>

መንግስት ሲደናበር ለውጡ ነውጥ እንዳይወልድ....!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

መንግስት ሲደናበር ለውጡ ነውጥ እንዳይወልድ….!!!

ያሬድ ሀይለማርያም

* …. ልክ የዛሬ ሁለት አመት አድማጭ ካለ ብለን ይችን ጭረን ነበር። ‘ነበር ምን ዋጋ አለው?!?’ ያለው ማን ነበር?!
 
ከገዠው ፓርቲ አባል ድርጅቶች እየወጡ ያሉት መግለጫዎች ሥርዓቱ ከራሱ ጋር እየተቃረነ እና ለነውጥ ኃይሎችም ሁኔታዎችን እያመቻቸ ይመስላል።
+ የአማራ ክልል እና የትግራይ ክልል መንግስታት ትላንትና እና ዛሬ የተወነጫጨፉት የመግለጫ ተኩስ እንዲህ በቀላሉ የሚታለፍ አይደለም። ክልሎቹ ለጦርነት መዘጋጀታቸውን አንዱ ሌላውን በሚከስበት መግለጫቸው ገልጸዋል። ከመግለጫም አልፎ መሬት ላይ በግልጽ በሚታይ መልኩ ወታደራዊ ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው።
+ ሌላው አስደማሚ መግለጫ ደግሞ ዛሬ ማምሻውን ኦዴፓ ያወጣው ማስጠንቀቂያና ዛቻ አዘል መግለጫ ነው። መግለጫው የአዲስ አበባ መስተዳድርን እና የፌደራል መንግስቱን የሚያስጠነቅቅ ይመስላል። የኦዴፓ መግለጫ የበለጠ ትኩረት የሚስበው የድርጅቱ ሊቀመንበር የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፌደራል መንግስት ከሚያራምዱት አቋም ጋር የሚጣረስ የሚመስለውን የፓርቲያቸውን መግለጫ እንዴት ያዩታል የሚለው ነው። ተስማምተውበታል ወይስ ባላየ ችላ በለው ያልፉታል ወይስ የተለየ ቋም አላቸው የሚለው ግልጽ አይደለም።
+ ሌላው መግለጫ በአዲስ አበባ ጉዳይ አዴፓ እና ኦዴፓ እጅግ የሚጣረስ አቋም የተንጸባረቀበት መግለጫ ማውጣታቸው እና አዴፓም ጥብቅ ማሳሰቢያ መስጠቱ ነው።
እነዚህ የክልል መንግስታት እርስ በእርሳቸው እና ከማዕከላዊ መንግስቱ ጋር የሚቃረኑ እና የሚጋጩ መግለጫዎችን ከየአቅጣጫው ማውጣታቸው ለውጡን ተስማምተው በጋራ እየመሩ አለመሆኑን ነው የሚያመላክተው። ወይም በጋራ ተስማምተው እና አቅደው እየተጓዙ አይደለም። ይህ አይነቱ ችግር ደግሞ ሳይዘገይ መፍትሔ ካልተበጀለት አገሪቱን ወዳልተፈለገ ግጭት ይከታታል የሚል ስጋት በብዙዎ ዘንድ ተፈጥሯል።
የእነዚህ ኃይሎች በዚህ ደረጃ በአደባባይ መወንጃጀል እና መፍረክረክ ለሌሎች በነውጥ ጉዳያቸውን ማስፈጸም ለሚፈልጉ ጽንፈኛ ኃይሎች ጉልበት ሊፈጥርላችው ይችላል የሚል ስጋትም አለ።
በመንግግስት ኃይሎች በኩል ሳይዘገይ ሊከወኑ የሚገባቸው ነገሮች ብዮ የማስበው፤
+ ሁሉም የክልል አካላት ከሚያወጧቸው መግለጫዎች እና የሚዲያ ንትርክ ታቅበው ችግሮቻቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት ባፋጣኝ መቀመጥ ካልቻሉ፤
