>

የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ አሻራ በብሔረሰብ ጥያቄ ላይ  ( በባሕሩ ዘውዴ፣ የታሪክ ፕሮፌሰር - ኤሚሪተስ)

የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ አሻራ በብሔረሰብ ጥያቄ ላይ 

በባሕሩ ዘውዴ፣ የታሪክ ፕሮፌሰር – ኤሚሪተስ

የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ከ1950ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ዕጣ ፈንታ ላይ ወሳኝ ሊባል የሚችል ጫና አሳድሯል። የኢትዮጵያ ተማሪዎች ዐሠርት ያህል በቆየው የፖለቲካ ትግላቸው ካነሷቸው ጥያቄዎች መካከል ሁለቱና መሠረታዊ ሊባሉ የሚችሉት የመሬት እና የብሔረሰብ ጥያቄ ናቸው። በየካቲት 1958 “መሬት ለአራሹ!” የሚል መፈክር በማንገብ አደባባይ ወጡ። ያ ጥያቄም ሲንከባለል ቆይቶ ከዘጠኝ ዓመት በኋላ በ1967ቱ ስር ነቀል የመሬት አዋጅ የመጨረሻ ምላሹን አገኘ። በጥቅምት 1962 ዋለልኝ መኰንን በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ልደት አዳራሽ ለመጀመሪያ ጊዜ የብሔረሰብን ጥያቄ በማንሳት ትልቁን ቦንብ አፈነዳ። ያኔ የተጫረው ሐሳብም ከዐሠርት ዓመታት የብሔረሰባዊ ትጥቅ ትግል በኋላ ኢሕአዴግ በ1983 የፖለቲካ ሥልጣንን ሲጨብጥ መጀመሪያ በሽግግር መንግሥቱ ቻርተር፣ ቀጥሎም በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አማካይነት ሕጋዊ መሠረት አገኘ።
የዚህ ጽሑፍ ዓላማ የዚህን የሁለተኛውን የተማሪዎች መሠረታዊ ጥያቄ ከትንሣዔው እስከ ማሳረጊያው ለመቃኘት ነው። ጥያቄው ለምንና እንዴት እንደተነሣ፤ በጥያቄው፣ በተለይም በመፍትኄው፣ ዙሪያ የነበረውን የጋለ ክርክርና ብሎም መከፋፈል፤ ከ1983 በኋላ መፍትኄው ከነችግሮቹ የመንግሥት ፖሊሲ እንዴት ለመሆን እንደቻለ ይዳስሳል። ከዚያ በፊት ግን ለብሔረሰብ ጥያቄ መነሳት መሠረታዊ ምክንያት የሆነው የኢትዮጵያ ቅድመ ሁኔታ በአጭሩ ይቀርባል።
ቅድመ ሁኔታ
በዘመነ ኃይለ ሥላሴ ወይም በዘመነ ደርግ ለኖረ ሰው ኢትዮጵያ ዝንተ ዓለም አሓዳዊ መንግሥት የነበራት መስሎ ሊታየው ይችል ይሆናል። የሀገሪቱ ታሪክ የሚያሳየው ግን ይህን አይደለም። ይልቁንስ ታሪክ የሚያሳየን ለረጅም ዘመናት የመንግሥት አሥተዳደር ያልተማከለ እንደነበረ ነው። “ንጉሠ ነገሥት” የሚለው የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣን መጠሪያ ራሱ የሚያመለክተው ከእሱ ስር በግዛታቸው አሥተዳደር የነበራቸው መሪዎች እንዳሉ ነው። የእርሱን የበላይነት የሚያውቁት በየዓመቱ፣ ብዙውን ጊዜም በትልቅ አጀብና ወግ በሚያቀርቡት ግብር ነው። ከዚያ በተረፈ ግን ንጉሠ ነገሥቱ በውስጥ አሥተዳደራቸው ጣልቃ አይገባም ነበር። በመካከለኛው ዘመን የነበሩት ግዛታዊ ባለ ማዕረጎች (ባሕረ ነጋሽ ወይም ማዕከለ ባሕር፣ የትግሬ መኰንን፣ ፀሐፌ ላም፣ ቢትወደድ፣ ወዘተ…) ለዚህ ያልተማከለ አሥተዳደር ጉልህ ማስረጃዎች ናቸው።
ይህ ያልተማከለ አሥተዳደር በአፄ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት የመለወጥ አዝማሚያ አሳይቶ ነበር። ይሁን እንጂ የቴዎድሮስ መሠረታዊ ዓላማ አሓዳዊ መንግሥት ለመመሥረት ሳይሆን፣ በዘመነ መሣፍንት በእጅጉ ተዳክሞ የነበረውን አፄያዊ ሥልጣን የቀድሞ ግርማና ሞገሱን ለማስመለስ ነበር። አሓዳዊ መንግሥት ልመሥርት ቢል እንኳ የጊዜው የአገሪቱ የመሠረተ ልማት ሁኔታ አይፈቅድለትም ነበር። የመገናኛ አውታሮች ባልዳበሩበት፣ የፋይናንስ አቅም ባልጎለበተበት፣ ብሔራዊ የጦር ሠራዊት ባልደረጀበት ሁኔታም ይህን ለማድረግ አይችልም ነበር። ስለሆነም የራሱን ሹማምንት ከሰየመባቸው ከመቅደላና ከጎጃም በስተቀር አብዛኛውን ጊዜ የአካባቢውን ተወላጆች ነበር የሚሾመው። ለዚህም በሸዋ የሣህለ ሥላሴ ልጅ የሆነውን ኃይለ ሚካኤልን፣ በትግራይ የሹም አጋሜ ሱባጋዲስ ልጅ የሆነውን ካሣን መጥቀስ ይቻላል።
