>
5:13 pm - Thursday April 20, 1065

"የመግለጫ ጋጋታ ህዝብን ከሞት አያድንም...!!!" የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አባላት

“የመግለጫ ጋጋታ ህዝብን ከሞት አያድንም…!!!”
የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አባላት
ዘጋቢ፡- ጽዮን አበበ- ከአዲስ አበባ

 በአማራ ህዝብ ላይ እየተደረገ ያለዉን ጭፍጨፋ መንግስት ማብራሪያ ይስጥበት…!!”
ሕዋሃት እና ኦነግ ሸኔ በምክር ቤቱ በሽብርተኝነት እንዲፈረጁ የጠየቁ የምክር ቤት አባላት ጠይቀዋል
የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ለዛሬ የያዛቸውን አጀንዳዎች እንዲወያይባቸው በአፈ ጉባኤው በኩል የቀርበለትን ዜጎች ማንነታቸውን መሰረት ባደረገ ጥቃት እየተጨፈጨፉ ሌላ አጀንዳ ላይ አንወያይም ብለዋል፡፡
በእምቢተኝነታቸው በፅናትም ለዕለቱ የተያዘላቸውን አጀንዳ ውይይት ከመጀመራቸው በፊት ከ2 ሰዓት በላይ ስለዚሁ ጉዳይ በእንባ እየተናነቃቸው ጭምር ሀሳባቸውን በስሜት ገልፀዋል፡፡
በመግለጫ መፍትሄ አይመጣም፣ድርጊትና እርምጃ ያስፈልጋል፣ዛሬ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች እየተጨፈጨፉ ዝም ካልን ነገ በሺዎች የሚቆጠሩ እንዲጨፈጨፉ መፍቀድ ነው፣ ሲሉም ሞግተዋል፡፡
ምክር ቤቱ ዛሬ ስብሰባውን በተለየ መንገድ ነው ነበር የጀመረው፡፡ አፈ ጉባኤው፣የዕለቱን አጀንዳዎች በዝርዝር ከማቅረባቸው በፊት በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ከትናንት በስቲያ በዜጎች ላይ የደረሰውን ጭፍጨፋ በተመለከተ መንግስት አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ የሚያሳስብ መግለጫ በማንበብ ጀምረዋል።
የ1 ደቂቃ የህሊና ፀሎት ከተደረገ በኋላ ወደ ዕለቱ አጀንዳዎች ለመገንባት ማስተዋወቅ ሲጀምሩ፣የተለያዩ የምክር ቤቱ አባላት እዚህም እዛም እጅ እያወጡ ተራ ሳይጠብቁ መናገር ጀመሩ፡፡
 * በዜጎች ላይ የብሔር ማንነትንና ሃይማኖትን መሰረት ባደረገ ጥቃት በየጊዜው እየተጨፈጨፉ በምን ሞራል ነው ሌላ አጀንዳ ላይ የምንነጋገረው? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
* የመግለጫ ጋጋታ ህዝብን ከሞት አያድንምና መንግስት በአማራ ህዝብ ላይ እየተደረገ ያለዉን ጭፍጨፋ ማብራሪያ እንዲሰጥበት የህዝብ ተወካዮቹ ጠይቀዋል
* በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ጥቃት አድርሰዋል የተባሉት ኦነግ ሸኔ እና ህወሃት በሽብርተኝነት እንዲጠየቁ የምክር ቤቱ አባላት አሳስበዋል፡፡
* ብልጽግና ያለሰዉ ምንም ባለመሆኑ ህይወቱ እያለፈ ያለን ህዝብ ድምጽ መወከል አንችልም ሲሉ እንደራሴወቹ ገልፀዋል፡፡
