>
5:16 pm - Monday May 24, 6179

ያለ እረፍት ሲሰለቅጥ የሚውለው ኦሮሙማ ያሻውን እንዲያደርግ ፈቅዶ በሞተው ሕወሓት ላይ ቃላት እየፈተሉ ሲራቀቁ  መዋል ሞያ አይደለም!  (አቻምየለህ ታምሩ)

ያለ እረፍት ሲሰለቅጥ የሚውለው ኦሮሙማ ያሻውን እንዲያደርግ ፈቅዶ በሞተው ሕወሓት ላይ ቃላት እየፈተሉ ሲራቀቁ  መዋል ሞያ አይደለም! 

አቻምየለህ ታምሩ


የብአዴን ሰዎች ፈጣሪያቸው የነበረውንና ጀርባቸው እስኪጎብጥ ድረስ ሲያገለግሉት የኖሩትን የሞተውን ሕወሓትን የሚንኳኩ ቃላትን እየሰደሩ ሲያነሱ ሲጥሉ መዋልን ፖለቲካቸው ያደረጉት ይመስላል። ሕወሓት ግብዓተ መሬቱ ተፈጽሟል። የሕወሓት ግብዓተ መሬት የተፈመጸው ሻዕብያን ተከትሎ አዲስ አበባ ከገባበት ከግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም. ጀምሮ ግብዓተ መሬቱ እስከተፈጸመበት እስከ ጥር 10 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ መስዕዋት በከፈሉ  አገር ወዳድ የኢትዮጵያ ልጆች ተጋድሎ ነው።

የሞተውን ሕወሓትን ሲያነሱ ውሎ ማደር ሞያ አይደለም። የሞተውን ሕወሓትን ሲወቅሱ መዋል ፈረንጆቹ እንደሚሉት “beating a dead horse” ነው።

ባሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ  ላይ የተጋረጠው አደጋ  የሕወሓትን አስተሳሰብ ይዞ በመንግሥትነት የተሰየመው በዐቢይ አሕመድ የሚመራው የኦሮሙማ የአፓርታይድ አገዛዝ ነው። በመላው ኢትዮጵያ ኢትዮጵያን ይወዳሉ በሚባሉ ነገዶች ላይ እየተካሄዱ የሚገኙ ጭፍጨፋዎችን ስፖንሰር እያደረገ የሚገኘው፣ ኦሮምያ ብለው የፈጠሩት የተስፋ ምድራቸው አጎራባች የሆኑን  ወረዳዎችና ዞኖች መውረሩ አልበቃ ብሎት በሱዳን ጭምር እንድንወረር [እስካሁን ያልተስተባበለውን የሱዳኑ ኢታማጆር ሹም ኢትዮጵያን የወረርነው በዐቢይ አሕመድ ፍቃድ ነው ያለውን መግለጫ ልብ ይሏል] እያደረገ ካለው፤ አገር ወዳዱን ኢትዮጵያዊ ሁሉ አዳክሞና አጥፍቶ ምድሩንም ሰማዩንም ኦሮሞ በማድረግ ኦሮሞን የሌላው የበላይ አድርጎ የኢትዮጵያውያን የጋራ ቋንቋ የሆነውን አማርኛን አዳክሞና አጥፍቶ [የዐቢይ ሹሙ ሺመልስ አብዲሳ የተናገረውን ልብ ይሏል] ኦሮሞኛን በአማርኛ ላይ የበላይ አድርጎ አማርኛ የማይነገርባትን ኢትዮጵያ እንደ አዲስ በኦሮምያቸው አምሳያ፣ ቅርጽ፡ ወርድና ስፋት የማበጀትና የመስራት አላማ ይዞ ያለ እረፍት እየተገበረ ከሚገኘውና ዘላቂ ጉዳት ሲያደርስ ከሚውለው  የዐቢይ አሕመድ ኦሮሙማ ፕሮጀክት የከፋ በአገራችን ላይ ያንዣበበ አደጋ የለም።