በተከታዩ የአፄ ዮሐንስ ዘመነ መንግሥት ደግሞ የአሓዳዊ መንግሥት ሐሳብ ጭራሽ ደብዛው ጠፍቶ “ፌዴራላዊ” ሊባል የሚችል የአሥተዳደር ስሪት ሰፍኖ ነበር። አፄ ዮሐንስ ንጉሠ ነገሥት ከመሆኑ በፊት ይጠራበት የነበረው “ርዕሰ መኳንንት” የሚለው ማዕረግ ራሱ የሚያመለክተው ይህንኑ ቅኝት ነው፤ ፍጹም አምባገነንነትን ሳይሆን፣ የአቻዎች አውራነትን (primus inter pares, first among equals)። ስለሆነም በ1870 የምኒልክን ከአያቱ የወረሰውን የሸዋ ንጉሥነት ሲያፀድቅለት፣ ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ የጎጃሙን ራስ አዳል ተክለ ሃይማኖት አሰኝቶ “የጎጃምና የከፋ ንጉሥ” ብሎ ሾመው። በዚህ ረገድ በ1870 በንጉሠ ነገሥት ዮሐንስና በንጉሥ ምኒልክ መካከል የተፈረመው የመከባበር ስምምነት የዚህ “ፌዴራላዊ” ስሪት ጉልህ ማስረጃ ነው። ስምምነቱ የተፈረመበት በሰሜን ሸዋ የሚገኘው ልቼ የተባለው ሥፍራም በኢትዮጵያ ታሪክ ልዩ ቦታ ለማግኘት ችሏል፡፡
የምኒልክ አሥተዳደር ስሪት የመስፋፋት ፖሊሲው ነፀብራቅ የሆኑ ሁለት ገፅታዎች ነበሩት። በሰላም አንገብርም ባሉትና ጦርነት በገጠሙት የደቡብ ግዛቶች ላይ ከድል በኋላ የራሱን ሰዎች ሲሾም፤ በሰላም የገበሩትን የአካባቢ መሪዎች ግን የማዕከላዊውን መንግሥት ማዕረግ (ደጃዝማች) ሰጥቶ ግዛታቸውን በሙሉ ነፃነት እንዲያስተዳድሩ ፈቅዶላቸዋል። ለመጀመሪያው ስልት ማስረጃ የሚሆኑት ግዛቶች አርሲ፣ ሐረር፣ ከፋ ሲሆኑ፣ ለሁለተኛው ደግሞ የሌቃ ነቀምቴውን ኩምሳ (ገብረ እግዚአብሔር) ሞሮዳ፣ የሌቃ ቄለሙን ጆቴ ቱሉ እና የጂማውን አባ ጂፋር በማስረጃነት መጥቀስ ይቻላል። ከዚያም አልፎ ከሌላ ብሔረሰብ የመጡ የጦር መሪዎችንና ነገር አዋቂዎችን በማስጠጋት ለከፍተኛ ማዕረግ አብቅቷቸዋል። በዚህም ረገድ በተለይ ለመጥቀስ የሚቻለው በግዛት ማስፋፋቱ ቁልፍ ሚና የነበረውን ጎበና ዳጨን እና በተለይም መሬት የማይወድቅ ምክር በመስጠት ልዩ ከበሬታ ያገኘውን የጨቦውን ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴን መጥቀስ ይቻላል።
ከላይ እንደተጠቆመው የአሓዳዊ መንግሥት ምሥረታ ጉልህ እየሆነ የመጣው በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ነው። ይህ ሂደት ገና በንጉሠ ነገሥቱ የአልጋ ወራሽነት ዘመን ጀምሮ ከንግሥናው በኋላ ደግሞ እየተጠናከረ ሄደ። ከንግሥናው በፊት ከተንበረከኩት መካከል የሲዳሞው ገዥ ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ እና የንግሥት ዘውዲቱ ባልና የቤጌምድር መስፍን ራስ ጉግሣ ወሌ ተጠቃሽ ናቸው። ከንግሥናው በኋላ ደግሞ በ1924 ገናና እና ሀብታም የነበረውን የጎጃሙን ራስ ኃይሉን፣ ልጅ ኢያሱን ከፍቼ እስር ቤት አስመልጠሃል በሚል ወንጀል በማሰር ግዛቱን ጠቀለለው። በዓመቱ አባ ጂፋር 2ኛ ሲሞት ደግሞ እስከዚያ ድረስ ተከብሮ የኖረውን የግዛቱን የውስጥ አስተዳደር ነፃነት በመሻር የማዕከላዊውን መንግሥት ሹም አስቀመጠ። ይህ የአሓዳዊ መንግሥት ግንባታ ሂደት ሁለት ዐቢይ መሠረቶች (ፋይናንሳዊና ሕጋዊ) ነበሩት። ፋይናንሳዊው የተማከለ የግብር አሰባሰብ ሥርዓት ሲሆን፣ ሕጋዊው ደግሞ በ1923 የታወጀው የመጀመሪያው ሕገ መንግሥት ነው። የሕገ መንግሥቱ ዋና ዓላማ ሕዝቡን  ሲቪክ መብቶች ለማጎናፀፍ ሳይሆን፣ የመሣፍንቱን ግዛታዊ ሥልጣን ለመገደብ ነበር።
