>

ጦርነቱ ተከፍቶአል ፤የእኛ ድርሻ ምንድነዉ? (ሃራ አብዲ)

ጦርነቱ ተከፍቶአል ፤የእኛ ድርሻ ምንድነዉ?

 

ሃራ አብዲ


ከሁሉ በፊት፤በመቀሌ በቅራቅርና በማይካድራ እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች አረመኔዋ የህወሀት ጦር በክህደት ለፈጃቸዉ የመከላከያ ሰራዊት አባላትና ራሳቸዉን መከላከል በማይችሉት ሰላማዊ ዜጎች ላይ ባደረሰው የዘር ፍጅት ለተሰዉት ወገኖቼ ይህ ነዉ ከምለዉ በላይ ማዘኔን እገልጻለሁ።

ህወሃት አዲስ አበባን በረገጠች ሰሞን በነፍሰ ገዳዮችዋ  ወንድሙን የገደለችበት ወዳጃችን ዮተናገረዉና ፈጽሞ ልረሳዉ የማልችለዉ አባባል አለ። «ኑዊ ሬፍ ኑ ጋአ» (ኦሮምኛዉ  ወደ አማርኛ ሲተርጎም፤ እኛ አስከሬኑ ይበቃናል) ማለት ነዉ።

ከሶስት አስርተ-አመታት እኩይና ወራዳ ተግባር ማብቅያ ላይ ወያኔ በሀገር የመከላከያ ሰራዊታችን ላይ የከፋ ክህደት ፈጽማለች። ከጀርባቸዉ ከወጋቻቸዉ በሁዋላ እርቃን ያስቀረችዉን አስከሬናቸዉን ከባ ጨፍራለች። የወዳጃችንን አባባል እንዳስታዉስ ያደረገኝም ይኸዉ ነዉ። አስከሬናችንን በክብር ብንቀብር ምን ነበረበት? ለሀዘናችን ማሳረጊያ አስከሬኑ ይበቃን ነበር። ኑዊ ሬፍ ኑ ጋኣ።

ከገደሉ በሁዋላ አስከሬን ክብር መንፈግ አንዱ የጦር ወንጀለኞች መለያ ነዉ። ሰለባ ባደረጉት ጦር ላይ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶችን መፈጸም፤ ለሰዎች አስከሬን ክብር መንፈግና በጅምላ ንጹሃ ዜጎችን መጨፍጨፍ ከጦር ወንጀሎች መስፈርት ዉስጥ ናቸዉ። አሁን ጦርነቱ ከጦር ወንጀለኞች ጋር ነዉ።( ይህ ጽሁፍ ተዘጋጅቶ ለሶስት ቀናት  ገደማ በእጄ ላይ ቆይቶአል፤ አሁን ይህ የጦር ወንጀል በአምነስቲ ኢንተርናሽናል ደረጃ እየተደረሰበት መሆኑ ይፋ ሲሆን  «ብዬ ነበር» ለማለት ቃጥቶኝ ነበር )

ኢትዮጵያ ተገድዳ የገባችበት ጦርነት። ትልቁ ጥያቄ በአሁኑ ሰአት መጋፈጥ ያለብን ከዚህ የጦር ወንጀለኛና ሰራዊቱ ጋር ነዉ ወይንስ የኢትዮጵያን መከላከያ ከሚመራዉ የጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛጝ ( ኮማንደር ኢን ቺፍ ጋር ነዉ)

 

ወያኔ ፍላጎትዋም ይህ ነዉ። ማዘን መብሰልሰላችን እንደተጠበቀ ሆኖ ታድያ፤ ከዚህ ዉጥንቅጡ ከወጣ የዉርደት እሽክርክሪት እንዴት ነዉ የምንወጣዉ?….

ይቀጥላል

 

 

Filed in: Amharic