልክና አምሳያ ፈጠረው እንዳለው ሁሉ የሰው ልጆች በዚህ ዓለም ስንኖር ሁላችን የእግዚአብሔር ፍጥረት መሆናችንን ተገንዝበን ሐሳባችንም ሆነ ተግባራችን እንደ እግዚብሔር ሐሳብ ሆኖ ሁላችን የዚህ ዓለም እንግዶች መሆናችን ተገንዝበን በወንድማማችነትና በፍቅር በአንድነት በመተሳሰብ እግዚአብሔር ፈጥሮ በሰጠን ምድር ላይ በፍቅር ልንኖር ይገባል፡፡
በርግጥ እንደ ሥጋ ለባሽነታችን በተለያየ አካባቢ ተወልደን እንደማደጋችን የተለያየ መልክ ሊኖረን የተለያየ ቋንቋ ልንናገር የተለያየ ባሕልና ሥርዓት ሊኖረን የእኔ የምንለው የራስ አመለካከትም ሊኖረን ይችላል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ሌላው ከእግዚአብሔር የተሰጠን የፀጋ ስጦታ እንጂ ለመለያየት ምክንያት ሊሆነን አይገባም፡፡
ስለዚህ አላስፈላጊ በሆነ ምክንያት በግፍ ለተገደሉትና ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን በቤተ ክርስቲያናችን ስም ልባዊ ሐዘናችንን እየገለጽን ዳግሞ እንዲህ ዓይነት ኢ-ሰብአዊ ድርጊት እንዳይፈጸም መንግሥት ለዜጐች አስፈላጊውን ጥበቃ እንዲያደርግ ወንጀለኞችንም ለፍርድ እንዲያቀርብ እያሳሰብን መላው ኢትዮጵያውያን ልጆቻችንም በቀጣይ ለጋራ ሰላምና አንድነት እንድትቆሙ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡ የሞቱ ወገኖቻችንን ነብስ ይማርልን፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ፤ ይቀድስ፤
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
አሜን!!
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም
ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም.
አዲስ አበባ
(ፎቶ- በዲ/ን ሙሉዓለም ዐሥራት)
Filed in: Amharic