ይህ የአሓዳዊ መንግሥት ግንባታ ሂደት በጣልያን ወረራ ምክንያት ከተቋረጠ በኋላ ነፃነት ሲመለስ ደግሞ እንደገና ተጠናክሮ ቀጠለ። በዚህ ረገድ ቁልፍ ሥፍራ የሚይዘው በ1934 የታወጀው የጠቅላይ ግዛት አስተደደር አዋጅ ነው። በዚህ አዋጅ መሠረትም የኢትዮጵያ የሃያኛው መቶ ዓመት መለያ የሆነው የተማከለ አስተዳደር ተመሠረተ። የግዙፉ የአገር ግዛት ሚኒስቴር ቁጥጥር በ12ቱም (ኋላ 14ቱም) ጠቅላይ ግዛቶች እስከ ወረዳ አስተዳደር ድረስ ዘለቀ። ከዚህ የተማከለ አስተዳደር በመጠኑም ቢሆን የተረፉት የአካባቢው ተወላጅ በሆኑ መሣፍንት ይተዳደሩ የነበሩት ወለጋና ትግራይ ነበሩ። ስያሜዎች በጊዜ ሂደት እየለዘቡ ቢመጡም (ለምሳሌ አገር ግዛት በማለት ፈንታ አገር አስተዳደር፣ ጠቅላይ ግዛት በማለት ፈንታ ክፍለ ሀገር፣ ጠቅላይ ገዥ በማለት ፈንታ አስተዳዳሪ) ማዕከላዊነቱ አልተለወጠም። ሁኔታው የተለወጠው የኢፌዴሪን ምሥረታ ተከትሎ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሲፈርስ ብቻ ነው።
የአፄ ኃይለ ሥላሴ የተማከለ መንግሥት ምሥረታ በአገር ግንባታ ቁልፍ ሚና የተጫወቱ ሌሎች ዓምዶችም ነበሩት። ከነዚህም መካከል ብሔራዊ የጦር ሠራዊት ማቋቋሙ ልዩ ሥፍራ የሚሰጠው ነው። ሠራዊቱ ማዕከላዊው መንግሥት ዳር አገሮችን ጨምሮ በጠቅላይ ግዛቶች ላይ ያለውን የበላይነት ከማረጋገጡም ባሻገር ከተለያዩ ብሔረሰቦች የመጡ ኢትዮጵያውያን አብረው የሚኖሩበትና የሚሞቱበት ተቋም በመሆኑ ኢትዮጵያዊነትን ለማስረግ የማይናቅ ሚና ተጫውቷል። በተመሳሳይ መንገድም እየተስፋፉ የመጡት የትምህርት ተቋማት የቀለም ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያዊነትም ትምህርት ቤት ነበሩ ለማለት ይቻላል። እንዲሁም በስፋት የተዘረጉት የመሠረተ ልማት አውታሮች ወረዳዎችን ከጠቅላይ ግዛት፣ ጠቅላይ ግዛቶችን ከማዕከላዊው መንግሥት ጋር ለማገናኘት ወሳኝ ሚና ተጫውተዋል፡፡ በተለይም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በየብስ ለመድረስ ከባድ የሆኑትን ቀዬዎች ሳይቀር ከማዕከሉ ጋር ለማገኛኘት ችሏል። አየር መንገድ ባይኖር ኖሮ አብዛኛው ሕዝብ እንደ ቴፒ፣ ቀላፎና መስሎ የመሳሰሉትን ቦታዎች ሊያውቅ መቻሉ ያጠራጥራል። አየር መንገዱ ሞቶው ወይም መመሪያው እንደሚያመለክተው አፍሪካን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያንም ነው ያቀራረበው “Bringing Africa Together!” ብቻ ሳይሆን “Bringing Ethiopia Together”)።
ይህ ከላይ የተገለፀው የአሓዳዊ መንግሥት ግንባታ በዘመነ ደርግ ደግሞ ይበልጥ ከሮ አገሪቱን ለፍፁማዊ አገዛዝ ዳረጋት። ምናልባትም በኢትዮጵያ ታሪክ እንደዚያን ጊዜ መንግሥት የዜጎቹን ሕይወት የተቆጣጠረበት ወቅት ነበር ብሎ ማሰብ ያዳግታል። ይህ ቁጥጥር ስሙ ተሞካሽቶ አገር አስተዳደር በተባለው ሚኒስቴር አማካይነት ብቻ ሳይሆን ገበሬውን በሚቆጣጠሩት የገበሬ ማኅበራት፣ ከተሜውን በሚዳኙት ቀበሌዎችና ወጣቱን፣ ሴቶችንና ሠራተኛውን የደርግ ሠራዊት ባደረጉት የብዙኃን ድርጅቶች አማካይነት ጭምር ነበር።
የጥያቄው መንስዔዎች
በ1962 እንደ ድንገት የተነሳውን የብሔረሰብ ጥያቄ መንስዔዎችን በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል፤ የረጅም ጊዜና የአጭር ጊዜ። የጥያቄው ዋነኛ የረጅም ጊዜ መንስዔ ከአፄ ምኒልክ የግዛት ማስፋፋት ሂደት በተጓዳኝ የሰፈነው የብሔረሰብ ጭቆና ነው። ኋላ በተማሪዎች ንቅናቄ ውስጥ በጥያቄው መፍትኄ ላይ የሐሳብ ልዩነት ቢፈጠርም በጭቆናው ነባራዊነት ላይ ሙሉ ስምምነት ነበር። በተለይ በደቡቡ የኢትዮጵያ ክፍል ጭቆናው ብዙ ገፅታዎች ነበሩት። የአስተዳደር ነፃነት ከማጣት አንስቶ፣ መሬት እስከ መነጠቅ፣ በባርነት እስከ መጋዝ ዘልቋል። በባርነት መጋዝን በተመለከተ በተለይ በወላይታ፣ ከፋ እና ጊሚራ የደረሰው እልቂት ከባድ ጠባሳ ትቶ አልፏል። ከዚህ ተያይዞም የብሔረሰቦቹ ባሕልና ቋንቋ ተዋርዷል። በትግራይ ደግሞ ላይ ከተጠቀሰው ዓይነት ጭቆና ይልቅ ከአፄ ዮሐንስ ሞት በኋላ ከማዕከላዊ ሥልጣን መገለል ቁጭት አሳድሯል።