+ አወዛጋቢ በሆኑት እንደ አዲስ አበባ የባለቤትነት ጥያቄ እና ሌሎች የግጭት መንስዔ በሆኑ ጉዳዮች የጋራ አቋም ወይም በነዚህ ነጥቦች ዙሪያ ያሉትን ችግሮች ሊፈቱ በሚችሉበት አግባብ ላይ አንድ አይነት ስምምነት ላይ ካልደረሱ፤
+ በአገሪቱ ጎልቶ እየታየ ያለውን ሕገ ወጥነት እና የተወሰኑ ቡድኖች ከሕግ በላይ በመሆን ዜጎችን ማስፈራራት እና ስጋት ውስጥ እየጣሉ ያለበትን ሁኔታ በአፋጣኝ እና በሕግ አግባብ ማስቆም ካልቻሉ፤
+ በተለያዩ ሚዲያዎች እና በአደባባይ በግልጽ ቋንቋ ሕዝብን ለእርስ በእርስ ግጭት የሚቀሰቅሱ፣ ዜጎች ሕግ እንዳያከብሩ የሚያነሳሱ ሰዎችን እንዲታቀቡ መምከር እና መገሰጽ ካልቻሉ፤
+ በአገሪቱ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ሕገ ወጥ የመሳሪያ ዝውውር መግታት እና የታጠቁ ግለሰቦችም መሳሪያቸውን እንዲያስመዘግቡ፣ እንዲሁም በአደባባይ መሳሪያ እያነገቡ (ሜጫንም ይጨምራል) ሕዝብ በተሰበሰበበት ስፍራ መንቀሳቀስም ሆነ አደባባይ መውጣትን አጥብቀው ካልከለከሉ እና ይህን በሚተላለፉ ሰዎች ላይ አፋጣኝ ሕጋዊ እርምጃ የማይወስዱ ከሆነ፤
+ አገሪቱ እስክትረጋጋ ድረስ ከልማት ጋር በተያያዘ ዜጎችን ስጋት ላይ የሚጥሉ የቤቶች ማፍረስ ወይም ማፈናቀልም ሆነ የማስፈር ስራዎችን ለጊዜው መግታት እና ነገሮችን እንደገና በጥናት እና ጥንቃቄ በተመላው መልኩ ማከናውን ካልቻሉ፤
+ የድንበርም ሆነ የማንነት ጥያቄ በተነሳባቸው ሥፍራዎች ላይ ያለውን ውጥረት ለማርገብ ላልተወሰነ ጊዜ አካባቢዎቹን ከክልል አስተዳደር ነጻ አድርጎ ችግሮቹ በሕግ እና በፖለቲካ ድርድር እስኪፈቱ ድረስ ነጻ ቀጠና ሆነው በፌደራል መንግስቱ ቁጥጥር ስር እንዲቆዩ እና የክልል ታጣቂዎች ከአካባቢዎቹ ገለል ብለው እንዲቆዩ እና በምትካቸው የፌደራል የጸጥታ ኃይል እንዲሰፍር ካልተደረገ፤
አገሪቱ ዳግም ወደ ፖለቲካ አለመረጋጋት እና እርስ በርስ ግጭት ልታመራ ትችላለች።  ይህ ችግር የሚያሳስባቸው የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የሲቪክ ማህበራት፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራን እና የመብት አቀንቃኞች በእነዚህ ዙሪያ ያላቸውን ስጋት በጋራ በመግለጽ መንግስት ለጉዳዩ አፋጣኝ እና አግባብነት ያለው ምላሽ እንዲሰጥ ማሳሰብ ይኖርባቸዋል። ማሳሰብ ብቻ ሳይሆን ችግሩን ለመፍታትም አብረው ሊሰሩ ይገባል።
በፉክክር ስሜት ተወጥረን ነገሮችን በማራገብ ወይም የሌላውን ጩኸት ችላ በማለት ወይም ማዶና ማዶ ቆሞ በመናቆር አገርን መታደግ አይቻልም። የተፈጠሩት መልካም እድሎች እንዳይጨናፉና አገር በጮሌዎች እና በጠባብ ዘረኞች እጅ ወድቃ ወደ ሌላ የመከራ እና የግፍ ዘመን እንዳናመራ ከወዲሁ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል።
ቸር ያሰማን!
Filed in: Amharic