* ኢትጵያ በአንድ ዘር የምትገነባ ባለመሆኗ ሁሉንም መጠበቅ ሃላፊነት የመንግስት ነዉ፤ ይህንን ሃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት ባለመቻሉ በንጹሃን ዜጎች ላይ ጭፍጨፋ እየደረሰ ነዉ ብለዋል፡፡
* በመንግስት መግለጫ ላይም ብሄሩን ላለመጥቀስ የሚደረግ ማሽሞንሞን ተገቢ ባለመሆኑ የተጨፈጨፈዉ አማራ ነዉ በሚል መስተካከል እንደሚኖርበት የምክር ቤቱ አባላት አንስተዋል፡፡
* ሀገሪቱ እንድትፈርስና እንድትበጣበጥ ይፈልጋሉ የሚባሉት ሃይሎች ባንክ ሲዘርፉ ዝም በመባላቸዉ ሃይል አጠናክረዋል፤ ህገወጥ ቡድኑ ከህጋዊዉ መንግስት በላይ ባለመሆኑ መንግስት የህዝብ ከለላነቱን እንዲያረጋግጥ ጠይቀዋል፡፡
* በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ የመከላከያ ሰራዊት በቦታዉ ሲነሳ በምትኩ ሌላ የፀጥታ ሃይል መተካት የነበረበት ቢሆንም ይህ ባለመሆኑ የአሠራር ክፍተት ብቻ ተብሎ መታለፍ የለበትም፡፡
* ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ብሔራዊ የመረጃ ደህንነት ሰላም ሚኒስቴር ፣ የመከላከያ ሚኒስትር እና ሌሎችንም የሚመለከታቸው አካላት መጥተው ማብራሪያና ምላሽ እንዲሰጡን እንፈልጋለን ብለዋል፡፡
* አልሸባብና አይ ኤስ ኤስን ለመመከት በሰው አገር ጭምር ሰላም የሚያስከብረው የመከላከያ ሰራዊታችን ፣ እውን ኦነግ ሸኔን ማሸነፍ አቅቶት ነው ወይ ሲሉ የጠየቁ የምክር አባላትም አሉ፡፡
* ከ2 ዓመት በፊት በለውጥ ስሜት ስራ ስንጀምር የነበረን ተስፋና ሞራል አሁን የለም ፤ ሲሉ በስሜትና በእንባ ታጅበው ሀሳባቸውን ሲገልፁ ተደምጠዋል፡፡
* የምዕራብ ወለጋ አካባቢ የሰላም የማጣት ችግር እንዳለበት እየታወቀ የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ ከሚችል ሌላ አካል ጋር ርክክብ ሳይደረግ መከላከያው ለምን ከዛ ስፍራ ለቆ ወጣ? የሚለው መጠናትና ሪፖርት መቅረብ ያስፈልገዋል፣ ከአስፈፃሚ የመንግስት አካላትም ማብራሪያ እንዲሰጠን እንፈልጋለን ብለዋል የምክር ቤቱ አባላት፡፡
* መንግስት ጥቃት በተፈፀመ ቁጥር፣ይህን ያደረገው እገሌ ነው እያለ በተደጋጋሚ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ጠላት ነው የተባለው ከታወቀ “ለምን የማያዳግም እርምጃ መውሰድ አልተቻለም”? ሲሉም ጠይቀዋል፡፡
የምክር ቤቱ አባላት በሙሉ በአንድ ድምፅ እና በተመሳሳይ ስሜት ውስጥ ሆነው ስለ ጉዳዩ በምሬት ሲናገሩ ሰምተናል፡፡
ሕዋሃት እና ኦነግ ሸኔ በምክር ቤቱ በሽብርተኝነት እንዲፈረጁ የጠየቁ የምክር ቤት አባላት ጠይቀዋል።፡
ከአባላቱ መካከል በዛሬው ስብሰባ ላይ ሙሉ ጥቁር ልብስና ጥቁር ሻርብ የለበሱ 15 ያህል ሴቶችንም ተመልክተናል፡፡
እንዲህ በጋለ ስሜት ከ2 ሰዓት በላይ ከተወያዩ በኋላ በአጠረ ጊዜ የመንግስት አስፈፃሚ አካላት በምክር ቤቱ ተጠርተው ስለ ጉዳዩ ማብራሪያ እንዲሰጡና አስፈላጊው ውሳኔ እንዲተላለፍ በመወሰን ወደ እለቱ አጀንዳቸው ተመልሰዋል፡፡
Filed in: Amharic