ወደ ቅርብ ጊዜ መንስዔው ስንመጣ ደግሞ እ.አ.አ. ከ1961 ጀምሮ በኤርትራ ምድር የተቀሰቀሰው የመገንጠል እንቅስቃሴ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ነው። ተማሪዎችም ሆኑ ሌሎች ተራማጅ ኃይሎች ይህን እንቅስቃሴ ኢትዮጵያውያን ለዲሞክራሲና እኩልነት የሚያደርጉት ትግል አጋር ለማድረግ በማሰብ በጦርነት ሳይሆን በሰላማዊ መንገድ መፍትኄ ማግኘት እንዳለበት ማመን ጀመሩ። በሌላ በኩል ወቅቱ በኦሮሞዎችም ዘንድ ብሔረሰባዊ ስሜት ያቆጠቆጠበት ነበር። ለአብነትም የሜጫ ቱለማ መረዳጃ ማኅበርንና የባሌ ገበሬዎችን አመፅ መጥቀስ ይቻላል።
ሌላ እንደ ቅርብ ጊዜ መንስዔ ሊታይ የሚችለው ሁኔታ ደግሞ በ1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ተቋማት በተማሪዎች መካከል የተከሰቱት ብሔረሰባዊ ግጭቶች ናቸው። እነዚህ ግጭቶች በኤርትራውያንና በመሃል አገር ተማሪዎች፣ በትግራዋዮችና ሌሎች ብሔረሰቦች መካከል የተከሰቱ ሲሆኑ የነዚህ ግጭቶች አውድማ በመሆን ደግሞ የልዑል በዕደ ማርያም የዩኒቨርሲቲ መሰናዶ ት/ቤት፣ የጄኔራል ዊንጌት ት/ቤትና የባሕር ዳር ፖሊቴክኒክ ተጠቃሽ ነበሩ። ይህ ሁኔታ አሳስቧቸውም የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ማኅበርና በወቅቱ የነበሩ ‘ራዲካል’ የሚባሉ የተማሪ መሪዎች ተማሪው ከእንዲህ ያለው የጠባብነትና የጎጠኝነት አስተሳሰብ እንዲርቅ ማሳሰብ ጀምረው ነበር።
የጥያቄው አነሳስና ሂደት
ብዙውን ጊዜ የብሔረሰብ ጥያቄ አነሳስ ከዋለልኝ መኰንን ስም ጋር ተያይዞ ነው የሚቀርበው። በእርግጥም ጉዳዩን ለመጀመሪያ ጊዜ አደባባይ ያወጣው እርሱ ነው፤ መጀመሪያ በጥቅምት 1962 ልደት አዳራሽ ባቀረበው ጽሑፍና አከታትሎም ታገል በሚባለው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ማኅበር (ኡዙዋ) ልሳን ላይ አሳትሞ በማውጣቱ። ይህ ሥርዓቱን ብቻ ሳይሆን ተማሪውን ጭምር ድንገት እንደ መብረቅ የመታውን ሐሳብ ከየት አመጣው የሚለው ጥያቄ ተደጋግሞ ተጠይቋል፤ አግባብነትም አለው። ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠው መልስ በ1961 “ለአዋጁ አዋጅ” በሚል ርዕስ ንጉሠ ነገሥቱን ከፍ ዝቅ አድርጎ በመዝለፉ ምክንያት አምስት ዓመት ተፈርዶበት እስር በቆየበት ወቅት ካገኛቸው ከኤርትራ ግንባር አባላትና ከባሌ አመፅ መሪዎች ጋር በመቀራረቡ የተቀሰቀሰበት ስሜት ነው የሚል ነው። ከዚህ በተጨማሪም በዚያው ዓመት ክረምት ላይ የዘመኑ አብዮተኞች የብሔረሰብን ጉዳይ ቸል ማለት እንደማይቻልና አልፎ ተርፎም በብሔረሰብ ላይ የተመሠረቱ ትግሎችን ዕውቅና መስጠት እንደሚያስፈልግ ተስማሙ። ምንም እንኳ ዋለልኝ እስር ላይ በመሆኑ በዚህ ስብሰባ ባይገኝም ለአዲሱ ዓመት ምኅረት ተደርጎለት ከወጣ በኋላ ውጤቱን የሰማውና የተቀበለውም ይመስላል። ያም ሆነ ይህ ዋለልኝ ያቀረበው ጽሑፍ ዋና ማጠንጠኛው ኢትዮጵያ የአንድ ብሔር ብቻ ሳይሆን የብዙ ብሔረሰቦች አገር እንደሆነችና የብሔረሰባዊ አርነት ትግሎችም ዓላማቸው መገንጠልም ቢሆን ሶሻሊስታዊ እስከሆኑ ድረስ ሊደገፉ እንደሚገባቸው ነው።
እንዳጋጣሚ ሆኖ በዚያው ክረምት በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማኅበር (ኤዙና) 17ኛ ዓመታዊ ጉባዔውን ሲያካሄድ ዋና መወያያ ርዕሱ ይኸው ጉዳይ ነበር። ሆኖም ጉባዔው “የብሔረሰብ ጥያቄ” ከማለት ይልቅ የአካባባዊነት ችግር (በእንግሊዝኛው the problem of regionalism) ማለትን መርጧል። የማኅበሩ አንጋፋ መሪዎች ባቀረቧቸው የጥናት ወረቀቶች ላይ ተመርኩዞ ጉባዔው ከተወያየ በኋላ መጨረሻ ባሳለፈው ውሳኔም አካባባዊነትንና የመገንጠል እንቅስቃሴዎችን በማውገዝ የተራማጆች ዋነኛው ትኩረት በመደብ ትግል ላይ መሆን እንዳለበት በአጽንኦት አስቀመጠ።