ባጭሩ ባሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ላይ የተጋረጠው አደጋ ወይም “the elephant in the room” የራበውና ሁሉ ብርቁ የሆነው በዐቢይ አሕመድ የሚመራው የኦሮሙማ የአፓርታይድ አገዛዝ እንጂ የበላውና የጠገበው፤ እንደ ድርጅትም ግብዓተ መሬቱ የተፈጸመው  ሕወሓት አይደለም። በመሆኑም በየሰርኩ ሲሰለቅጥ የሚውለውን ኦሮሙማን አይተው እንዳላዩ፤ ሰምተው እንዳልሰሙ ሆነው እየደገፉ  በሞተው ሕወሓት ላይ ቃላት ሲያጣምሩ መዋል ሞያ አይደለም!

ስለዚህ የሞተውን ሕወሓትን በሚንኳኩ ባዶ ቃላት ሲወቅሱ ውሎ ማደር ለአማራ መቆርቆራቸውን ማሳያ የሚመስላቸው ብአዴናውያን ቢኖሩ  በእውነት ለአማራ ሕዝብ የምትቆረቆሩ ከሆነ የሞተውን ፈረስ ሕወሓትን ስትደበድቡ መዋሉን ተውትና  አዲስ አበባን ከአፍ እስከ ደገፉ በየዕለቱ ሲሰለቅጥ በሚውለው፤ አማርኛን ማጥፋት ፕሮግራሙ ባደረገው፤ ኢትዮጵያን የምታህል ኦሮምያን የመፍጠር ሕልም ይዞ እየሰራ በሚገኘው፤ አማራ አያሳየን ብሎ ኢትዮጵያን የአማራ ተወላጆች በማንነታቸው በጅምላ የሚታረዱባት ቄራና የድኆች የጅምላ መቃብር እንድትሆን ያለ እረፍት እየሰራ በሚገኘው፤ በፈረንጆቹ አባባል “the elephant in the room” በሆነው የዐቢይ አሕመድ የኦሮሙማው ፕሮጀክት ላይ አምጹ! እንዴው እንደምን አይነት ፍጡራን ብትሆኑ ነው በሰላሳ ዓመታት ውስጥ አማራ ተበደለ ብሎ የሚያምጽ አንድ ሰው እንኳን ከመካከላችሁ የጠፋው?

የሕወሓትን የ27 ዓመታት የነውረኛነት ክብረ ወሰን በአስር ወራት ውስጥ የሰበረውን፣ ጎጃም በነበረው መተከል አማራ እና አገው «አገራችሁ አይደለም» ተብለው እንደ ፋሲካ ዶሮ በየዕለቱ በጭካኔ እንዲታረዱ፤ ለመስማትም ለማየትም በሚዘገንን መልኩ የእርጉዝ ሴት ማሕጽን ተቀዶ ጽንሱ ሜዳ ላይ እንዲጣል፤ ገበሬዎች በማሳቸው ላይ እንዳሉ፣ እናቶችና ሕጻናት ቤታቸው በተቀመጡበት በዐይናቸው፣ በአፍንጫቸውና በጀርባቸው ላይ በመርዝ በተነከረ ክርክር ያለው ቀስት እየተቀደዱ በምድር ላይ ተፈጽሞ የማያውቅ የጅምላ ፍጅት በየሰርኩ እንዲፈጸማቸው እያደረገ የሚገኘው ሰልቃጩ በዐቢይ አሕመድ የሚመራውን የኦሮሙማ አገዛዝ ትናንትና ሕወሓት ሲያደርግ የነበረውን  ነውረኛነት ሁሉ ያለ ከልካይ እንዲያደርግ ፈቅዶ ለመስዕዋትነት በቆረጡ የሕዝብ ልጆች ተጋድሎ ገብዓተ መሬቱ የተፈጸመውን ሟቹን ሕወሓትን እንጨት እንጨት በሚሉ ባዶ ቃላት ሲደበድቡ መዋል ግብዝነት ነው።

 

Filed in: Amharic