ከአንድ ስድስት ወራት በኋላ ይህን የኤዙናን አቋም በመፃረር በ1961 መጨረሻ ላይ አውሮፕላን ጠልፈው ከኢትዮጵያ በመውጣት መጠለያቸውን በአልጄሪያ ያደረጉ ታጋዮች (ብርሃነ መስቀልና ጓዶቹ) ጥላሁን ታከለ በሚል የብዕር ስም ሰፊ ትችት አቀረቡ። እስከዚያን ጊዜ ድረስ እምብዛም የተለመደ ባልነበረ ኃይለ ቃል የታጀበው ይህ ጽሑፍ የኤዙና መሪዎችን አቋም በማብጠልጠል በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ብሔሮች እንዳሉ፣ በነሱ ላይ የተመሠረቱ ትግሎችንም በተመለከተ አብዮታውያን ሊከተሉ የሚገባቸው መርህ “የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠል ድረስ” እንደሆነ አበክረው ገለፁ። የመገንጠል መብትን መደገፍ መገንጠልን ከማበረታቱ ይልቅ ፍትሓዊ አንድነትን ያጎለብታል ብለው ሞገቱ። በዚህ ረገድም በኅብረ-ብሔራዊ ተራማጅ ድርጅት ውስጥ ላሉ ታጋዮች የሥራ ክፍፍል በመፍጠር፤ ከጨቋኝ ብሔር የመጡት የመገንጠል መብትን ሲደግፉ፣ ከጭቁን ብሔር የመጡት ደግሞ በመፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ አንድነት መስበክ እንደሚገባቸው ገለፁ።
ከአንድ ዓመት ግድም በኋላ የኤዙና መሪዎች ለጥላሁን ታከለ ጽሑፍ መልስ ሰጡ። ቱምቱ ሌንጮ በሚል የብዕር ስም አንድርያስ እሸቴ በጻፈው ረዘም ያለ ትንተና ጥላሁን ታከለ በጽሑፉ ደጋግሞ በጠቀሳቸው የሌኒን እና ስታሊን ጽሑፎች ላይ በመመርኮዝ የብሔረሰብ ጥያቄ ምንጊዜም ቢሆን ከመደብ ጥያቄ ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ የሚታይ ቅራኔ እንደሆነ፤ ስለሆነም የአርነት ንቅናቄዎች ሊደገፉ የሚችሉት ዋናውን ፀረ-ፊውዳልና ፀረ-ኢምፔሪያሊስት ትግል እስካለደናቀፉ ድረስ ነው ብሎ ተከራከረ። እነ ጥላሁን ታከለ በመገንጠል መብት ላይ ያላቸውን ሙዝዝ ያለ አቋም በመተቸትም የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ዒላማው መገንጠል ሳይሆን ክልላዊ የውስጥ አስተዳደር (Regional Autonomy) መሆን ይገባዋል ብሎ ደመደመ።
እነዚህ ርዕዮተ ዓለማዊ ክርክሮች ለድርጅታዊ አቋም መግለጫዎች መቅድም ነበሩ። ማሳረጊያቸውን ያገኙትም በ1963 ክረምት ላይ በተከታታይ በበርሊንና ሎስ አንጀለስ በተደረጉት የተማሪ ማኅበራት ጉባዔዎቸ ላይ ነው። መጀመሪያ በሐምሌ ወር በርሊን በተደረገው የአውሮፓ ኢትዮጵያ ተማሪዎች ማኅበር 11ኛ ዓመታዊ ጉባዔ ሰፊ ክርክር ከተደረገ በኋላ የነጥላሁን ታከለ አቋም አብላጫ ድምፅ አግኝቶ “የራስን ዕድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል” የሚለው መርህ የማኅበሩ አቋም ለመሆን በቃ። ቀጥሎም በነሐሴ ወር በሎስ አንጀለስ በተደረገው የኤዙና 19ኛው ዓመታዊ ጉባዔ ይኸው አቋም የበላይነትን ሲያገኝ በፕሬዚዳንቱ በሠናይ ልኬ የሚመራው ቡድን ስብሰባውን ረግጦ ወጣ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ኤዙና ለሁለት ተከፈለ።
ውሎ አድሮም በ1963 መጨረሻ ላይ የበላይነትን ያገኘው ይህ አቋም ከተማሪ ማኅበራትም አልፎ ከዚያ የመነጩት የግራ ፖለቲካ ድርጅቶችም አቋም ለመሆን በቃ። በዚህ ረገድ፣ ኢሕአፓ፣ መኢሶን እና ሕወሓትም ይህን መርኅ በመተዳደሪያ ደንባቸው ውስጥ አካተቱ። የግራ ክንፍ ኃይሎች ይህን መርህ ሲደግፉ በተለይ ያተኩሩ የነበረው በኤርትራው የአርነት ትግል ላይ ነበር። እምነታቸውም ኤርትራውያን እስከ መገንጠል ድረስ ላላቸው መብት ዕውቅና በመስጠት ትግላቸውን የመላው ኢትዮጵያ ትግል አጋር ለማድረግ እና ለችግራቸውም በዚያው ማዕቀፍ ውስጥ መፍትኄ ለመሻት ነበር። ይሁን እንጂ የኤርትራ ግንባሮች የኤርትራ ጥያቄ የብሔር ሳይሆን የቅኝ ግዛት ጥያቄ ነው፤ ስለሆነም መፍትኄው ሊሆን የሚችለው ነፃነት ብቻ ነው ሲሉ ይህ ስሌት ከሸፈ። ኢሕአፓና መኢሶንም በፊት የወሰዱትን አቋም ለመከለስ ተገደዱ። በተቃራኒው ሕወሓት የቅኝ ግዛት ጥያቄን ሙሉ በሙሉ በመቀበል የኤርትራ ነፃነት ግንባሮች (በተለይም የሻዕቢያ) አጋር ሆነ፤ በመጨረሻም ለድል በቃ።
በተማሪዎች ማኅበራትም ሆነ በግራ ክንፍ የፖለቲካ ድርጅቶች ዘንድ በብሔረሰብ ጥያቄ ዙሪያ የተደረጉትን ክርክሮችና መጨረሻ የተደረሰበትን ውሳኔ ጠለቅ አድርገን ስንመረምር ብዙ ጉድለቶችን እናገኝበታለን። የመጀመሪያውና ምናልባትም ዋነኛው ጉድለት ተሟጋቾቹ ስለ አገራቸው የነበራቸው ዕውቀት ምን ያህል አናሳ እንደነበር ነው። የክርክሮቹ መሠረት የማርክሲስት ቀኖና እንጂ ያገሪቱ ታሪካዊና ነባራዊ እውነታ አልነበረም። ሐቅ የሚገኘው ከሌኒንና ስታሊን ጽሑፎች እንጂ ባገሪቱ ላይ ከተጻፉት አያሌ የታሪክና የኤትኖግራፊ መጻሕፍት አልነበረም። በዚህ ረገድ በተለይ የጥላሁን ታከለ ጽሑፍ ከፍተኛ ጉድለት ይታይበታል። ያገሪቱን ብሔረሰቦች ሲዘረዝር ከተራ ስድብ ያለፈ ፋይዳ የሌለውን “ሻንቅላ” የሚለውን ስያሜ ከመጨመሩም በላይ የኦሮሞ ብሔረሰብ አካል የሆኑትን አርሲ፣ ባሌ እና ቆቱ ራሳቸውን እንደቻሉ ብሔረሰቦች አድርጎ ይዘረዝራቸዋል።
ሁለተኛው ጉድለት በጥላሁን ታከለ ተጀምሮ በቱምቱ ሌንጮ የቀጠለው ሐሳብን በከረረ ቋንቋ (polemics) የመግለፅ አባዜ ነው። ይህ አባዜም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የተማሪ ማኅበራትን፣ ከዚያም የግራ ክንፍ ድርጅቶችን፣ ተጠናውቶ የማታ ማታ ወደ መጠፋፋት ፖለቲካ መራቸው። በቃላት የተጀመረው አመፅ ወደ ጦር መሣሪያ አመፅ ተሸጋገረ። ፍፃሜውም ሁላችንም እንደምናውቀው ኅብረ ብሔራዊ ድርጅቶችን ከጨዋታ ውጪ አድርጎ ለብሔረሰባዊ ድርጅቶች ጥርጊያ መንገድ ከፈተ። ይህም ሁኔታ ከ1983 ጀምሮ እስከ ቅርብ ጊዜ የቆየውን የብሔረሰብ ፖለቲካን አነገሠ።
ሦስተኛው ጉድለት ብሔርና ብሔረሰብ በሚሉት ጽንሰ ሐሳቦች ላይ የነበረው ብዥታ ነው። ጥያቄው በሚነሳበት ጊዜ እንኳ አንዳንዴ “የብሔር ጥያቄ”፣ ሲያሰኝ ደግሞ “የብሔረሰብ ጥያቄ” ይባል ነበር። እርግጥ አንዳንዴ ብሔረ ሰብ ለቅድመ-ካፒታሊስት፣ ብሔር ደግሞ ለካፒታሊስት ማኅበረ ሰብ ነው የሚውለው የሚል ሐሳብ ይቀነቀን ነበር። እነ ጥላሁን ታከለም የ1963ቱን ክርክር ያሸነፉት በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ “በፍጥነት ወደ ብሔርነት በመሸጋገር ላይ ያሉ ብሔረሰቦች” የሚገኙበት ነው በማለት ነበር። ይህን ሲሉ ግን ከላይ እንደጠቀስነው በርግጥ የኢትዮጵያን ታሪካዊና ነባራዊ ሁኔታ በማጤን ሳይሆን በቀኖና ላይ ተመርኩዘው ነበር። ይህ ውዥንብር አልበቃ ብሎ ደግሞ ኋላ ምንነቱ በውል ያልታወቀ “ሕዝብ” የሚል ካታጎሪ ተደነጎረ፤ እስካሁንም አለ።
አራተኛው ጉድለት ቱምቱ ሌንጮ እንዳስቀመጠው በመገንጠል መብት ላይ ሙጭጭ ማለት ነው። ይህን አቋም ችክ ብለው የያዙትም በኢትዮጵያ ሁኔታ ያዋጣል ወይስ አያወጣም ከሚል እሳቤ ሳይሆን የነስታሊን ቀኖና ስለነበረ ብቻ ነው። የመርሁ አቀንቃኝ ስታሊን ራሱ የገዛ ትውልድ ግዛቱ ጆርጂያ ለመገንጠል ስትንሳቀስ እንደ እባብ ራስ ራሷን ቀጥቅጦ እንዳላስገበራት ሁሉ፤ ለኢትዮጵያ የሚሠራው ብቸኛው መንገድ ይህ ነው የሚል አቋም በከረረ ሁኔታ ተስተጋባ። ኤርትራን ከመገንጠል ያድናል የተባለው መርህም ለኤርትራ መገንጠል መንገዱን አመቻቸ።
አምስተኛው ጉድለት ደግሞ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብቱስ ይታወቅ፤ ለመሆኑ ይህን መብት መጠየቅ የሚችለው ማነው ለሚለው ጥያቄ አጥጋቢ መልስ ለመስጠት አለመቻሉ ነው። ከልምድ እንደታየው ጥቂት ልኂቃን ተሰባስበው “የነፃነት ግንባር” አቋቁመው ጦርነት በመክፈት ምንም በማያውቀውና ፍላጎቱንም ባልተጠየቀው በሰፊው ሕዝብ ስም የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ከዚያም አልፎ የመገንጠልን አጀንዳ ሊያራምዱ ይችላሉ። ዲሞክራሲ ባልዳበረበት ኅብረተሰብም በብዙኃን ስም የተጀመረ እንቅስቃሴ የጥቂቶች ሥልጣን መወጣጫ እና ብሎም መበልፀጊያ ይሆናል።
አሻራው
ተማሪዎች መጀመሪያ ያቀነቀኑት የብሔረሰብ ጥያቄ ከአምስት ዐሠርት በኋላም ገዢ ፖለቲካ ሆኖ እንደቆየ ሁላችንም የምናውቀው ጉዳይ ነው። ትንሽም ጉዳዩን በአዲስ ዐይን መመልከት የተጀመረው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አዲስ የፖለቲካ መስመር ከቀየሱ በኋላ ነው። በአፋኝነቱና ጨፍጫፊነቱ የሚታወቀው ደርግ እንኳን ጥያቄውን በቸልታ ሊያልፈው አልቻለም። የብሔረሰቦች ጥናት ኢንስቲቱት አቋቁሞ በአገሪቱ ብሔረሰቦች ባህልና ቋንቋ ላይ ጠቃሚ የሆኑ ሰነዶች ለማከማቸት ችሏል። የኢንስቲቱቱ ሌላ ዐቢይ ተግባር የኢትዮጵያን ሕዝባዊ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት ማርቀቅ ነበር። የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 2 የብሔረሰቦችን እኩልነት ከማረጋገጡም በላይ ክልላዊ የውስጥ አሥተዳደርን (Regional Autonomy) ያረጋግጣል። እሱን ተከትሎም የተወሰኑ ራስ ገዝ አስተዳደሮች ተቋቋሙ። ትምክህተኝነትና ጠባብ ብሔርተኝነትን መዋጋት እንደሚያስፈልግም አፅንኦት ተሰጠው። ይሁን እንጂ ደርግ የወሰዳቸው እርምጃዎች ለይስሙላ ያህል እንጂ በሐቀኛ መርህ ላይ የተመሠረቱ አልነበሩም። ለዚህም ጥሩ ማረጋገጫው የኤርትራንም ሆነ የትግራይን ችግር ከሰላም ይልቅ በጦርነት ለመፍታት መሞከሩ ነው። የሰላሙ መንገድ በቅጡ የተገለጠለት ነገር ሁሉ ካበቃለት በኋላ በ11ኛው ሰዓት ነው።
እንደሚታወቀው ተማሪዎች የተለሙት የብሔረሰቦች የራስን ዕድል የመወሰን መብት እስከ መገንጠል ድረስ ሙሉ በሙሉ ሕጋዊ መገለጫ ያገኘው በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ነው። የሕገ መንግሥቱ መግቢያ “እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች” ብሎ ነው የሚጀምረው። በተለይም እስካሁንም አወዛጋቢ ሆኖ በቆየው አንቀጽ 39 የመገንጠልን መብት በማያሻማ መንገድ አረጋግጧል። ይህ አንቀጽ ሁለት አስገራሚ ገፅታዎች አሉት። አንዱ የመገንጠልን መብት ከሁሉ አስቀድሞ በንዑስ አንቀጽ 1 ላይ ማስቀመጡ ነው። አንድ ብሔረሰብ መብቱ ስለታገደበት ወይም ስለተሸራረፈበት ሳይሆን ከመሬት ተነስቶ የመገንጠል መብቱ እንዲከበርለት ሊጠይቅ ይችላል ማለት ነው። የብሔረሰቦች ልዩነት አጽንኦት የተሰጠውን ያህል ስለ አንድነታቸውና ትስስራቸውም በተጓዳኝ ቢገለጽ መልካም ነበር። ነገር ግን ይህ ዓይነቱ ማረቂያ ሐሳብ እዚህ በመገለጽ ፈንታ ወደ አንቀጽ 88 ተወርውሯል። በሌላ ርዕስ ስር ስለተቀመጠም ብዙ ሰው መኖሩንም በደንብ ሳያጤነው ቆይቷል።
ሁለተኛው በንዑስ አንቀጽ 5 ላይ ለሦስቱም ምድቦች (ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ) የጅምላ ፍቺ መስጠቱ ነው። ከላይ እንዳየነው በተማሪዎቹ ንቅናቄ በብሔርና በብሔረሰብ መካከል ያለውን ልዩነት ለማስረዳት የተደረገው ሙከራ ያን ያህልም የሚያረካ አልነበረም። አሁን ደግሞ ሦስተኛ ምድብ (“ሕዝብ”) መጨመሩ ነገሩን የባሰ ውስብስብ አድርጎታል። ነገሩ የተዋረድ አንድምታ ቢኖረውም፤ እስካሁን ድረስ በምድረ ኢትዮጵያ ማን ብሔር፣ ማን ብሔረሰብ፣ ማን ደግሞ ሕዝብ እንደሆነ ግልፅ አይደለም። አንዳንዴ ይህን ችግር “ብሔር ብሔረሰቦች” በሚል ጠቅለል ያለ ገለፃ ለመወጣት ሲሞከር ይታያል፡፡ ነገሩ ድሮ ብይ ስንጫወት “ሰይ ብል፣ ባንከረባብት” የምንለው ዓይነት መሆኑ ነው። ውዥንብሩ “የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች” ተብሎ በተሰየመው ክልል ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል።
ትምህርቱ
እንግዲህ መጨረሻ ላይ ልናይ የሚገባን ከዚህ ትንታኔ የወደፊቱን ፖሊሲ ለመቀየስ የሚረዳ ምን ትምህርት እናገኛለን የሚለውን ጉዳይ ነው። ተማሪው ለብሔረሰብ ጥያቄ የሰጠው መፍትኄ ምን ያህል የኢትዮጵያን ታሪክና ነባራዊ ሁኔታ እንዳላገናዘበ ከላይ ካደረግነው ገለፃ ተረድተናል ብዬ አምናለሁ። የመፍትኄው መሠረት ታሪካዊ እውነታ ሳይሆን ስታሊናዊ ቀኖና ነበር። አሁን ኢትዮጵያ የምትተዳደርበት ሕገ መንግሥት የተማሪውን የመፍትኄ ሐሳብ ሳይበርዝና ሳይከልስ ነው የደነገገው። ስለሆነም አሁን አገሪቱ መሠረታዊ የሆኑ የማሻሻል እርምጃዎች በምትወስድበት ጊዜ ሕገ መንግሥቱንም እንደገና መርምሮ ማሻሻል ያስፈልጋል። ሕገ መንግሥት ጽላተ ሙሴ ወይም መጽሐፍ ቅዱስ አይደለም። ከሌሎች አገሮች ተመክሮ እንደምናየው በየጊዜው ወቅቱን ያገናዘበ ማሻሻያ የሚደረግለት መነሻ ሰነድ እንጂ።
ስለሆነም በተለይ የብሔረሰቦችን ጉዳይ በተመለከተ የሚከተሉትን የማሻሻያ ሐሳቦች ላቀርብ እፈልጋለሁ።
ከፍተኛ ብዥታ ያለበትን “ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ” የሚለውን አገላለጽ አንድ ወጥ በሆነ “ብሔረሰብ” በሚል ቃል መተካት፡፡ ይህ በብሔረሰቦች መካከል የማበላለጥ ስሜትን አስወግዶ ሁሉንም በእኩል ደረጃ ያስቀምጣቸዋል፡፡ በተለይ “ሕዝብ” የሚለውን አጠራር በማስቀረት ይህ አጠራር ያነጣጠረባቸው ብሔረሰቦች የሚሰማቸውን የዝቅተኛነት ስሜት ያስወግዳል፡፡ ይልቁንስ “ሕዝብ” የሚለውን መጠሪያ ልዕልና ሰጥቶ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መጠሪያ ማድረግ፡፡
ባለሥልጣናት “የኢትዮጵያ ሕዝቦች” ብለው ንግግራቸውን ሲጀምሩ ለጆሮ በጣም የሚከብድ ነገር ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ባላነሰ ሁኔታ ቅይጥ የሆነው የአሜሪካ ሕዝብ እንኳ በነጠላው እንጂ በብዙኃኑ ሲጠራ አንሰማም፡፡ ‹‹የጀርመን ሕዝቦች››፣ ‹‹የስዊትዘርላንድ ሕዝቦች››፣ ወይም ‹‹የናይጄሪያ ሕዝቦች›› ሲባልም አንሰማም፡፡ ስለዚህ ሳንፈራ ሳንቸር ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ›› ብለን መናገር መጀመር ይኖርብናል፡፡
አንቀጽ 39ኝን እንደገና በመመርመር የብሔረሰቦችን ቋንቋና ባህል የማዳበሩ ንዑስ አንቀጽ እንዳለ ሲቆይ በሚያስገርም ሁኔታ በንዑስ አንቀጽ 1 ቅድሚያ የተሰጠው የመገንጠል መብት መሰረዝ ይኖርበታል። በአንቀጽ 88 ውስጥ የተወሸቀው ብሔረሰቦች አንድነታቸውንና ትስስራቸውን እንዲያጠናክሩ የሚያበረታታውና መንግሥትም ይህንን የሚያግዙ እርምጃዎች እንደሚወስድ የሚገልጸው ንዑስ አንቀጽ ወደ አንቀጽ 39 መምጣት ይኖርበታል፡፡
ይህንኑ ትስስርና አንድነት ለማጠናከርም መንግሥት በትምህርት ቤቶችና በዩኒቨርሲቲም መጀመሪያ ዓመት ይሰጥ የነበረውን የኢትዮጵያ ታሪክ ማስተማር እንደገና መመለስ አለበት፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርትን በተመለከተ በትምህርት ሚኒስቴር በኩል የታሰበ ነገር እንዳለ ተረድቻለሁ፡፡ ይህ ተጠናክሮ ዳር መድረስ ሲገባው፤ በዩኒቨርሲቲ ደረጃም ያለ በቂ ምክንያተ የታጠፈው የጀማሪ ተማሪዎች መርሀ ግብር ተመልሶ ተማሪዎች ወደ መረጡት ሙያ ከመሰማራታቸው በፊት ስለ አገራቸው ጄዎግራፊ፣ ታሪክና ባሕል በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው መደረግ አለበት፡፡
ብሔራዊ መግባባትንና የባህል መወራረስን ለማዳበር የአፋን ኦሮሞ ትምህርት ከአማርኛ ጋር በመላ የኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች መሰጠት ይኖርበታል፡፡ ሁኔታውን ምቹ ለማድረግ ግን አፋን ኦሮሞ በግዕዝ ፊደላት ተጽፎ ቢቀርብ ይመረጣል፡፡ አያሌ የቋንቋ ሊቃውንት እንዳስረዱት አፋን ኦሮሞ ያሉትን ሁለት ልዩ ባሕርያት (ማለትም ዸ እና የአናባቢዎች መርዘም) ልዩ ምልክቶች (diacritical marks) በማድረግ መግለፅ ይቻላል፡፡ በዚህ ረገድ መርሳት የሌለብን ነገር ከመቶ ዓመት በፊት ኦኖሲሞስ ነሲብና አስቴር ገኖ የአፋን ኦሮሞ መጽሐፍ ቅዱስን (መጫፈ ቁልቁሉ) በግዕዝ ፊደላት ሊጽፉ እንደቻሉ ነው፡፡
Filed in: Amharic